በደቡባዊው የአፍሪካ ክፍል የምትገኘውና 17 ሚሊየን ሕዝብ የሚኖርባት ዚምባቡዌ ሰሞኑን ጤናዋ ተናግቷል፡፡ በነዳጅ እና በዳቦ ዋጋ ላይ የተደረገ ጭማሪ ባስነሳው ተቃውሞ ዜጎቿ ለሞትና ለአካል ጉዳት ተዳርገዋል፡፡ ለተቃውሞ አደባባይ የወጡት ዜጎች የመኪና ጎማዎችን ያቃጠሉና መንገዶችን የዘጉ ሲሆን በዋና ከተማዋ ሐራሬና በቡልዋሎ ከተማ አብዛኞቹ የሸቀጣሸቀጥ መደብሮችና ትምህርት ቤቶች ተዘግተዋል፡፡ አጋጣሚዎችን ተጠቅመው የተፈፀሙ ዘረፋዎችን ለመከላከል ፖሊስ አስለቃሽ ጭስ መጠቀሙን የዓይን እማኞች ተናግረዋል፡፡ የሀገሪቱ መንግሥት ዋነኛ ተቃዋሚ የሆነው ‹ንቅናቄ ለዴሞክራሲያዊ ለውጥ› የተሠኘ ፖለቲካ ፓርቲ ዋና ጽ/ቤት በእሳት መቃጠሉ ደግሞ ሌላው የተቃውሞ አመፁ ገጽታ ነው፡፡ አመፁ ከአቅሙ በላይ የሆነበት መንግሥት ድረ ገጾችንና የማኅበራዊ መገናኛዎችን አገልግሎት ማቋረጥ መርጧል፡፡
በስዊዘርላንድ በሚካሔደው የዓለም ኢኮኖሚ ፎረም ላይ ለመሳተፍ ወደ ሀገሪቱ ተጉዘው የነበሩት ፕሬዚዳንት ኤመርሰን ምናንጋግዋ መቋጫ ባጣው ብጥብጥ ምክንያት ወደ ሀገራቸው ለመመለስ የተገደዱ ሲሆን ሳምንታትን ካስቆጠረው የሕዝብ ተቃውሞ በኋላ ለመጀመርያ ጊዜ በትዊተር ገጻቸው ባስተላለፉት መልእክትም ‹‹የወሰንኩት የነዳጅ ዋጋ ጭማሪ በሕዝቡ ዘንድ እንደማይወደድ አውቅ ነበር፡፡ ነገር ግን ትክክለኛውን ነገር ነው ያደረግኩት፡፡ የተከተለው ነገር ግን እጅግ አሳዛኝ ነው፡፡ ማንኛውም ሰው የመቃወም መብት አለው፡፡ ይህ ግን የሰላማዊ ተቃውሞ መገለጫ አይደለም፡፡ ንብረት ማውደምና ፖሊስ ጣቢያዎችን መዝረፍ፣ መሳሪያዎችንና የፖሊስ የደንብ ልብሶችን መስረቅ የዚምባቡዌያውያን መገለጫ አይደለም›› ብለዋል፡፡
እስከ ባለፈው ረቡዕ ድረስ ከተቃውሞው ጋር በተያያዘ ከዐሥራ ሁለት በላይ ሰዎች መሞታቸው ሲገለጽ ለጥይት ጉዳት የተዳረጉ 78 ሰዎች ደግሞ ሕክምና እየተከታተሉ መኾኑ ተነግሯል፡፡ 700 ያህል ሰዎች ለእስር ተዳርገዋል፡፡
በስዊዘርላንዷ ዳቮስ ከተማ በሚደረገው የኢኮኖሚ ፎረም ላይ ለመሳተፍ የተገኙት የዚምባቡዌ ገንዘብ ሚኒስትር ምቱሊን ኩቤ ከሲኤንኤን ጣቢያ ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ በሀገራቸው የተነሳው ተቃውሞ በነዳጅ ዋጋ ጭማሪ ተሳበበ እንጂ ‹አስቀድሞ የታለመ እንደነበር እናውቃለን› ብለዋል፡፡ የዚምባቡዌ መንግሥት የሰሞኑ ተቃውሞ መነሻ በተቃዋሚ ፖለቲከኞች የተቀሰቀሰና ፖለቲካዊ ምክንያት ያለው ነው ብሏል፡፡ መንግሥት በነዳጅ ዋጋ ላይ የ150 በመቶ ጭማሪ ሲያደርግ ዋነኛ ዓላማው የነበረው በሀገሪቱ የተፈጠረውን የነዳጅ እጥረት መቅረፍ ነበረ፡፡ በሕገ ወጥ መንገድ ይቸበቸባል የሚባለውን ነዳጅ ለመቆጣጠርም ያለመ ነበር፡፡ በተደጋጋሚ የኢኮኖሚ ጫና ውስጥ የሚገኙት ዚምባቡዌያውያን ግን ወደሥራ የሚሔዱበትን የአውቶቡስ ክፍያ እንኳን ለመክፈል በመቸገራቸው ለተቃውሞ አደባባይ መውጣት መረጡ፡፡ አሁን ባለው ሁኔታ ዚምባቡዌ በውድ ዋጋ ነዳጅ የሚሸጥባት ቁጥር አንድ ሀገር መሆኗን የዓለም ነዳጅ ዋጋን የሚዘግብ ግሎባል ፔትሮል ፕራይስስ የተባለ ድረገጽ አስነብቧል፡፡
ኢኮኖሚ
ዚምባቡዌ በዐሥርት ዓመታት ውስጥ ታይቶ የማይታወቅ አስከፊ የኢኮኖሚ መዋዠቅ ውስጥ ገብታለች፡፡ ለሠራተኞች የሚከፈለው አማካይ የደሞዝ መጠን 340 የአሜሪካ ዶላር ሲሆን የሥራ – አጥነት መጠኑ ዘጠና በመቶ መድረሱ እጅግ አሳሳቢ ሆኗል፡፡ በርካታ ሰዎች የሚሠሩት መደበኛ ያልሆኑ ሥራዎችን ነው፡፡ ተቃውሞውን ተከትሎ ታዲያ የሀገሪቱ መንግሥት፤ ለመንግሥት ሠራተኞች የደሞዝ ጭማሪ ፈቅዷል፡፡ ከአምስት እስከ ሃያ ሦስት በመቶ የሚደርሰው ጭማሪ ለቀጣዮቹ ሦስት ወራት እንደሚቆይ ተነግሯል፡፡ ‹ቦላርስ› የሚባለው የሀገሪቱ ገንዘብ ዋጋው እጅግ በመውረዱ ዚምባቡዌ የምታካሒደው የውጪ ግብይት ላይ የፈጠረው ተፅዕኖም ቀላል አይደለም፡፡ ፕሬዚዳንት ኤመርሰን ምናንጋግዋም ችግሩን በመጠኑ ለማቃለል የሚረዳቸውን የገንዘብ ብድር ለመጠየቅ ወደ ሩሲያ ተጉዘው ነበር፡፡ ቤላሩስ፣ አዘርባጃንና ካዛኪስታንንም መጎብኘታቸው ተነግሯል፡፡
የመንግሥት ምላሽ
በከፍተኛ ጫና ውስጥ የሚገኘው የምናንጋግዋ መንግሥት አመፁን ለመቆጣጠር ማንኛውንም መንገድ መከተል የመረጠ ሲሆን ከፖሊሶች ጋር በሚደረጉ ግጭቶች ለጉዳትና ለሞት የተዳረጉ ሰዎች ቁጥርም ከዕለት ዕለት እየጨመረ መጥቷል፡፡ መንግሥት ባለፈው ዓመት በምርጫ የተሸነፈው ‹ንቅናቄ ለዴሞክራሲያዊ ለውጥ› የተባለውና በኔልሰን ቻሚሳ የሚመራው ተቃዋሚ ፓርቲ ለአመፁ መስፋፋት የራሱን ሚና ተጫውቷል የሚል ክስ አቅርቧል፡፡ የተወሰኑ የፓርቲውን አባላትና በተቃውሞው እጁ አለበት ያለውን የንግድ ማኅበራት መሪ ጃፌት ሞዮም አስሯል፡፡
የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት በበኩሉ የዚምባቡዌ መንግሥት ተመጣጣኝ ያልሆነ ኃይል ከመጠቀም እንዲቆጠብ ነው ያስጠነቀቀው፡፡ ፕሬዚዳንቱም በትዊተር ገጻቸው ባስተላለፉት መልእክት ‹ያልተገባ ድርጊት የፈፀሙ የፖሊስ ኃይሎች ላይ ምርመራ እናካሒዳለን› ብለዋል፡፡ ‹ተቀባይነት የሌለውና አዲሲቷን ዚምባቡዌ መክዳት ነው› ሲሉም ነው ድርጊቱን የኮነኑት፡፡
ምናንጋግዋ ይሳካላቸው ይኾን?
የ76 ዓመቱ ኤመርሰን ምናንጋግዋ ከአንድ ዓመት በፊት የቀድሞው ፕሬዚዳንት ሮበርት ሙጋቤ ከ37 ዓመት በኋላ በወታደራዊው ኃይል ከስልጣን እንዲወርዱ ተደርጎ ወደስልጣን ከመጡ በኋላ የሀገሪቱን የወደቀ ኢኮኖሚ ለማሻሻልና የፖለቲካ ምኅዳሩን ለማስፋት እንደሚጥሩ ቃል ገብተው የነበረ ቢሆንም በሀገሪቱ የሚታየው ለውጥ ግን ዚምባቡዌያውያንን የሚያረካ አልሆነም፡፡
የሙጋቤ ወዳጅ እንደነበሩ የሚነገርላቸው ምናንጋግዋ ቃላቸውን ጠብቀው ከሙጋቤ ዘመናት የተሻለች ሀገር ይፈጥራሉ ተብሎ ዕምነት ቢጣልባቸውም በፖለቲካውም ሆነ በኢኮኖሚው ዘርፎች የሙጋቤን ስህተት እየደገሙ ነው የሚል ትችት ከተቃዋሚ ወገን ተሠንዝሮባቸዋል፡፡ ፕሬዚዳንት ምናንጋግዋ ‹ኢኮኖሚዋን አረጋግቼ ለምገነባት አዲሲቷ ዚምባቡዌ ጊዜ ስጡኝ፤ ብሔራዊ መግባባትም ይፈጠር› የሚል ጥሪ ቢያቀርቡም ዜጎቻቸው ግን ‹‹ከሙጋቤ የተሻልክ አልሆንክምና በቃኸን›› እያሏቸው ይመስላል፡፡ የሕዝባዊ ተቃውሞው ‹አዞው› በሚል ቅፅል ስም የሚታወቁትን የ76 ዓመት ሰው ከስልጣን የማውረድ አቅም ይኖረው ይኾን ወይስ ሕይወት ወደ ቀደመ መልኳ ትመለሳለች? . . . መልሱን መጪው ጊዜ ያሳየናል፡፡

