ፓለቲካዊ ኦፔራ /በአያ እሸቴ ካናዳ ቶሮንቶ/

አያ እሸቴ ከቶሮንቶ

ፓለቲካዊ ኦፔራ

ነገራችን ሁሉ ሶፕ ኦፔራ መሰለሳ! እናንትዬ ረጅም ትረካና አንድ ዓይነት ሰዎች ፓለቲካ መድረኩን ሞሉትኮ። ገፅ ባህሪያት ሆኑ እንዴ? የሽህ ስፒር ” ዓለም ቲያትር ናት። ተዋናኞቹም እኛ” እንዳለው ይሆን።

እንግዲህ እየተወኑ መኖር፤እየኖሩ መተወን ሳያስፈልግ አይቀርም። በርናርድ ሾውን፣ በርትሌት ብረሽትን፣ ኢብሰን፣ ጋሽ ፀጋዬን፣ አብዬ የመንግሥቱን፣ …እያሰብክ …የኑሮን ድርሰት ትተውናለህ።

…..ሞዴል ባለሀብት፣ ሞዴል ነጋዴ፣ ሞዴል አርሶ አደር፣ ….በተቃራኒው ከዛ…ማዶ…ከበላተኞች መንደር ደግሞ ወደል ተሿሚ..ወደል በላተኛ…ወደል ካድሬ ተሰልፏል። ካድሬ ጣጣ አለው ካይዘን የሚባል የጃፓን አስማት ይጠራና ….ያስደነግጥህል። ውቃቤው ሲያስለፈልፈው በቀዥቃዣ ጋዜጠኛ አፍ ሳይፈራ ሳያፍር… “በያዝነው የበልግ ወቅት አስር ሚልዩን ቶን ሰብል ተሰብስቧል…” ይለፈልፋል ሰሚ እስከሚጠፋ ይጮሃል። ከነዓንን እንደወረስክ አድርጎ  ይሰብክሀል። የማታየውን ለውጥ፣ የማትበላውን ምርት፣ የማትገዛውን የማትሸጠውን ሸቀጥ በራዲዬ አምርቶ ይሰጥሀል። የማትኖርበትን ቤት ገንብቶ ያሳይሃል። “ዞሮ መግቢያየ” እያልክ እስኪ ዞርብህ ትለፈልፋልህ። ሲነገርህ ታምናለህ…የፖለቲካ ብፁዓን ትሆናልህ። ምክንያቱም ሳታይ አምነሀልና! ልማቱን ካመንክ ደግሞ ሞዴል አማኝ ነህ። በእንተ ሥር አራት አማኞች ይሰጡሀል። ስለዚህ እነሱን ሳያዩ ማየት ታስተምራቸዋለህ። …. ነፃ ማውጣትህ ይቀጥላል…ካይዘንም የዋዛ አይምሰልህ በእግር እግር እየተከተለ “በማስፋት ስትራቴጂ..በመጭው ወራት አገራዊ ምርትን በእጥፍ ለማሳደግ እየተሰራ ነው።” ይልና የልማት መርግ ያሸክምሃል። እውነትህ ቅዥት መሆኑን ብዙም ሳትቆይ ትረዳዋለህ። ተቀበል ብሎ ያውጅብሃል። ትቀባላለህ። አለመጠየቅ የጥበብ መጀመሪያ ነው። ረሃብ በፕሮፓጋንዳና በዓዋጅ ይጠፋ ይመስል …ቁጥርና ዓዋጅ እስኪ ሰለችህ ይፈራረቁብሀል። ያኔ በእውነትና በልማት ስብከት መካከል ያለው ልዩነት ይጠፋብሃል።

ድንገት …. ኦቻ የሚባል     ፀረ-አስማት ደግሞ “እረ ባክህ ንቃ” ብሎ እውነቱን በጆሮህ ሹክ ይልሃል። የፕሮፖጋንዳውን አፍዝ አደንግዝ ያፋርሰዋል። እንተ ግን ውለታውን አሳንስህ “አይ ኦቻ መርዶ ነጋሪ ሆነህ ትቀር!” ትለዋለህ። ታዲያ የካይዘን ጥጋብ ከሆዳችን ሳይጠፋ ቆዳ የለበሱ ህፃናትን ምስል እየላከ መንፈሳችን ሲበጠብጥ ምን ይባላል። ኦቻ ካለ ማን በሰላም ይተኛል።

….ዝም ብለህ ከሰማህ ደግሞ ይሄ አስማት ይመጣና “ሞዴሉን እናስፋው” ይልሀል። በሌላ ቋንቋ እንጠቅልለው ማለቱ ነው። በቃ ዉጤታማ ነዋ! ያልጠቀለልከው ነገር አያስተማምንማ! ሰላም አይሰጥም። አባ ጠቅል መሆን ብቻ ነው የሚያዋጣው። መዝረክርክ ምን ዋጋ አለው። ዘመነ መሳፍንት ዋናው የመዝረክረክ ታሪካችን ነው። ንጉስ ያለ አንጋሽና ቀዳሽ ይነግስ ነበር። ሲነግስ በቅዳሽ ሲወርድ ደግሞ በሻሽ! ዛሬም እንደዛ ነው። አንጋሽም ሻሽም አለ።

የኢትዩጵያ ዘመናዊ የመንግስት አስተዳደር በአጭሩ የመጠቅለል ታሪክ ነው። ግዛት መጠቅለል….ስልጣንን በማዕከል ማሰባሰብ…ብቻ በጋብቻም…በድለላም…በተግሳፅም በምክርም …ግዛት ስትጠቀለል ኖራለች።

ወዛደራዊ አምባገነንነት ግን የተለየ ነው። ሃሳብን ሰልቦ፣ አገራዊ እሴትን አጥፍቶ፣ የነበረውን አፍርሶ፣ ያፈረሰውንም በሚፈልገው ሳይተካ እንዲሁ እልም። “ኢሕድሪን እንመሰርታለን” እንዳለ በዚያው ጠፋ። ጭልጥ …ብን…ጥፍት! ምን አባትክ ትሆናለህ ማለቱ አይደል። መጥፋቱስ ባልከፋ የሚያሳዝነው ለአጥፍቶ ጠፊ መንገድ ጠራጊ መሆኑ ነው።

እኔ ምለው መሬትን የመንግስት ያደረገው “ፋሽስቱ” ደርግ፣ ትርፍ ቤትን ወርሶ ለደሀ ያደለው “ሰው በላው” ደርግ፣ ተቀራማጭ የውጭ ሀይሎችን ሀብት የህዝብ ያደረገው “አውዳሚው” ደርግ። አቤት ፕሮፓጋንዳ ነፍስሽ አይማር! ነጩን ጥቁር፤ ጥቁሩን ነጭ ትቀቢዋለሽ። ዛሬ’ኮ የህዝብን የግል የማድረግ ስራ ነው የሚሰራው። ሃይለ ስላሴ ከጣሊያን የወረሱትን ፋብሪካ ለፈረንጅ አዝማሪ እጅ መንሻ ትሰጣለህ። ከከበርቴ የቀማኸውንና በሰፊው ህዝብ የተያዘን ንብረት መልሰህ ላለፋበት ተቀራማጮች ጀባ ትላለህ። መልከ ጥፉን በስም ..እንደሚባለው ንብረት ዘረፋውን ፕራይቬታዜሽን ትለዋልህ።

ከነጋዴ ቀምተህ ለህዝብ፤ ከህዝብ ቀምተህ ደግሞ ለደላላ…ለግለሰብ። ከተነሳህበት ተመልሰህ ታርፋለህ። ከጀመርክበት ትጨርሳለህ፤ እንደገና ወደ መነሻህ ትዞራለህ። የፀሀይህ መውጫና መግቢያ ይሆንልሃል። በምስራቅ ወጥተህ ወደ ምዕራብ ትመለሳለህ….እንደገና ያንኑ ትደግመዋለህ። ኑረዲን ዒሳ ” እምቧላሌ” የሚላት ነገር ነች። እምቧለሌ ብለህ ትመለሳልህ። የፖለቲካ እምቧለሌ!  በገባህበት ትወጣለህ። በጉልበት ወደ ላይ ትወጣልህ በጉልበት ወደ ታች ትወርዳለህ። ዞሮ ዞሮ ወደ ቤት እንደሚባለው ዞሮ ዞሮ ወደ አቢዬት ያመጣሀል።

የጥቀሩ ቦልሸቪክ ገድል በለሆሳስ ይደመጣል። ምን ቀረ? አየሩ ሁሉ ዋዜማ ዋዜማ ይሸታል። የጣልነውን የአብዮት መፈክር መልሰን ልናነሳው ይሆን? “ሕዝባዊ መንግስት ይቋቋም፣ አቆርቋዥ ይውደም፣ ዋይ ዋይ ተለያየን፣…. መሬት ላራሹ፣ .

…”.ሰውረነ ከመዓቱ” -ተራኪው ራሱን አማተበ። ኮሚኒስት ሲያማትብ ምፅዓት ደርሷል ማለት ነው።

ልደት ኬክ ቤት ግንቡ ላይ “ፋሽስት” የሚል ፁሁፍ ተፅፏል። በቀይ ቀለም መሆኑ ደግሞ አሰጋኝ።

“ፋሽስት” ግን የመንግስታት የወል ስም ሆነች እንዴ። ደርግ ገዳይ ነው። ስለዚህ ቢጠራበት ስሙ ይመጥነዋል። ወያኔም ገዳይ ነች። ፋሽስት ብትባል ይገባታል። በኮሚሽን አጣራኸው አላጣራኸው በትዛዝ ዜጎች ተገድለዋል። ቆስለዋል። አካል ጉዳተኛ ሆነዋል። …..እንዴውም አሁንማ መንግስት ህዝቡ ላይ ኢንቲፋዳ የሚያካሂድ ነው የሚመስለው። ህዝብ ላይ መወርወር፣ ህዝብ ላይ ማሻጠር፣ ማሰርና መደብደብ…..መንግስታዊ አመጽ የሚያካሂዱ ይመስላል። ህዝብ መንግስት ላይ ቢያምፅ የወግ ነው። ይጠበቃል። ግን እንዴት መንግስት ህዝብ ላይ ያምፃል።

“አይ ስምንተኛው ሺ” አለ ተራኪው። በነጋ በጠባ ያማርራል። አይ ኢትዮጵያ ብር ሲጠፋ ሸቀጥ ይበዛል። ሆድ ሲሰፋ ምግብ ይጠፍል። ምግብ የሞላው በራዲዮ ብቻ ነው። ጥርሱ ውስጥ በመታኘክ ብዛት ልትጠፋ የደረሰች መፋቂያውን ሰክቶ አስፋልቱን ተሻገረ። እሷኑ  እያኘከ ይተክዛል። እየተከዘ ቀስ ብሎ ይራመዳል። ጉልበት ሲደክም ትካዜ ይበዛል።

 

በሌላው አንፃር ተቀናቃኙ ይሰለፋል። ተመሳሳይ አሰላለፍ፣ እንድ ዓይነት ግንኙነት ይዘረጋል። ጎፈርና ዘውድ ነገር ነው። አይመችም። አይደላም! የምትቃወመውን ከመሰልክ ቢቀርብህ ባትቃወም ይሻላል። ሌላ ጨቋኝ..ሌላ አስልቃሽ ጭስ ለመሆን መቸኮል አያስፋልግም። የሃሳብ ጥራት፣ የርዕዬተ ዓለም ጥራት፣ የአባላት ጥራት፣ የስነ ልቦና ዝግጁነት…..አዋጭ አደረጃጀት …እያለ ዝርዝሩ ሊሄድ ይችላል።

የገዢው  ካርቦን ኮፒ መሆን ግን አያዋጣም። ትርፋ የተራ መለዋወጥ  ብቻ ነው የሚሆነው።

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

ትስስር ይፍጠሩ

325,851FansLike
49,039FollowersFollow
13,194SubscribersSubscribe