በመላው ፈረንሳይ በተቀሰቀሰው የተማሪዎች ተቃውሞ ጋር በተያያዘ ታዳጊዎችን ጨምሮ ከ400 በላይ ሰዎች በቁጥጥር ሥር መዋላቸውን የውስጥ ጉዳይ ሚኒስትሯ ተናገሩ።
በፓሪስ የተጀመረው እና ታዳጊዎች ለቀናት ትምህርት የዘጉበት የተቃውሞ ሰልፍ የተነሳው የክፍለ ጊዜዎች መጨናነቅ እና የመምህራን እጥረትን ጨምሮ ከተነሱ ጉዳዮች ጋር በተያያዘ ነው።
ማክሰኞ ዕለት በተካሄደው የተቃውሞ ሰልፍም ቢያንስ 10 መምህራን፣ በርካታ ተማሪዎች እንዲሁም 48 ሕግ አስፈፃሚ አካላት ላይ ጉዳት መድረሱ ተገልጿል። እንደ ትምህርት ሚኒስቴር ከሆነ በተቃውሞ ሰልፉ ቢያንስ 400 የሚሆኑ ትምህርት ቤቶች ተስተጓጉለዋል።
ቪዲዮ እና ምስሎችም በተቃዋሚዎች የወደሙ የአውቶብስ መቆሚያዎች እና በእሳት የተያያዙ የቆሻሻ ቅርጫቶችን አሳይተዋል።
ተማሪዎች በዱላ እና አስለቃሽ ጭስ በመተኮስ ምላሽ በሰጡት የጸጥታ ኃይሎች ላይ የተለያዩ ቁሳቁሶችን መወርወራቸውንም የአገሪቱ መገናኛ ብዙኃን ዘግበዋል።
የትምህርት ሚኒስትሩ ኤዶርድ ጂፍሬይ፣ ተማሪዎች ተቃውሞ የማካሄድ መብት እንዳላቸው ገልጸው፤ ነገር ግን የሚፈፅሙትን ጥቃት ” ስህተት” ሲሉ አውግዘዋል።
የውስጥ ጉዳይ ሚኒስትሩ ላውረንት ኑንዝ በበኩላቸው ከተቃውሞው ጋር በተያያዘ 440 ሰዎች በቁጥጥር ሥር መዋላቸውን ጠቅሰው፤ ከእነዚህ መካከል ሁለት ሦስተኛ የሚሆኑት እስር ላይ መሆናቸው እንደተነገራቸው ገልጸዋል።
የተማሪዎቹ ተወካይ እና የማኅበሩ ፕሬዚደንት የሆነው ሪያድ ራኒ ለኤኤፍፒ የዜና ወኪል “በአፈና” እና “ፖሊስ ያልተመጣጠነ ኃይል ተጠቅሟል” ሲል መንግሥትን ከስሷል።
ፖሊስ የሰጠው ምላሽ በበርካታ የአገሪቱ ፖለቲከኞችም የተተቸ ሲሆን የውስጥ ጉዳይ ሚኒስትሩ ግን ክሱን አስተባብለዋል።//
በፈረንሳይ ከተባባሰው የተማሪዎች ተቃውሞ ጋር በተያያዘ ከ400 በላይ ሰዎች በቁጥጥር ሥር ዋሉ

