የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር ምርቶቹን በፍራንኮ ቫሉታ እንዲያስገቡ ከተፈቀደላቸው ነጋዴዎች ጋር ውይይት ማድረጉን ሸገር ኤፍ ኤም 102.1 ዘግቧል።
ዘይት ፣ ስኳር ፤ ሩዝና የህፃናት ወተት በፍራንኮ ቫሉታ እንዲገቡ የተፈቀዱ ምርቶች መሆናቸው ይታወሳል።
ምርቶቹ በፍራንኮ ቫሉታ እንዲገቡ በመፈቀዱ ባለፉት አስር ወራት ብቻ መንግስት በታክስ መልክ ማግኘት የነበረበትን ከ10 ቢሊየን ብር በላይ አጥቷል ተብሏል።
ነገር ግን የምርቶቹ ዋጋ ከመቀነስ ይልቅ በየጊዜው ሲጨምር እንደሚታይ የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስትር ድኤታ አቶ ተሻለ በልሁ ተናግረዋል።
ጭማሪው እየታየ ያለዉ በአለም ላይ ዋጋቸው #ቀንሶ ባለበት ወቅት ጭምር ነው ብለዋል። ምርቶቹ ወደ ሀገር ውስጥ ከገቡ በኋላ ስርጭታቸውም ላይ ብዙ ግልፅነት እንደሌለ ተነግሯል።
እንደ ማሣያም ዘንድሮ በአስር ወራት ወደ ሀገር ውስጥ የገባው የምግብ ዘይት 97 ሚሊየን ሊትር እንደሆነ ተጠቅሷል። አምና በተመሣሣይ ጊዜ ወደ ሀገር ውስጥ የገባው ግን ከአንድ መቶ ሚሊየን ነበር ተብሏል።
እንዲያም ሆኖ በገበያው ላይ የምርት አቅርቦት ችግር የለም ተብሏል። ሁኔታው በስርጭቱ ላይ ችግር መኖሩን አመላካች እንደሆነ ተጠቅሷል። አስመጪዎች በበኩላቸው በብርና ዶላር መካከል ያለው ልዩነት ከጊዜ ወደ ጊዜ መስፋት የምርቶቹ ዋጋ እንዲጨምር ምክንያት ሆኗል ማለታቸውን ከሬድዮ ጣቢያው ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።

