“ በኮሮና ምክንያት ለሁለት ዓመታት ዝግ ሆኖ የቆየው እገዳ በመነሳቱ ደስ ብሎናል ብለዋል ›ብጹዕ አቡነ እንባቆም
የእስራኤል የአገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስቴር ከኢትዮጵያ ለሚመጡ ጎብኚዎች የቡድን ቪዛ እገዳ በቅርቡ መጣሉን ተከትሎ ቅሬታ የተሰማቸው የተለያዩ አካላት በተለይቶ በእየሩሳሌም የኢ/ኦ/ተ/ቤተክርስቲያን ገዳም አባቶች ባቀረቡት አቤቱታ መሠረት፣ ተጥሎ የነበረው እገዳ መነሳቱ ታውቋል፤
የኢትዮጵያ ኤምባሲ ከእስራኤል ጠቅላይ ሚ/ር ጽ/ቤት፣ ከእስራኤል የውጭ ጉዳይ ሚ/ር፣ ከሕዝብና ኢሚግሬሽን ጉዳይ የሥራ ኃላፊዎች እንዲሁም ጉዳዩ ከሚመለከታቸው ከተለያዩ አካላት ጋር በተደረገው ተደጋጋሚ ምክክር ውሳኔው የሁለቱን አገራት ወዳጅነት አንጻር ተገቢ አለመሆኑን ከመግባባት ላይ የተደረሰ ሲሆን በእስራኤል ከሕዝብና ኢሚግሬሽን ባለስልጣን ኃላፊዎች ጋር በተደረገው ውይይት ተጥሎ የነበረው የጉዞ ገደብ የተነሳ መሆኑን ተገልጾል።
የእስራኤል የፓርላማ አባል የሆኑት የተከበሩ አቶ ጋዲ ይባርከን “የእስራኤል አምላክ ፈቃድ ሆኖ ይህ መልካም ዜና ለኢትዮጵያዊያን በመድረሱ ደስታዬ ከፍ ያለ ነው ብለዋል”። በማያያዝም በቤተ-እስራኤላዊያን ስም ለክርስትና እምነት ተከታዮች እንኳን ለፋሲካ በዓል አደረሳችሁ፤ እንዲሁም ለእስልምና እምነት ተከታዮችም ረመዳም ከሪም በማለት መልካም ምኞታቸውን ገልጸዋል።
በእስራኤል የኢትዮጵያ ባለሙሉ ስልጣን አምባሳደር ረታ ዓለሙ ባስተላለፉት መልዕክት፣ በሂደቱ ከፍተኛ ሚና ለነበራቸው የመንግሥት አካላት እንዲሁም የእስራኤል መንግስት ያለውን ወዳጅነት በመመልከት ውሳኔውን እንዲለወጥ በመደረጉ ምስጋና አቅርበዋል። አክለውም ውሳኔው በእየሩሳሌም የሚገኙ ቅዱሳን መካናትን ለመሳለም እና ጸሎት ለማድረግ ለሚመጡ ሁሉ መልካም በመሆኑ የተሰማቸውን ልባዊ ደስታ ገልጸዋል።
በእየሩሳሌም የኢ/ኦ/ተ/ቤተክርስቲያን ሊቀ ጳጳስ ብጹዕ አቡነ እንባቆም በበኩላቸው “ምዕመናን ከመላው ዓለም ወደ እየሩሳሌም እየመጡ የሚያከብሩት በዓል በኮሮና ምክንያት ለሁለት ዓመታት ዝግ ሆኖ ከቆየ በኋላ አሁን በመከፈቱ ደስ ብሎናል፣ እገዳው ተነስቶ የትንሳዔ በዓልን ለማክበር ከሚመጡት ኢትዮጵያዊያን ጋር ለመገናኘት የእግዚአብሄር ፈቃድ በመሆኑ ደስታችን ታላቅ ነው ብለዋል”። በማስከተል የትንሳኤ በዓልን በእየሩሳሌም ማክበር ለኢትዮጵያዊያን ልዩ በመሆኑ፣ ይህ ላደረጉ ለእስራኤል መንግስት እና ጉዳዩ እንዲሳካ ለደከሙ ሁሉ ምስጋና እናቀርባለን ማለታቸውን በእስራኤል ከሚገኘው የኢትዮጵያ ኤምባሲ የተገኘው ዜና አመልክቷል፡፡

