በማይታመኑ ቁጥሮች የታጀበው የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ

በማይታመኑ ቁጥሮች የታጀበው

የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ

ኮከብ ግብ አስቆጣሪ ተጫዋች በቡድንህ ውስጥ ቢኖር ወይም ከየትኛውም ክለብ በላይ ግብ ብታመርት ሊጉን ለመምራት ዋስትና አይሆንህም፤ እንዲያውም ላለመውረድ ከሚታገሉት ክለቦች ተርታ ራስህን ልታገኘው ትችላለህ፡፡

ግብ የሚያስቆጥር አጥቂ ብታጣና በ15 ጨዋታ ከስድስት በላይ ግብ ማስቆጠር ቢሳንህ አበቃልኝ ብለህ አትሰጋም፡፡ በደረጃ ሰንጠረዡ ብዙ ግቦችን ካስቆጠረው ክለብ በላይ የምትቀመጥበት እድል ሰፊ ነው፡፡

ካሸነፍከው ጨዋታ ይልቅ አቻ የተለያየህበት ቢበዛ ከዋንጫ ፉክክሩ አትርቅም፡፡ ምክንያቱም ይህ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ነው፡፡

እስካሁን በሊጉ 120 ጨዋታዎች ተደርገው 227 ኳሶች መረብ ላይ አርፈዋል፡፡ በእያንዳንዱ ጨዋታ በአማካይ 1.89 ግብ ይቆጠር ነበር እንደ ማለት ነው፡፡

ከ120 ጨዋታዎች መካከል 24ቱ ምንም ግብ ሳይስተናገድባቸው የተጠናቀቁ ናቸው፡፡ በአንድ አቻ ውጤት የተደመደሙት ደግሞ ቁጥራቸው በእጅጉ የላቀ ነው፡፡

እነዚህን ቁጥሮች እማኝ በማድረግ ሊጉ ብዙ ግቦች ሳይስተናገዱበት አንደኛውን ዙር ደምድሟል ማለት እንችላለን፡፡

መቐለ ወደዋንጫው?

የ2011 ዓ.ም የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ የመጀመሪያ ዙር መርሃ ግብር እንደአምና ካቻምናው ዘንድሮም በብዙ ተስተካካይ ጨዋታዎች ታጅቦ ተደምድሟል፡፡

ባለፈው የውድድር ዓመት ጅማ አባጅፋርን እየመሩ ለሻምፒዮንነት ያበቁት የቀድሞው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ተጫዋች ገብረመድህን ሃይሌ መቐለ 70 እንደርታን እያሰለጠኑ ወደዋንጫው ጉዞ ጀምረዋል፡፡

የመጀመሪያ ሳምንት ጨዋታውን በትግራይ ስታድዬም ከደደቢት ጋር አድርጎ 2ለ0 በማሸነፍ አጀማመሩን ያሳመረው መቐለ ሰባ እንደርታ ዙሩን የጨረሰውም በድል ነው፡፡ የዓምናው ሻምፒዮን ጅማ አባጅፋርን በሜዳው ጋብዞ 2ለ1 በመርታት፡፡ አሰልጣኝ ገብረመድህን ሃይሌ የቀድሞ ክለባቸውን የገጠሙበት ይህ ወሳኝ ጨዋታ መቐለ ሰባ እንደርታ የሊጉን መሪነት በአምስት ነጥቦች ልዩነት አስፍቶ ወደሁለተኛው ዙር እንዲቀላቀል ያደረገ ነው፡፡

መቀሌ ካደረጋቸው 15 ጨዋታዎች 11ዱን አሸንፏል፡፡ በሁለቱ አቻ ሲለያይ በሁለቱ ደግሞ ተሸንፏል፡፡ ከአምናው በተሻለ ሁኔታ ግቦችን እያስቆጠረ የሚገኘውና በአማኑኤል ገብረሚካኤል የሚመራው የክለቡ አጥቂ መስመር 23 ጊዜ ኳስና መረብን አገናኝቷል፡፡ የአምናውን ጥንካሬ ዘንድሮም የደገመው ተከላካይ ክፍሉ ደግሞ መረቡን ከ10 ጊዜ በላይ አላስደፈረም፡፡ እነዚህ ሁለት ነገሮች ለቡድኑ ውጤታማነት ትልቁን ድርሻ ይወስዳሉ፡፡

በሊጉ ባልተለመደ ሁኔታ መቀሌ ዘጠኝ ተከታታይ ጨዋታዎችን ማሸነፍ የቻለ ሲሆን በ11 ተከታታይ ጨዋታዎች ደግሞ አልተሸነፈም፡፡ ይህን ውጤት አስጠብቆ በሁለተኛውም ዙር ከቀጠለ በታሪኩ ለመጀመሪያ ጊዜ የሊጉን ዋንጫ ያነሳል፡፡ ከሀዋሳ ከተማ እና ጅማ አባጅፋር በመቀጠል ሻምፒዮን የሆነ ሶስተኛው የክልል ክለብ ይሆናል፡፡

የባህርዳር ከተማ ጥንካሬ

ከከፍተኛ ሊግ ወደ ፕሪምየር ሊጉ ካደጉት ሶስት ክለቦች መካከል ሁለቱ ወራጅ ቀጠናን የሙጥኝ ብለው የመጀመሪያውን ዙር አጠናቀዋል፡፡

ስሑል ሽረ ከአንድ በላይ ጨዋታ ማሸነፍ አልቻለም፡፡ በስድስቱ ደግሞ ሽንፈት ገጥሞታል፡፡ ስምንት ጊዜ አቻ ተለያይቷል፡፡

ከስድስት በላይ ግቦችን ማስቆጠር ያልቻለውና በአንጻሩ መረቡን 21 ጊዜ ያስደፈረው ስሁል ሽረ በ11 ነጥቦች 15ኛ ደረጃ ላይ ይገኛል፡፡

ከዘጠኝ ዓመታት በኋላ ዳግም ወደሊጉ የተመለሰውና በአንጋፋ ተጫዋቾች ተሞልቶ ውድድሩን የጀመረው ደቡብ ፖሊስ ካደረጋቸው 15 ጨዋታዎች መካከል በድል የተወጣው ሶስቱን ብቻ ነው፡፡ የአምናው ሻምፒዮን ጅማ አባጅፋርን 6ለ1 የረታበት ያልተጠበቀ ውጤት የስፖርት አፍቃሪውን ያነጋገረ ነበር፡፡ ይሁን እንጅ ደቡብ ፖሊስ ብዙ ጨዋታዎችን በመሸነፍ ከደደቢት ቀጥሎ ሁለተኛው ክለብ ነው፡፡ 10 ጊዜ የሽንፈትን ጽዋ ተጎንጭቷል፡፡ 2 ጊዜ ደግሞ አቻ ተለያይቷል፡፡ ደረጃው 14ኛ ነው፡፡

ከከፍተኛ ሊጉ ካደጉት ክለቦች መካከል የተሻለ ተፎካካሪ መሆን የቻለው ባህርዳር ከተማ ብቻ ነው፡፡ ቡድኑ የአጥቂ ችግር ቢኖርበትም በወንድሜነህ ደረጀ የሚመራው የተከላካይ መስመር ግን በቀላሉ ግብ የሚቆጠርበት አልነበረም፡፡

በሊጉ ትንሽ ግብ ካስተናገዱት ሶስት ክለቦች መካከል አንዱ ነው፡፡ የተቆጠረበት ስምንት ግብ ብቻ ነው፡፡ ኢትዮጵያ ቡና እና ቅዱስ ጊዮርጊስን በተመሳሳይ 1ለ0 ውጤት ማሸነፍ የቻለው ባህርዳር ከነማ በደረጃ ሰንጠረዡ ሰባተኛ ላይ ይገኛል፡፡

ኢትዮጵያ ቡና

ባልተለመደ መልኩ ለአሰልጣኝ ዲዲዬ ጎሜዝ ካላቸው የአንድ ዓመት ቀሪ ውል በተጨማሪ ሁለት አመታትን እንዲቆዩ ወስኖ በየቦታው ወሳኝ የሚባሉ ተጫዋቾችን አስፈርሞ፣ ተስፋ ያላቸው ታዳጊዎችን ወደዋናው ቡድን አሳድጎ በጥሩ መንፈስ ዓመቱን የጀመረው ኢትዮጵያ ቡና የመጀመሪያው ዙር ሲጠናቀቅ ግን በነበረበት ቦታ ላይ አልተገኘም፡፡ ለሳምንታት ሲመራው ከነበረው የደረጃ ሰንጠረዥ ተንሸራቶ ስምንተኛ ላይ ተቀምጧል፡፡ ተቃውሞ የበረከተባቸውን ፈረንሳያዊ አሰልጣኝ አሰናብቷል፡፡ ላለፉት አርባ አመታት ክለቡን በአመራርነት ያገለገሉት መቶ አለቃ ፍቃደ ማሞም ከአመራርነት መልቀቃቸውን ያሳወቁት የመጀመሪያው ዙር የሊጉ መርሃ ግብር ከመጠናቀቁ በፊት ነበር፡፡

ቡድኑ በተለይ በመጨረሻዎቹ አራት ተከታታይ ጨዋታዎች ሽንፈትን ማስተናገዱ ከሊጉ መሪነት ተነስቶ የሰንጠረዡ ወገብ ላይ እንዲቀመጥ አድርጎታል፡፡

ቅዱስ ጊዮርጊስ

የሊጉን ዋንጫ 14 ጊዜ በማንሳት ባለታሪክ የሆነው ቅዱስ ጊዮርጊስ በዚህ የውድድር ዓመት አጀማመሩ ጥሩ ባይሆንም በተለይ አጥቂው ሳልሃዲን ሰዒድ ወደሜዳ ከተመለሰ በኋላ መነቃቃትን አሳይቷል፡፡ በተከታታይ ካደረጋቸው 12 ጨዋታዎች መካከል ሽንፈትን ያስተናገደው አንዴ ብቻ ነው፡፡ ስድስቱን በአሸናፊነት ሲያጠናቅቅ በአምስቱ ደግሞ አቻ ተለያይቷል፡፡ 26 ነጥቦችን የሰበሰቡት ፈረሰኞቹ አሁን በደረጃ ሰንጠረዡ ሶስተኛ ላይ ናቸው፡፡

እንደማጠቃለያ

በመጨረሻ የተወሰኑ አሃዞችን እንመልከት፡፡ በሊጉ ብዙ የተሸነፈው ደደቢት ነው፡፡ 13 ጊዜ እጁን ሰጥቷል፡፡ ጥቂት ጨዋታ የተሸነፈው ደግሞ በሊጉ ሁለተኛ ደረጃ ላይ የሚገኘውና ብዙ ግቦችን በማስቆጠር ቀዳሚ የሆነው ሲዳማ ቡና ሲሆን የተረታውም አንዴ ብቻ ነው፡፡ መቐለ ሰባ እንደርታ ብዙ በማሸነፍ ቀዳሚው ክለብ ነው፡፡ በ11 ጨዋታዎች ሶስት ነጥቦችን እየያዘ ወጥቷል፡፡

ሰባት የሊጉ ክለቦች ከአሰልጣኞቻቸው ጋር ተለያይተዋል፡፡ ሁሉም በደረጃ ሰንጠረዡ ከስምንተኛ በታች የተቀመጡ ክለቦች ናቸው፡፡

በሊጉ ብዙ ግቦች የተቆጠሩበትን ክለብ ገምቱ፡፡ ምናልባት ወራጅ ቀጠና ላይ ከሚገኙት ክለቦች አንዱ ሊሆን እንደሚችል ታስባላችሁ፡፡ ግን አይደለም፡፡ 27 ጊዜ መረቡን ያስደፈረው የተከላካይ ክፍሉ እጅግ ተዳክሞ የነበረው መከላከያ ነው፡፡ ይሁን እንጅ መከላከያ 11ኛ ደረጃ ላይ ነው፡፡ ምክንያቱም ክለቡ ብዙ ግቦችን በማስቆጠርም ይታወቃል፡፡ 19 ጊዜ ኳስና መረብን አገናኝቷል፡፡ 11ዱ በአንድ ተጫዋች፣ በምንይሉ ወንድሙ አማካኝነት የተቆጠሩ ናቸው፡፡

ምንይሉ ኮከብ ግብ አስቆጣሪ ነው፤ ክለቡ መከላከያ ግን 11ኛ ደረጃ ላይ ይገኛል፡፡ ይህ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ አንዱ ገጽታ ነው፡፡

 

 

 

 

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

ትስስር ይፍጠሩ

325,851FansLike
49,039FollowersFollow
13,194SubscribersSubscribe