ፌሊክስ ሺሴኬዲ – አዲሱ የኮንጎ ተስፋ

መያዛቸው ተረጋግጦ አፍሪካዊቷን ጣጠኛ ሀገር መምራት ከጀመሩ ሳምንታት ተቆጥረዋል፡፡ የሃምሳ አምስት ዓመቱ ሺሴኬዲ ከመራጮች 38.57 የሆነ ድምጽ በማግኘት የዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎን ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ ያሸነፉት፤ ማርቲን ፋዩሉ የተባሉትንና 34.8 በመቶ ድምጽ ያገኙትን ተቀናቃኛቸውን በመርታት ነው፡፡ ተቀናቃኛቸው የምርጫውን ውጤት ሳይቀበሉት ቀርተዋል፡፡ የዘንድሮው ምርጫ ውጤትም ሀገሪቱ እ.ኤ.አ በ1960 ከቤልጂየም ቅኝ ግዛት ነፃ ከወጣችበት ጊዜ ወዲህ ለመጀመርያ ጊዜ ሰላማዊ ሽግግር የተካሔደበት ኾኗል፡፡

ጉዞ ወደ ምርጫ

ቡጂ ማዪ የተባለችውን የሀገሪቱን ሦስተኛ ትልቅ ከተማ በመወከል እ.ኤ.አ በ2011 ወደ ኮንጎ ፓርላማ ለመግባት ተመርጠው የነበረ ቢሆንም በዚያው ዓመት አባታቸው በጆሴፍ ካቢላ የተሸነፉበትን ፕሬዚዳንታዊ የምርጫ ውጤት መቀበል ባለመፈለጋቸው ወደ ፓርላማ ሳይገቡ ቀርተዋል፡፡

እ.ኤ.አ በ1982 በአባታቸው የተመሠረተውን ‹ዩኒየን ፎር ዲሞክራሲ ኤንድ ሶሻል ፕሮግረስ› የተባለ በዕድሜ አንጋፋና ከፍተኛ ተቀባይነት ያለው የፖለቲካ ፓርቲ መሪ የኾኑት ሺሴኬዲ በፖለቲካው መስክ በቂ ልምድ የላቸውም የሚል ትችት ከተቀናቃኞቻቸው ይሠነዘርባቸዋል፡፡ እርሳቸው ግን ‹‹ከአንዳንድ ተቀናቃኞቼ የተሻለ ልምድ አለኝ፡፡ ወደ ፖለቲካ የገባሁት ከሃያ አምስት ዓመት በፊት ነው›› በማለት ይከራከራሉ፡፡ ‹‹እኔ የአባቴ ልጅ ነኝ፤ ነገር ግን እኔ የራሴ ሰውም ነኝ›› ይላሉ፡፡

ሺሴኬዲ የአምስት ልጆች አባት ናቸው፡፡ ሀገሪቱ ከቤልጂየም ቅኝ ግዛት ነፃ ከወጣችበት ጊዜ ወዲህም ፕሬዚዳንት ለመሆን አምስተኛው ሰው ናቸው፡፡ በዋና ከተማዋ ኪንሻሳ የተወለዱት ሺሴኬዲ በገበያና ግንኙነት ዘርፍ ትምህርታቸውን በቤልጂየም ተከታትለው በዲፕሎማ ተመርቀዋል፡፡ ሺሴኬዲ ለረጅም ዓመታት በካቢላ ቤተሰብ ቁጥጥር ስር የነበረውን የኮንጎ ፕሬዚዳንትነት መረብ ለመበጠስ ከስድስት ተቃዋሚ አጋሮቻቸው ጋር በመሆን በጆሴፍ ካቢላ ለቀጣዩ ፕሬዚዳንትነት ተዘጋጅተው የነበሩትን ኢማኑኤል ራማዛኒ ሻዳሪ ማሸነፍ ይችላሉ ብለው ያመኑባቸውን ማርቲን ፋዩሉ የተባሉ ሰው በመደገፍ ነበር የዘንድሮውን ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ የተቀላቀሉት፡፡ በኋላ ግን ‹ደጋፊዎቼ በተመራጮች ዝርዝር ውስጥ እንድካተት ይፈልጋሉ› የሚል ጥያቄ በማንሳት ከሌሎቹ ፖለቲከኞች ጋር የገቡበትን ስምምነት አፍርሰው መወዳደር ጀመሩ፡፡ በምረጡኝ ዘመቻቸውም ሙስናና ድህነትን እዋጋለሁ በማለት ለሕዝባቸው ቃል ገቡ፡፡ ፉክክሩን ካሸነፉ በኋላ ግን ከተለያዩ አካላት ቅሬታ ቀርቦ ነበር፡፡

የዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ የምርጫ ኮሚቴ ያወጣውን ውጤት ያልተቀበሉት ተፎካካሪው ማርቲን ፋዩሉ ብቻ ሳይሆኑ ፈረንሳይና ቤልጂየም እንዲሁም በሀገሪቱ ከፍተኛ ተከታዮች ያሏት የካቶሊክ ቤተክርስቲያንም ነበሩ፡፡ 40 ሺህ ያህል የምርጫ ታዛቢዎችን ያሳተፈችው የካቶሊክ ቤተክርስቲያን የምርጫው ውጤት እርሷ ከመዘገበችው ውጤት ጋር የሚለያይ መሆኑን ስትገልጽ ቤልጂየም በበኩሏ በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ውስጥ ያላትን የፀጥታው ምክር ቤት ተሳታፊነት በመጠቀም ጉዳዩን ለውይይት እንደምታቀርበው ገልጻ ነበር፡፡ የአፍሪካ ህብረት ደግሞ በምርጫው ሰበብ የሚፈጠሩ አለመግባባቶች ወደ ግጭት ሳያመሩ በንግግር ብቻ እንዲፈቱ አሳስቦ ነበር፡፡

የሰሞኑ ሰላማዊ የስልጣን ርክክብ፤ ጆሴፍ ካቤላ በሕገ – መንግሥቱ የተፈቀደላቸው የፕሬዚዳንትነት ዘመን አብቅቷል በሚል ላለፉት ሁለት ዓመታት ከሀገሪቱ ሕዝብ በተለያዩ መንገዶች ሲሰነዘሩ የነበሩ ተቃውሞዎች ማብቂያ እንደሚሆን ታምኗል፡፡ የኬንያው ፕሬዚዳንት ኡሁሩ ኬንያታና የተቃውሞ መሪው ራይላ ኦዲንጋን ጨምሮ የጎረቤት ሀገራት ተጋባዥ እንግዶች የተገኙበት የቃለ መሃላ ሥነ ሥርዓት በቀጥታ የቴሌቪዥን ስርጭት በተላለፈ የእንኳን ደስ አላችሁ መልእክታቸው ላይ ‹ደህንነት እየተሰማኝ አይደለም› በማለት ንግግራቸውን አቋርጠው የነበረ መሆኑ አነጋጋሪ ሆኗል፡፡ ተመልሰው ባጠናቀቁት መልእክትም ሀገሪቱ የክፍፍልና የጥላቻ ሆና እንደማትቀጥል ተናግረዋል፡፡ ‹‹በባህላዊ ስብጥሯ ያማረች ኮንጎን መገንባት እንፈልጋለን፡፡ ዕድገቷንም በሰላምና ደህንነት ማጀብ እንፈልጋለን፡፡ ሁሉም የራሱን ድርሻ የሚይዝባትንና ለእያንዳንዱ ዜጋ የምትሆን ኮንጎ እንገነባለን›› ብለዋል፡፡

የኮንጎ አዲስ ምዕራፍ?

ከዓለም የኮባል ማዕድናት 60 በመቶውን የምታመርተው ኮንጎ በአፍሪካ ሁለተኛዋ የመዳብ አምራች ሀገር ብትሆንም ዛሬም ድረስ በድህነት ማጥ ውስጥ ተዘፍቃለች፡፡ ጤናማ የሚባል የኋላ ታሪክም የላትም፡፡

እ.ኤ.አ ከ1996 እስከ 1997 እንዲሁም ከ1998 እስከ 2003 ድረስ የዘለቀ የእርስ በርስ ጦርነት አስተናግዳለች፡፡ እ.ኤ.አ በ2006 እና በ2011 የተካሔዱትና በጆሴፍ ካቤላ አሸናፊነት የተቋጩት ፕሬዚዳንታዊ ምርጫዎችም በግጭትና ደም መፋሰስ ነበር የተጠናቀቁት፡፡ ከተደጋጋሚ ግጭቶችና በተለይ ምሥራቃዊ ክፍሏን ክፉኛ እያጠቃ ከሚገኘው የኢቦላ ቫይረስ ጋር ተዳምሮ ባለ ሠማንያ ሚሊየን ዜጎች ሀገሯን ኮንጎ መምራት እጅግ ከባድ ይመስላል፡፡ የወርቅ፣ የአልማዝና የመዳብ አምራቿ ኮንጎ በማዕድናት የመበልፀጓን ያህል ሕዝቦቿ በአስተሳሰብ የበለፀጉ አለመሆናቸው ተፍሮ ያደላትን ፀጋ ያልተጠቀመች ምስኪን ሀገር አድርጓታል፡፡ እዚህ ላይ ስር የሰደደው የሙስና ችግር ሲጨመር ደግሞ ሀገሪቱ በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሰው ልጆች ሁሉን አቀፍ ልማት መለኪያ መሠረት ከዓለም 189 ሀገራት መካከል 176ኛ ደረጃ ላይ እንድትገኝ አድርጓታል፡፡

የመጀመርያው የሀገሪቱ ፕሬዚዳንት የነበሩት ፓትሪስ ሉሙምባ እ.ኤ.አ በ1961 በመፈንቅለ መንግሥት ከስልጣን ወርደዋል፡፡ ቀጣዩ ፕሬዚዳንት ሞቡቱ ሴሴሴኮም ከሦስት አሥርት ዓመታት በላይ ሀገሪቱን ከመሩ በኋላ በአመፀኛው ሎረን ካቢላ በ1997 የመንግሥት ግልበጣ ተካሒዶባቸዋል፡፡ ካቢላ እ.ኤ.አ በ2001 መገደላቸውን ተከትሎ ደግሞ ልጃቸው ጆሴፍ ነበሩ በሃያ ዘጠኝ ዓመታቸው የአባታቸው ዙፋን ላይ ወጥተው ላለፉት አሥራ ስምንት ዓመታት ኮንጎን ሲመሩ የቆዩት፡፡

የቀድሞው ፕሬዚዳንት ጆሴፍ ካቢላ ከአዲሱ ፕሬዚዳንት ፌሊክስ ሺሴኬዲ ጋር ተመሳጥረው ‹ሰርቀውኛል› ያሉትን ስልጣን በሰላማዊ ትግል መቃወም እንደሚጀምሩ መናገራቸውም በድህረ – ምርጫ የሚኖረው የኮንጎ አየር ንብረት ሰላማዊ እንደሚሆን ፍንጭ የሰጠ ይመስላል፡፡

አሁን የኮንጓውያን ዓይን አዲሱ ሰው ላይ አርፏል፡፡ አዲሱ ሰው ለዓመታት በሙስና የማቀቀችውን፣ ድህነት ድር ያደራባትንና በፖለቲካ ልዩነት ዜጎቿ ደም ሲፋሰሱባት የኖረችውን ሀገር አዲስ ምዕራፍ ይገልጻሉ ተብሎ ይጠበቃል፡፡ ከካቢላ ጋር ባላቸው ቅርበት ምክንያት እ.ኤ.አ ከ1997 ጀምሮ በኮንጎ ገናና ሆኖ የኖረው የካቢላ ቤተሰብ አስተዳደር ስም ብቻ ቀይሮ በመምጣቱ ምንም ለውጥ አይኖርም የሚል አስተሳሰብ ያላቸውም አሉ፡፡

Kumneger Media
Kumneger Media
Kumneger Media is a News and Entertainment Website & Channel. Kumneger Media in addition to News and Entertainment it is the hub of Politics, Movies, Drama, Music, Comedy, Documentary and More!

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

ትስስር ይፍጠሩ

325,851FansLike
49,039FollowersFollow
13,194SubscribersSubscribe