ፀሐይ ባንክ ሐምሌ 16 ቀን 2014 ሥራውን በይፋ ጀመረ

ፀሐይ ባንክ ለሁሉ” በሚል መሪ ቃል በ2.9 ቢሊዮን ብር የተፈረመና በ734 ሚሊዮን ብር በሥራ ላይ በዋለ ካፒታል፤ 373 ባለአክሲዮኖች ይዞ ሥራ የጀመረው ፀሐይ ባንክ በዛሬው ዕለት አገልግሎት መስጠት መጀመሩን አስታውቀ።

ሃምሌ 14  ቀን 2014 ዓ.ም ባንኩ በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ – ባንኩ ዝቅተኛ የአክሲዮን ግዢውን ከብር 100 ሺህ በመጀመር፣ በ373 ባለአክሲዮኖች ባንክን ለመስረት የሚያስችለውን ካፒታል በማሰባሰብና የመስራች ጉባኤውን የካቲት 11 ቀን 2013 በሸራተን አዲስ ሆቴል በማካሄድ፤ የባንክ ኢንዱስትሪውን መቀላቀሉን የባንኩ ዋና ሥራ አስኪያጅ ያሬድ መስፍን ተናግረዋል፡፡

በዚሁ ጋዜጣዊ መግለጫ << ዓላማችን የባንክ አገልግሎት ብቻ ሳይሆን በፋይናንስ ዘርፉ በቂ ትኩረት ያላገኙትን የስራ ፈጠራን እና የስራ ፈጣሪዎችን፤ የጥቃቅንና አነስተኛ፣ የግብርናውን ዘርፍ እንዲሁም የአምራች ኢንዱስትሪውን ተደራሽ ለመሆን አልመናል>> ብለዋል የባንኩ ዋና ሥራ አስኪያጅ ያሬድ መስፍን።

የባንኩ የቦርድ ሰብሳቢ  ታየ ዲበኩሉ ደግሞ በሀገሪቱ ያሉ ባንኮች ቁጥር እና የኅብረተሰብ ተደራሽነት ዝቅተኛ በመኾኑ ፀሐይ ባንክ ይህንን ለመቅረፍ አጋዥ ኾኖ ወደ ሥራ ይገባል ሲሉ አስታውቀዋል።

የሀገሪቱ የባንክ ተደራሽነት ከሰሀራ በታች ካሉ 7 ሀገራት አማካይ በታች መኾኑን ያነሱት አቶ ታየ በኬንያ 82 በመቶ የባንክ ተደራሽነት ያለ ሲኾን በኢትዮጵያ ግን ከ20 በመቶ አይበልጥም ነው ያሉት።

የባንኩ የቦርድ ሰብሳቢ የሀገሪቱ ቁጠባ ኢንቨስትመንቱን ገና ፋይናንስ ማድረግ እንዳልቻለ ገልጸው ፀሐይ ባንክ ቁጠባን ማሳደግ የሚችል አሠራር እንደሚከተል አስረድተዋል።

ዛሬ ሃምሌ 16 ቀን 2014 ዓ.ም – በባንኩ የሥራ ማስጀመሪያ መርሀ ግብር ላይ የተገኙት የኢትዮጵያ ብሄራዊ ባንክ ገዢ ዶ/ር ይናገር ደሴ፤ በአገራችን ከፍተኛው የማህበረሰብ ክፍል በፋይናንስ ሥርዓት ተደራሽ አለመሆኑን ገልጸው፤ ስለዚህም የባንኮች ቁጥር መጨመር ይህን ክፍተት በመሙላት በማህበረሰቡ ውስጥ የፋይናንስ ተቋማት በሥፋት ዕውቅና እና ተቀባይነት እንዲኖራቸው የሚኖረው ፋይዳ ከፍተኛ ነው ብለዋል።

“በባንኮች ውስጥ ያለው ሀብት የህዝብ ሀብት ነው።” ያሉት ገዢው፤ ስለዚህ ባንኮች ይህን ሀብት በበላይነት የሚጠብቀውን እና የሚቆጣጠረውን የኢትዮጵያ ብሄራዊ ባንክ መመሪያ፣ ደንቦችና አዋጆች አክብረውና ጠብቀው ሊሰሩ እንደሚገባ አሳስበዋል።

አክለውም፤ በኢትዮጵያ ውስጥ ተቋቁሞ አንድም ከስሮ ከገበያ የወጣ የፋይናንስ ተቋም አለመኖሩን በማንሳት፤ “ይህም የሆነው ብሄራዊ ባንክ የሚያደርገው ክትትል እና ድጋፍ ጠንካራ በመሆኑ ነው” ብለዋል።

ፀሐይ ባንክ ወደ ባንክ ኢንዱስትሪው ዘግይቶ ቢመጣም ዘመኑ የደረሰባቸውን የባንክ ቴክኖሎጂዎችን፣ ብቁ የሠራተኛ አቅም እና ቀልጣፋ የአገልግሎት አሰጣጥ ሥርዓትን ከተጠቀመ ትላልቅ የሚባሉት ባንኮች የደረሱበት ቦታ ላይ በቅርብ ጊዜ ውስጥ የማይደርስበት ምንም ምክንያት እንደማይኖር ዶ/ር ይናገር ተናግረዋል።

በተጨማሪም፤ በአጭር ጊዜ ውስጥ የውጭ ባንኮች ወደ አገር ውስጥ እንዲገቡ የቅድመ ዝግጅት ሥራዎች እየተጠናቀቁ መሆኑን የጠቆሙት ገዢው፤ የአገር ውስጥ ባንኮች ወድድሩን በማሰብ ጠንክረው መሥራት እንደሚገባቸውም አሳስበዋል፡፡

በአሁኑ ሰዓት በ30 ቅርንጫፎች አገልግሎት መስጠት የጀመረው ፀሐይ ባንክ በቅርብ ቀናት የቅርንጫፍ ብዛቱን ወደ 50 እንደሚያሳድግ የገለጹት ደግሞ የባንኩ ዋና ሥራ አስኪያጅ ያሬድ መስፍን ሲሆኑ፤ በአንድ ዓመት ውስጥም የቅርንጫፎቹን ብዛት በኹሉም የአገራችን አካባቢዎች በማስፋት 100 ለማድረስ እቅድ መያዙንም ተናግረዎል።

የባንኩ የዳይሬክተሮች ቦርድ ሰብሳቢ ታዬ ዲበኩሉ በበኩላቸው፤ ፀሐይ ባንክ የባንክ ኢንዱስትሪውን ክፍተት በተረዱና ለትውልድ የሚሻገር ተቋም የመመስረት አላማን ባነገቡ 11 የአዳራጅ ኮሚቴ አባላት አማካኝነት 373 ባለአክሲዮኖች ይዞ ሥራ መጀመሩን ገልጸዋል።

በባንኩ ይፋዊ የሥራ ማስጀመሪያ መርሀ ግብር ላይም፤ ለኢትዮጵያ የልብ ህሙማን ህፃናት መርጃ ማዕከል የ500 ሺህ ብር፣ ለኩላሊት ህመምተኞች በጎ አድራጎት ድርጅት የ500 ሺህ ብር፣ ለኒያ ፋውንዴሽን የ300 ሺህ ብር እንዲሁም ለጌርጌሴኖን የአይምሮ ህሙማን መርጃና ማገገሚያ ማዕከል የ300 ሺህ ብር በአጠቃላይ የ1 ነጥብ 6 ሚሊየን ብር ስጦታ ተበርክቷል።

Kumneger Media
Kumneger Media is Ethiopian News and Entertainment Website & Channel. It is a hub of Ethiopian News, Politics, Movies, Drama, Music, Comedy, Documentary and More!

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

ትስስር ይፍጠሩ

325,851FansLike
49,039FollowersFollow
13,194SubscribersSubscribe