ቴዲ አፍሮ ከአቦጊዳ እስከ ኢቶሪካ

 “ማናቸውም ኢትዮጵያዊ ትክክል መብት እንዲኖረውና የተወደደ ሕዝባችን ሁሉ የአንድ ትልቅ ቤተሰብ ተወላጆች ሆነው በወንድማማችነት እኩል እንዲኖሩ ዘወትር የተከተልነው ዓላማ ነው።” ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ

ይህ ንግግር የተወሰደው ተወዳጁ ድምፃዊ ቴዲ አፍሮ ስድስተኛ አልበሙን ሰሞኑን ለአድማጭ ሲያቀርብ ከተጫወታቸው ዘፈኖች መሀከል አንዱ በሆነው ጀምበር ዜማ ላይ የገባ የቀዳማዊ አጼ ኃይለስላሴ ድምፅ ነው፡፡

የአፍሪካ አባት ለሚባሉት አጼ ኃይለስላሴ ቴዲ ተገቢውን ክብር ሲሰጥ ይህ የመጀመሪያው አይደለም፡፡ ቀደም ባለው ‹አቦጊዳ› አልበሙ ጀምሮ  ‹ ግርማዊነትዎ› የሚል የክብር ካባ ያጎናፀፈበትን ዜማ አቀንቅኗል፡፡ ቴዲ አፍሮ ከላይ የቀረበውን የንጉሠ ነገሥት አጼ ኃይለ ሥላሴን መልዕክት ጀንበር ላይ ያለ ምክንያት እንዳላስገባው መገመት ቀላል ነው፡፡ ነጉሰ ነገስቱ በጓዳ ሳይሆን በዓለም አደባባይ ቀርበው ሁሉም ሰው እኩል መብት እንዳለው እና የአንድ ትልቅ ቤተሰብ ተወላጅ እንደሆነ ከመመስከራቸውም በላይ አቅማቸው በፈቀደው ልክም ቃላቸውን ተግባራዊ ለማድረግ ጥረዋል። ግርማዊነታቸው ያሉት በእኩልነት እና በወንድማማችነት እንኑር ነው። ቴዲም ሌላ ያለው ነገር የለም።

ቴዲ አፍሮ በኦፊሻል የፌስ ቡክ ገፁ ላይ ከሳምንት በፊት ‹አክብሮት ሰላምታዬን በማስቀደም ቀጣዩ ‘ኢቶሪካ’ የተሰኘው አዲስ አልበም የፊታችን ሐሙስ ሚያዝያ 8/2018 በTeddy Afro Official Youtube ድህረገፅ (www.youtube.com/TeddyAfroOfficial) ከቀኑ በ8 ሰዓት ወደ እናንተ እንደሚደርስ በአክብሮት እገልጻለሁ። ቴዎድሮስ ካሳሁን (ቴዲ አፍሮ)> ብሎ ነበር፡፡

ይህንኑ ተከትሎ ኢቶሪካ በሁለት ሳምንት በኦፊሴላዊው የቴዲ አፍሮ ዩትዩብ መተግበሪያ ብቻ ከ120 ሚሊዮን በላይ ዕይታ በማግኘት በመላው አፍሪካ የመጀመሪያ እና ታሪካዊ አልበም በመሆን ክብረ ወሰን ሰብሯል፡፡

ይህ ስታስቲክስ በስፖቲፋይ፣ በአይቲዩን፣ ሕገ ወጥ በሆነ መልኩ በራሳቸው ፕላትፎርሞች በመጫን፣ በፌስቡክ ፣ በቲክቶክ፣ በኢንስታግራም፣ በኤክስ( ትዊተር) ወዘተ የተሰራጩትን የማያካትት ሲሆን በየዕለቱም ከአንድ ሚሊዮን በላይ አድማጮች ዘፈኖቹን እየሰሙ ነው፡፡

ቴዲ አፍሮ ሁሌም አልበም ሊያወጣ ነው ሲባል ሽር ጉዱ ይጧጧፋል፡፡ በአንድ በኩል የቴዲ አድናቂዎች በጉጉት እየጠበቁት እንደሆነ ሲናገሩ ያለፈው ስርዓት ናፋቂ አድርገው የሚስሉት ተቺዎቹ ደግሞ የተቃውሞ ድማፃቸውን ያሰማሉ፡፡የዘንድሮው አልበሙ ልዩ የሚያደርገው ግን ዓለማዊ ሰዎች ብቻ ሳይሆኑ ‹ሃይማኖተኛ ነን› የሚሉ ሰባኪያን ሳይቀሩ በዘፈኑ ላይ ዘመቻ መጀመራቸው ነው፡፡

አንዳንዶች ሙዚቃው እንዳይታይ  ፈጣሪያቸውን ጭምር  ሲማፀኑ ሌሎች  መንግስትን  ጉልበት አንዲጠቀም ሲወተውቱ ተሰምተዋል፡፡ ቴዲ ግን እምነት እና እውነት ይዟልና እጅ አልሰጠም፤አልተሸነፈም። ቴዲ የበለጠ ለፍቅር፣ ሰላምና እውነት የቆመ መሆኑን አሻራውን አኑሯል።

የ”ኢቶሪካ” ጥሪ እና የኢትዮጵያዊነት ዋጋ!

የቴዲ አፍሮ አዲሱ አልበም “ኢቶሪካ” ለአድማጭ ከደረሰ ቅናት  ቢቆጠርም፣ ስራው ከሙዚቃዊ ይዘቱ በላይ የፈጠረው ማህበራዊ ንቅናቄ ግን አሁንም እንደቀጠለ ነው። ይህ አልበም በዜማና በግጥም የታጀበ የጥበብ ስራ ብቻ ሳይሆን፣ እንደ ሀገር የቆምንበትን የታሪክ መስቀለኛ መንገድ የፈተሸ እና የቁስላችንን ስር የነካ የታሪክ ማህደር ሆኖ ብቅ ብሏል። ሆኖም ግን፣ ይህ ጥበባዊ ስራ ከተለቀቀ በኋላ እየተከሰቱ ያሉት ሁኔታዎች፣ በተለይም በአርቲስቱ የቅርብ ሰዎች ላይ እየተካሄደ ያለው ማዋከብ እና እስር እንዲሁም በንብረቶቹ (ስቱዲዮ) ላይ የደረሰው ጥቃት በአርቲስቱ የመናገር እና የመፍጠር ሰብአዊ መብት ላይ የተቃጣ ግልጽ ጥቃት መሆኑን ያሳያሉ ይላሉ አድናቂዎቹ። ‹‹ቴዲ በሙዚቃው የመንግስትን አንዳንድ ፖለቲካዊ አካሄዶች በመተቸቱ ብቻ የሚደርስበት ይህ እንግልት፣ በሀገራችን ያለውን የሃሳብ ነፃነት አደጋ ላይ የሚጥል ነው።ቴዲ አፍሮ ግን አስቀድሞ እንደነገረን፣ ስለ ኢትዮጵያ የሚመጣውን ማንኛውንም መስዋዕትነት ለመቀበል ዝግጁ ነው። አድናቂዎቹ ዋናውን የቴዲ መልእክት መዘንጋትም የለብንም።›› ይላል አድናቂው አርአያ ጌታቸው በፌስ ቡክ ገፁ ላይ፡፡

ቴዲ ከጀርባው የቆመ ምንም አይነት የፖለቲካ ቡድን እንደሌለው በተደጋጋሚ ተናግሯል፣ በደጋፊዎቹ ፍቅርና በሀገር ፍቅር ብቻ የሚመራ አርቲስት ነው። ራሱንም ለዚህ ሁሉ ወከባና ስጋት አሳልፎ የሰጠው ለግል ጥቅሙ ሳይሆን፣ በኢትዮጵያዊነት አስተሳሰብ ላይ የተቃጣውን ስልታዊ ጥቃት፣ መገፋትና መገለል ዝም ብሎ ማየት ስላልቻለ ነው። የቴዲ ኢትዮጵያ የሁላችንም ናት፤ እሱን የምንወደውም ድምጹ ስላማረን ብቻ ሳይሆን፣ ለሀገሩ ያለው ጽኑ ስሜት ከእኛ ውስጣዊ ስሜት ጋር ስለሚስተጋባ ነው ባዮች ናቸው፡፡

እንደሚታወቀው ኢትዮጵያዊነት የትውልድ አደራ እንጂ በዘመን ለዋጮች የሚቀየር ካባ አይደለም። አርቲስቱ ጥሪ ያቀረበው በጎሳ ላይ የተመሰረተው የፖለቲካ ስርዓት በኢትዮጵያዊነት ላይ እያሳደረ ያለውን ጭቆና በጋራ እንድንከላከል እና የጋራ ማንነታችን እንዳይዳከም ነው። ቴዲ ሁሌም እንደሚሰብከው መፍትሄው ጥላቻ ሳይሆን ፍቅር፣ በቀል ሳይሆን ይቅርታ፣ መከፋፈል ሳይሆን ህብረት ነው። የቴዲን መልእክት በማጋራትና የሀገራችንን ሰላም በመመኘት የኢትዮጵያዊነትን አደራ እንጠብቅ።›› ይላል አድናቂው አርአያ፡፡

የኢትዮጵያን የሙዚቃ ሰንጠረዥ መሪ

በኢትዮጵያ የሙዚቃ ታሪክ ታይቶ በማይታወቅ መልኩ ድምፃዊ ቴዎድሮስ ካሳሁን (ቴዲ አፍሮ) አዲሱን አልበሙን ተከትሎ የሳምንቱን የሙዚቃ ሰንጠረዥ በበላይነት መርቷል። ከሚያዝያ 9 እስከ ሚያዝያ 16 ቀን 2018 ዓ.ም ባለው ጊዜ ውስጥ ብቻ በ”የኔ ቫይብ” ይፋዊ የሙዚቃ ደረጃ መሠረት፣ በሳምንቱ ከፍተኛ እይታ ካገኙ 10 ሙዚቃዎች ውስጥ ዘጠኙን የቴዲ አፍሮ የ”ኢትዮሪካ” አልበም ስራዎች ተጠቃሽ ነው።

በተለይም “ዳስ ጣል (አንሳው)” የተሰኘው ስራው በአንድ ሳምንት ውስጥ ብቻ ከ11 ሚሊዮን በላይ አዳዲስ ተመልካቾችን በማግኘት ቀዳሚነቱን የያዘ ሲሆን፣ አጠቃላይ የእይታ መጠኑንም ወደ 21.6 ሚሊዮን አሳድጓል። ይህ አሃዝ በሀገሪቱ የዲጂታል የሙዚቃ ስርጭት ታሪክ ውስጥ አዲስ ክብረ ወሰን መሆኑ ተመልክቷል።

በቴዲ አፍሮ ስራዎች በተጥለቀለቀው በዚህ ሰንጠረዥ ውስጥ ብቸኛው ተፎካካሪ ሆነው የቀረቡት ገላና ጋሮምሳ እና ዮሳን ጌታሁን በጋራ የተጫወቱት “ጋልሜ ሴና” የተሰኘው አዲስ የኦሮምኛ ሙዚቃ ሲሆን፣ በሳምንቱ 2.4 ሚሊዮን እይታዎችን በማግኘት 10ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል።

የሙዚቃ ባለሙያዎች እንደሚሉት፣ የቴዲ አፍሮ ስራዎች እንዲህ ባለው ፍጥነት በሚሊዮኖች መታየታቸው የአርቲስቱን የቆየ ተወዳጅነት ከማሳየቱም በላይ፣ የኢትዮጵያ የዩቲዩብ ተጠቃሚዎች ቁጥር በከፍተኛ ሁኔታ ማደጉን ማሳያ ነው። ደረጃው የተሰላው ከሰው ንክኪ ነፃ በሆነ አውቶማቲክ ሲስተም መሆኑ ተዓማኒነቱን ከፍ አድርጎታል።

የሳምንቱ ምርጥ 10 የሙዚቃ ደረጃዎች ዝርዝር፦

  1. ዳስ ጣል (አንሳው) – ቴዲ አፍሮ (+21.3 ሚሊዮን እይታ)
  2. ስምምነን (ጉሬጌ) – ቴዲ አፍሮ (+14.2 ሚሊዮን እይታ)
  3. ሺ ቢባል (ወደ 90ዎቹ) – ቴዲ አፍሮ (+6.5 ሚሊዮን እይታ)
  4. ጀምበር – ቴዲ አፍሮ (+4.9 ሚሊዮን እይታ)
  5. ዝ ፀዳል – ቴዲ አፍሮ (+4.7 ሚሊዮን እይታ)
  6. መሬማ – ቴዲ አፍሮ (+4.5 ሚሊዮን እይታ)
  7. መርከብ – ቴዲ አፍሮ (+4.2 ሚሊዮን እይታ)
  8. ጽዮን ሙሽራዬ – ቴዲ አፍሮ (+4.0 ሚሊዮን እይታ)
  9. ብልጭታ – ቴዲ አፍሮ (+3.8 ሚሊዮን እይታ)
  10. ጋልሜ ሴና – ገላና ጋሮምሳ እና ዮሳን ጌታሁን (+2.4 ሚሊዮን እይታ)

ቴዲ አፍሮ በዓለም የምርጥ 20ዎች ዝርዝር ውስጥ ስሙን በወርቅ ቀለሙ ጻፈ

ድምፃዊ ቴዎድሮስ ካሳሁን (ቴዲ አፍሮ) ከ9 ዓመታት ቆይታ በኋላ፣ 18 ሙዚቃዎችን ያካተተ “ኢትዮሪካ” የተሰኘ ስድስተኛ  አልበሙ ከተለቀቀበት ቅጽበት ጀምሮ ከፌስቡክ እስከ ቲክቶክ፣ ከዩቲዩብ እስከ X (ትዊተር) ዋነኛ የመነጋገሪያ ርዕስ ሆኗል። በሀገራችን የኪነ-ጥበብ ስኬቶችን በዝርዝር መዝግቦ ይፋ የሚያደርግ ተቋም ባይኖርም፣ በግል ጥረት ጎግልን (Google) በመጠቀም በተደረገ ፍተሻ ቴዲ አፍሮ የሚከተሉትን ታሪካዊ ስኬቶች አስመዝግቧል፡

  1. የአፍሪካ አዲስ ሪከርድ ቴዲ አፍሮ በአንድ የአፍሪካዊ ድምፃዊ ታሪክ ውስጥ በ24 ሰዓታት ውስጥ ከፍተኛ ተመልካች በማግኘት ቀደም ሲል የነበረውን የ22 ሚሊዮን እይታ ሪከርድ በመስበር፣ በድምሩ 32.1 ሚሊዮን እይታዎችን በማግኘት የመጀመሪያው አፍሪካዊ ሆኗል።
  2. የሰብስክራይበር (Subscriber) እድገት የድምፃዊው የዩቲዩብ ቻናል በአንድ ቀን ውስጥ ብቻ ግማሽ ሚሊዮን የሚጠጉ አዳዲስ ተከታዮችን በማፍራት 1.84 ሚሊዮን ደርሷል። ይህ በአጭር ጊዜ ውስጥ የተመዘገበ ከፍተኛ እድገት በአፍሪካ ታይቶ የማይታወቅ 2 ሚሊዮን ሊገባ ችሏል።
  3. “ዳስ ጣል” እና ዓለም አቀፍ ተጽዕኖ በአልበሙ ውስጥ የሚገኘው “ዳስ ጣል” የተሰኘው ሙዚቃ ብቻውን ከ4 ሚሊዮን በላይ እይታዎችን በማግኘት፣ በዩቲዩብ ታሪክ በ24 ሰዓታት ውስጥ ከፍተኛ ትኩረት ከሳቡ ጥቂት ቪዲዮዎች ተርታ ተሰልፏል።
  4. ከምርጥ 20ዎቹ ተርታ የዓለምን የ24 ሰዓት የሪከርድ ዝርዝር ስንመለከት (ለምሳሌ የቢቲኤስ “Butter” 113 ሚሊዮን)፣ ቴዲ አፍሮ በ27.1 ሚሊዮን እይታው በዓለም ደረጃ በ24 ሰዓታት ውስጥ ከፍተኛ እይታ ካገኙ ምርጥ 20 አርቲስቶች አንዱ ለመሆን በቅቷል። ይህም አልበሙን ከእንግሊዝኛ ቋንቋ ውጭ ተሰርተው እንዲህ ያለ ከፍተኛ እይታ ካገኙ ጥቂት የሙዚቃ ስራዎች ቀዳሚ ያደርገዋል።

ለአድማጭ ያበቃው አዲሱ ስራው “ኢቶሪካ” አልበም በብዙ ሀገራት የዩቲዩብ ሙዚቃ ትሬንዲንግ (YouTube Music Trending) ቁጥር አንድ በመሆን መሪነቱን አሁንም እንደያዘ ነው። ይህ ለኛ ለኢትዮጵያውያን ብቻ ሳይሆን ለአፍሪካ የሙዚቃ ኢንዱስትሪም ትልቅ ክብር ነው።

የቴዲ ሙዚቃ ድንበር ተሻግሮ የብዙዎችን ልብ መግዛቱ፣ የጥበብን ኃይል እና የኢትዮጵያዊነትን ከፍታ የሚያሳይ ነው። የሀገር ፍቅርን እና የባህል ስብጥርን በዜማው አዋህዶ ዓለምን በማነቃነቅ ላይ ይገኛል። ሙዚቃ ቋንቋ የለውም፤ ነገር ግን የቴዲ ስራዎች እውነተኛ የሰው ልጅ ስሜትን የሚናገሩ በመሆናቸው ነው እንዲህ በዓለም አቀፍ ደረጃ በታላቅ ተቀባይነት እየተደመጡ ያሉት!

ከኢቶሪካ አልበም መውጣት ጀምሮ የቴዲ አድናቂዎች ለአልበሙ ያላቸውን አድናቆት ለመግለፅ ቃላት አጥተው ሲታዩ ራሳቸውን የቴዲ ተቃዋሚ አድርገው ከነበሩ ሰዎች ውስጥ አንዳንዶቹ ሙዚቃውን ከሰሙ በኋላ ስለ ቴዲ ያላቸውን አቋም ለመመርመር ሲገደዱ ታይተዋል፡፡ ከእነዚህም የሙዚቃ አድማጮች መሃከል አንዱ የሆነው ነጋሳ ደሳለኝ በፌስ ቡክ ገፅ ላይ ይህንን ብሏል፡፡ ‹‹በነገራችን ላይ ቴዲን ከሚተቹት አንዱ ነበርኩ፡፡ የኢትዮጵያን ሙዚቃ ከዜማ አንፃር አንድ እርከን ከፍ ማድረግ ነበረበት ብዬ፡፡ አሁን ግን ቴዲን በሚገባኝ መንገድ ሳይሆን በእርሱ መንገድ ፈለኩት፤ አገኘሁት፤የሀገራችን ድምፃውያን በሁለት መንገድ ሙዚቃን ይሰራሉ፡፡መጀመሪያ ግጥም፤ ከዛም ዜማ፤ መጀመሪያ ዜማ፤ ከዛም ግጥም፡፡ ለኔ በገባኝ ግጥም ሲቀድም ዜማው ለግጥሙ እንዲስማማ ተደርጎ ይሰራል፤ ከባዱ መንገድ ደግሞ ይሄ ነው፡፡ቴዲ ባለቅኔ ነው፤ ቅኔውን ኩልል አድርጎ ለማሰማት ዜማውን ቀላል ማድረግ የግድ ነው፤ እናም አደረገው፡፡ ግን ግን ደግሞ እንደ መሬማ ከባድ ግጥም እና ውስብስብ ዜማ ቅንብርም አለው፡፡ አረብኛ ሮክ እና ሀውስ ሚክስ የሚመስል፡፡ ግን ሁሉም በቦታው በሚያምርና በማይጎረብጥ መልኩ ተሰካክቶ፡፡ እናም ህይወትን ቴዲን በራሱ በመጣበትና ዘመኑን በገለፀበት መንገድ ተግባብቶ መስማት ይቀድማል እላለሁ›› ይላል፡፡

‹‹ኢትዮሪካ ለህዝብ ጆሮ ከደረሰ ሳምንት ቢቆጠርም በብዙ ተጠበቀ፣ ተደመጠ፣አስደሰተ ፣ አናደደ፣ ተተነተነ ብቻ በጥቅሉ አነጋጋሪነቱ እስከዛሬዋ እለት ድረስ እንደቀጠለ ነው›› የምትልው ደግሞ ደራሲ መአዛ ወርቁ ‹‹ እየመራን ባለው የዲጂታል ማህበራዊ መንግስት የአንድ አጀንዳ እድሜ ከሁለትና ሶስት ቀን አይዘልም ፡፡ ከፍተኛ የአድማጭ ቁጥር ከማግኘት አየር ላይ እስከማነታረክ እንዲህ መቆየት ክብረ ወሰኑ ነውና ይቆጠርለት፡፡ የአሁኑን ቴዲ አፍሮ ስራ ስኬት የቀደመውን የቴዲ አፍሮ አልበም ግዝፈትና እና ትኩረት በብዙ ያስከነዳል።›› ብላለች በፌስ ቡክ ገፃ ላይ፡፡

‹‹አንዳንዴ አንተ ወደ ፖለቲካው ባትሄድም፤ ፖለቲካው ወደ አንተ ይመጣል።›› የሚለው ደግሞ ሰለሞን አረዳ ነው፡፡‹‹ቴዲ የገጠመው እንደዚህ አይነት ፈተና ይመስለኛል።አርቲስቱ ኮርኳሪ አገራዊ እና ታሪካዊ ጉዳዮችን በማንሳት የሚታወቅ ነው። በዚህም የተነሳ ቴዲ አልበም ሊያወጣ ነው ሲባል:- “ደሞ ምን ብሎ ይኾን!” ብሎ የሚጠብቀው ብዙ ነው።ከግጥሞቹ መሃል ስንኝ መዞ ለገበያ የሚያቀርበው ብዙ ነው። ሰደበኝ እና አሞገሰኝ የሚለው ዕልፍ ነው። ስለዚህ ቴዲ በሚጓተቱ የፖለቲካ ኃይሎች መካከል የሚቆምና የከያኒነት ነጻነቱን የሚያጣ አሳዛኝ አርቲስት ነው።

እሱ ባይፈልግም የግራ እና የቀኝ ፖለቲካው ደጃፉ ይቆማል። በዙሪያው የሚሽከረከረው የፖለቲካ ፍላጎት እና ትርፍ ፈላጊነት ስለሚበዛ ወዳጅ እና ጠላት መለየት ያቅታል። የቴዲ ዝምታም ትክክል ነው። ከአፉ የሚወጣውን ቃል ለመሰነጣጠቅ የሚጠብቁ ብዙ ናቸውና።›› ይላል፡፡

የቴዲን ሙሉ አልበም ላይ አስተያት ከሰጡ አድናቂዎቹ ሌላ የአንዳንድ ዘፈኖቹን ግጥሞችና ቃላት በመተንተን ላይ የተጠመዱ አድማጮችም ነበሩ፡፡ዳንኤል ጌታቸው አንዱ ሲሆን ከኢቶሪካ አልበም ጥቂት የቃላት ትርጉሞች በሚል ርዕስ የሚከተለውን አጋርቷል፡፡

የዘፈኑ ርዕስ፦ የማዕረግ ጥግ(አብራ ኗሪዬ)

“መሳይ ሱላማጢስ የውበት ሩቅ ዳርቻ

አንድ አድርጎ ፈጠረሽ እስካይኖርሽ አቻ”

ሱላማጢስ፦ በመፅሐፍ ቅዱስ ውስጥ በመኃልየ መኃልይ ዘሰሎሞን ላይ የምትገኝ ወጣት ሴት ስም፥ ‘የሰላም ሴት’ የሚል ትርጉም ያላት፥ የሙሽራው (የንጉስ ሰሎሞን) ፍቅረኛ፥ ቆንጆ፣ ትሁትና ታማኝ ሴት

የዘፈኑ ርዕስ፦ ዝ ፀዳል

“ከወንዙ ዳር ከአባይ ግዮን

የተገኘች ቶጳዝዮን”

ቶጳዝዮን፦ በኢትዮጵያ የሚገኝ፥ አረንጓዴ ቀለም ያለው፥ የሚያብረቀርቅ፥ የሚያበራ፥ ለአልባሳት ጌጥና ለነገስታት ዘውድ የሚያገለግል የከበረ እንቁ

የዘፈኑ ርዕስ፦ ጀምበር

“ሀለዎቴ የልቤ ትርታ

አመላክቺኝ ሀቅ ያለው ቦታ”

ሀለዎቴ፦ ‘መኖሬ’ ወይም ‘ህልውናዬ’፥ ሀለወ፦ ኖረ ወይም አለ ከሚለው ግሥ የወጣ

የዘፈኑ ርዕስ፦ ፅዮን ሙሽራዬ

“የካባዋ ሙካሽ፥ ቀዩ ጥብጣብ ሲያምርባት”

ሙካሽ፦ በሀበሻ የባህል ልብሶች (ካባ፥ ቀሚስ) ላይ በወርቅ ወይም በብር ክር የሚሰራ ጥበባዊ የጥልፍ ስራ ወይም ማስዋቢያ

የዘፈኑ ርዕስ፦ መሬማ

“እንደ አፋር አፍሌታ የጠየመው ፊቴን

ሌላው ቢቀር እንኳን እይው ማንነቴን”

አፍሌታ፦ አፋር ውስጥ ለውሃ መያዣነት የሚጠቀሙበት፥ ከፍየል ቆዳ የሚሰራ

የዘፈኑ ርዕስ፦ ሳምነው

“እመምነቴ፥ እማማ”

እመምነት፦ የመነኮሳት እናት፥ የገዳም መሪ መንፈሳዊ እናት፥ አስተዳዳሪ

የዘፈኑ ርዕስ፦ በመስኮቱ

“ልክ እንደ ፀባርቅ የአይኖችሽ ውጋጋን

አንድ አድርጎ ዘለቀው ክረምትና በጋን”

ፀባርቅ፦ ማንፀባረቅ፥ መታየት/መገለጥ

በኢቶሪካ–ቲንታጎ/ፒንታጎ (ያሻገርከን_ቅኔ) የዎላይተኛ ዜማ ግጥምና ቅኔ ላይ ትንታኔ የሰራው የብሔሩ ተወላጅ ቦጋለ ታጁ

‹‹አስጌ ደንዳሾ/አስጌ (Asgegnew Ashko) ከብላቴናው ጋር “በኢትዮርካ” #ሃገር_አድን_ጥሪ አልበም «ትራክ 7» ላይ “ፒንታጎ” እያለ በግልና በጋራ እየተቀባበሉ አዚመዋል።›› ሲል ይጀምራል፡፡

‹‹ፒንታጎ ማለት ቀጥሎ ባለው መልኩ ከተጻፈ ሁለት ትርጉም ይኖረዋል። ‘ጎ’ is matter. ፒንታጎ እና ፒንታ-ጎ መካከል ሰፊ ልዩነት አለ፡፡ «ፒንታጎ» ማለት ‹‹ያሻገርከን›› ወይም «ያሻገረን እሱ ነው» ማለት ሲሆን፤ «ፒንታ-ጎ» ደግሞ እሱ ያሻግር ይበልህ/ሽ/ን ማለት ሲሆን፤ በዐ.ነገር ሲገለጽ፦ literally, “እሱ ካልፈቀደ ማሻገር አትችልም” ማለት ነው። አሁን ጥያቄው “እሱ” ማነው የሚለው ነው። ለእኔ እንደ ገባኝ “እሱ” ተብሎ የተጠቀሰው “ፈጣሪ” እንደሆነ እርግጠኛ መሆን ይቻላል። ግጥሙ ዜማውና መልእክቱ ለመላው ለሰው ልጅ ክብር ፣ መብትና ፍትህ የተነገረ፤ የተጠየቀ ጥያቄ እንጂ በማንም ግለሰብና ቡድን ላይ ያነጣጠረ አይደለም።›› ይላል፡፡

በኢቶሪካ አልበም የተሳተፉ ባለሙያዎች

ወጣቱ ጋዜጠኛ ታምሩ ዓለሙ ደግሞ ከምድረ አሜሪካ በአልበሙ ዙሪያ የተሳተፉ ባለሙያዎችን አስተዋውቋል፡፡ በኢቶሪካ አልበም የተሳተፉ ባለሙያዎች ቴዲ አፍሮ የ18ቱ ሙዚቃዎች ግጥምና ዜማ ደራሲ ከመሆኑ በተጨማሪ ‘የአዞ እምባ አይደለም’ በሚለው ዘፈን ላይ በአቀናባሪነት አግዟል ‘ፅዮን ሙሽራዬ’ በተሰኘው ሙዚቃ 23 ባለሙያዎች ተሳትፈውበታል፤ ይህም በአልበሙ ውስጥ ከሚገኙ ሙዚቃዎች መካከል ብዙ ሰው ያሳተፈ ሙዚቃ አድርጎታል በኢትዮጵያ የሙዚቃ ታሪክ ትልቅ ስምና ዝና ያላቸው ባለሙያዎች በዚህ አልበም አሻራቸውን አሳርፈዋል፤ አንጋፋው የሊድ ጊታር ተጫዋች ሰላም ስዩም ‘ዝ ፀዳል’ እና ‘ተወዳጅ’ በተሰኙ ስራዎች ላይ ተጫውቷል፤ እውቁ የሳክስፎን ተጫዋች ያሬድ ተፈራ ደግሞ በስምንት ሙዚቃዎች ላይ ድንቅ ጥበቡን አሳይቷል፤ አበጋዝ ክብረወርቅ በሁለት ሙዚቃዎች ላይ በድምፅ ቅጂና በማስተሪንግ አስተዋፅኦ አድርጓል፤ ክብረት ዘኪዎስ በድምፅ ቀረፃ ተሳትፏል ‘ፅዮን ሙሽራዬ’ በአቦጊዳ ባንድ የተቀናበረ ሲሆን ቀሪዎቹ 17 ስራዎች በ6 ባለሙያዎች ቅንብር፣ ሚክሲንግ፣ ኪቦርድና ማስተሪንግ ተሰርቶላቸዋል ወጣቱ በረከት ተስፋዝጊ ስምንት ሙዚቃዎችን ሰርቷል፤ ታየኝ፣ መሬማ፣ ስምምነ፣ ዝ ፀዳል፣ በመስኮቱ፣ ብልጭታ፣ ሳምነው፣ የማዕረግ ጥግ የእሱ ውጤቶች ናቸው፤ በተጨማሪ ሊድ ጊታርም ተጫውቷል የዳስ ጣል፣ ቲንታጎና ኢቶሪካ አቀናባሪ እንዲሁም የመሬማ፣ ታየኝ፣ ስምምነ፣ በመስኮቱ፣ ተወዳጅና የማዕረግ ጥግ ማስተሪንግ ቀማሚ ደግሞ ማሩ አለማየሁ ነው አቤል ጳውሎስ የአዞ እምባ አይደለምና ተወዳጅ፥ ሀይፐር ዜማ መርከብና ስማ እራሴ፥ በፍቃዱ ግርማ ጀምበር እንዲሁም ሮቤል ዳኜ ሺ ቢባል ዜማዎችን አቀናብረውና ሚክስ አድርገው ለአልበሙ ስኬታማነት ጉልህ ሚና ተጫውተዋል ታመነ መኮንን ክራር፥ ቻላቸው አረጋና ወንድሜነህ ክፍሌ ማሲንቆ እንዲሁም ጣሰው ወንድምና ኤርሚያስ ናደው ዋሽንት በመጫወት የሀገራችንን ባህላዊ የሙዚቃ መሳሪዎች ከዘመናዊው ጋር አቀናጅተው ለአልበሙ ተጨማሪ ጣዕም አበርክተዋል ስድስት የውጭ ሀገር ዜጎችም ተሳትፈዋል፤ ጀምስ ክሮምዌል እና ኮይሲ ክሮምዌል ትራምፔት፥ ስቲቭ ብራድሊና ፎስተር ሞቲ ትራምቦን፥ ግሬግ ጃንግ ሳክስፎን፥ ዴስትኒ ፒቮንካ አልቶ ሳክስፎን ተጫውተዋል ድምፃዊ አስገኘው አሽኮ(አስጌ ዴንዳሾ) በቲንታጎ ዘፈን በግጥምና በፊውቸሪንግ ተሳትፏል፤ ተዋናይ መኮንን ላዕከ ደግሞ በስማ እራሴ በድምፅ ግብአት ያልተጠበቀ ክስተት ሆኖ ተደምጧል፤ የወሎ እናቶች ምርቃት(ፀሎት)፣ የፀሀዬ ደመቀችና የኢትዮጵያ ትቅደም ዜማዎች እንዲሁም የአፄ ሀይለስላሴ ንግግር በጀምበር ሙዚቃ በድምፅ ግብአት ገብተዋል ድምፃዊያኑ ሚኪያስ ቸርነት፣ ልዑል ሲሳይ፣ አዲስ ጉርሜሳ፣ ምኞት ሀይሉ(ዲጄ ዊሽ)፣ አለማየሁ ደሊልና በሀይሉ ዳንኤል አጃቢ ተቀባዮች ሆነው አልበሙን አድምቀዋል በአጠቃላይ 50 የሚጠጉ ባለሙያዎች በኢቶሪካ አልበም ተሳትፈው ለስኬታማነቱ የራሳቸውን አሻራ አሳርፈዋል፤ ለሁሉም ምስጋና ይገባቸዋል!ብሏል፡፡

የሙያ ጓደኞቹ ምስክርነት

ቴዲ አፍሮ በሙዚቃ አድናቂዎች ብቻ ሳይሆን በሙያ ጓደኞቹም አድናቆትን የተላበሱ አስተያየቶችን አስተናግዷል፡፡ ከሙዚቃ አልበሙ መውጣት ጀምሮ በተከታታይ ስለ ቴዲ አድናቆቷን ስትገልፅ የታየችው ቬሮኒካ አዳነ ማየት የምፈልገው ኮንሰርት የቴዲ አፍሮን ነው በማለት ለሙዚቃ ስራዎቹ ያለትን አድናቆት ተናግራለች፡፡ ያሬድ ነጉና ልዑል ሲሳይ፤ ብስራት ሱራፌልና አስጌ ሳሚ ዳንና አብርሃም ወልዴ፤ ዮሴፍ ገብሬ(ጆሲ)ና ዳዊት ፅጌ፤ሄኖክ ጥበቡና ራሄል ጌቱ ፤ ዳኜ ዋለና ሸዋንዳኝ ኃይሉ፤ አህመድ ተሾመ(ዲንቢ)ናአዲስ ለገሰ፤መሳይ ተፈራና ናቲ ማን ከብዙ አርቲስቶች መሀከል ጥቂቶቹ ናቸው፡፡

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

ትስስር ይፍጠሩ

325,851FansLike
49,039FollowersFollow
13,194SubscribersSubscribe