የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ በሆርሙዝ ሰርጥ ላይ ዛሬ አዲስ ተልዕኮ እንደሚጀመር ገለጹ፡፡ ይህንን ተልዕኮ ለማደናቀፍ በሚሞክሩ ሃይሎች ላይም በሃይል የታገዘ እርምጃ እንደሚወሰድ ተናግረዋል፡፡ ቴህራን በበኩሏ ሁኔታው የተደረሰውን የተኩስ አቁም ስምምነት እንዲጣስ የሚያደርግ ነው ብላለች፡፡
አሜሪካ ከዛሬ ጀምሮ የሀገራትን የንግድ መርከቦች ከሆርሙዝ ሰርጥ በማጀብ ማስወጣት እንደሚጀመር ነው የተናገሩት፡፡
በአሜሪካ እና ኢራን መካከል ባለው ወታደራዊ ግጭት ምክንያት በሆርሙዝ ሰርጥ የታገዱ መርከቦችን ለማስለቀቅ በሚደረገው ኦፕሬሽን ፕሮጀክት ፍሪደም ላይ 15ሺ የአሜሪካ ወታደሮች፡አውዳሚ የጦር መርከቦች እና ከ100 በላይ አውሮፕላኖች እንደሚሳተፉ የአሜሪካ ማዕከላዊ ዕዝ አስታውቋል፡፡
ሴንትኮም በኤክስ ማህበራዊ ትስስር ገጹ ላይ ባወጣው መግለጫ አሜሪካ ለፕሮጀክት ፍሪደም የምታደርገው ወታደራዊ ድጋፍ አውዳሚ የጦር መርከቦችን፡ከ100 በላይ በየብስ እና በባህር ላይ የተመሰረቱ አውሮፕላኖችን ጨምሮ 15ሺ የጦር ሠራዊት አባላትን እንደሚያካትት አስታውቋል፡፡
ትራምፕ በሰርጡ መርከቦች በነጻነት እንዲንቀሳቀሱ ይደረጋል ያሉ ሲሆን፤ቴህራን በበኩሏ ማንኛውም በሰርጡ ላይ የሚደረግ ጣልቃ ገብነት እንደ ተኩስ አቁም ስምምነት ጥሰት ይቆጠራል ብላለች፡፡
ትራምፕ የአሜሪካ ጦር አለም አቀፍ መርከቦች በሆርሙዝ ሰርጥ በኩል በሰላም እንዲተላለፉ የማድረግ ስራውን ዛሬ እንደሚጀምር ይፋ አድርገዋል፡፡
የሆርሙዝ ሰርጥ እና የፐርሺያን ገልፍ በትራምፕ የቅዥት መልዕክት ቁጥጥር ስር አይደለም ነው ያለችው፡፡የአሜሪካ ባህር ሃይል ወደ ሆርሙዝ ሰርጥ ለመግባት ሙከራ የሚያደርግ ከሆነ የጥቃት ኢላማ እንደሚደረግ ኢራን አስታውቃለች፡፡
ፕሬዝዳንት ትራምፕ ዛሬ ሰኞ ፕሮጀክት ፍሪደም ሲሉ በጠሩት ተልዕኮ መርከቦች በሆርሙዝ ወሽመጥ በኩል በነጻነት መውጣት ይጀምራሉ ሲሉ ነው ያስታወቁት፡፡
ፕሬዝዳንት ትራምፕ ሁሉም የዓለም ሀገራት የንግድ መርከቦቻቸው ነጻ እንዲሆኑላቸው ጠይቀውናል፤እኛም ይህንን እንደምናደርግ ገልጸንላቸዋል ብለዋል፡፡ ነገር ግን ኢራን የአሜሪካ ጦር ይህንን እንዲያደርግ ፍላጎት የላትም፡፡
በዚህ ስዓት ወደ 20ሺ ሰራተኞች እና 2ሺ የሚደርሱ መርከቦች መንቀሳቀሻ አጥተው ቆመዋል፡፡
ትራምፕ እነዚህን መርከቦች አሜሪካ በማጀብ ልታስወጣ ስለመሆኗ ነው የገለጹት፡፡
እንደ ተንታኞች እምነት ከሆነ ሁለተኛ ወሩን ላስቆጠረው ለዚህ ጦርነት ብቸኛ መፍትሔ ሰርጡ እንዲከፈት ማድረግ ነው፡፡ በመቀጠልም በኢራን የኒውክሌር ጉዳይ ላይ ረጅም ዲፕሎማሲያዊ ድርድሮችን ማድረግ የሚለው እንደሆነ ያነሳሉ፡፡
በሌላ በኩል የአሜሪካ እና የኢራኑ ጦርነት 66ኛ ቀኑን በያዘበት በዛሬው እለት ፕሬዝዳንት ትራምፕ በሆርሙዝ ሰርጥ አዲስ ተልዕኮ አስጀምረዋል፡፡
ትራምፕ እንዲህ አይነቱን ውሳኔ የወሰኑት ኢራን ላቀረበችው የሰላም እቅድ ከአሜሪካ የተሰጣትን ምላሽ ከተቀበለች በኋላ ነው፡፡
ኢራን የካቲት 21 ጦርነቱ ከተቀሰቀሰ ጀምሮ አንድ አምስተኛ የሚሆነው የዓለም ነዳጅ የሚተላለፍበትን የሆርሙዝ ሰርጥን ዘግታ ቀጥላለች፡፡
ትላንት እሁድ ኢራን ከዩናይትድስቴትስ የተሰጣትን የሰላም እቅድ ምላሽ ተቀብላለች፡፡ የድርድሩ ዋነኛ አሸማጋይ የሆነችው ፓኪስታን ጥረት እየተደረገበት የሚገኘው ዲፕሎማሲያዊ ንግግርን በተመለከተ ከኢራን ተደራዳሪዎች ጋር የስልክ ግንኙነት ማድረጓን ቀጥላለች፡፡
ፕሬዝዳንት ትራምፕ ኔቶ አሜሪካ እና እስራኤል ከኢራን ጋር እያደረጉት ባለው ጦርነት በቂ ድጋፍ አለማድረጉን በማንሳት ወቅሰዋል፡፡
የኔቶ ዋና ጸሐፊ ማርክ ሩተ የአውሮፓዊያን መሪዎች ፕሬዝዳንት ትራምፕ 5ሺ የሚሆኑ ወታደሮች ከጀርመን ለቀው እንደሚወጡ ከተናገሩ በኋላ ይህንን በተመለከተ መልዕክት ደርሷቸዋል ብለዋል፡፡
በዚህ ምክንያት ከአሜሪካኖች በኩል መበሳጨት አለ ሲሉ ዛሬ ሰኞ ገልጸዋል፡፡
ሄዝቦላህ ከእስራኤል ጋር እያደረገ በሚገኘው ጦርነት ከባድ የሚባል ዋጋ እየከፈ ነው ተባለ፡፡
ጥቃቱን ተከትሎ በሺዎች የሚቆጠሩ ተዋጊዎቹ ተገድለውበታል ተብሏል፡፡ ከሳምንታት በፊት የሊባኖስ መንግስት በአስርት ዓመታት ውስጥ ለመጀመሪያ ጊዜ ከእስራኤል ጋር የፊት ለፊት ንግግር ማድረጉ ይታወሳል፡፡
የሊባኖሱ ታጣቂ ቡድን ሄዝቦላህ አሜሪካ እና እስራአል የጣምራ ጥቃት በኢራን ላይ በየካቲት 21 ከጀመሩ ከሁለት ቀናት በኋላ ነበር ጥቃት በማድረስ በይፋ ጦርነቱን የተቀላቀለው፡፡
ሄዝቦላህ በዚህ ጦርነት ለመሳተፍ የወሰነው ሊባኖስ በአሜሪካ እና በኢራን የድርድር አጀንዳ ውስጥ እንድትካተት ያስገድዳል በሚል ግምገማ መሆኑን ሮይተርስ ዘግቧል፡፡
ቡድኑ በጋዛው ጦርነት በነበረው ተሳትፎ ከፍተኛ ጉዳት የደረሰበት ሲሆን፤የቡድኑ መሪ ሀሰን ናስረላህ እና ወደ 5ሺ የሚጠጉ ተዋጊዎች ተገድለዋል፡፡
ይህም በሊባኖስ መንግስት ላይ የነበረውን የረጅም ጊዜ የበላይነት እንዲዳከም አድርጎታል ተብሎ ይታመናል፡፡
ከማርች 2 ጀምሮ ከ2ሺ600 በላይ ሰዎች መገደላቸውን የሊባኖስ ጤና ጥበቃ ሚኒስቴር ገልጻል፡፡ ከእነዚህም ውስጥ አንድ አምስተኛ የሚሆኑት ሴቶች፡ህጻናትና የህክምና ባለሙያዎች ናቸው ብሏል፡፡
የእስራኤል ጦር ሄዝቦላህ በመቶዎች የሚቆጠሩ ሮኬቶችን እና ሰው አልባ አውሮፕላኖችን ከማርች 2 ጀምሮ ወደ እስራኤል ተኩሷል፡፡
እስራኤል በደቡባዊ ሊባኖስ 17 ወታደሮች እንደተገደሉባት ያስታወቀች ሲሆን ከዚህ በተጨማሪ በሰሜን እስራኤል ሁለት ሲቪሊያን ተገድለዋል ብላለች፡፡
ከሄዝቦላህ ጋር ግንኙነት ያላቸው አንድ ዲፕሎማት ቡድኑ ወደ ጦርነቱ ለመግባት የወሰነውን ውሳኔ የህልውና ስልት ሲሉ ጠርተውታል፡፡
ቴህራን በሊባኖስ ላይ እየተካሄደ ያለው የእስራኤል ዘመቻ ከዋሽንግተን ጋር በሚደረግ ስምምነት ውስጥ እንዲካተት ጠይቃ ነበር፡፡ ነገር ግን ፕሬዝዳንት ትራምፕ ዋሽንግተን ከቴህራን ጋር የምታደርገው ማንኛውም ስምምነት በምንም መልኩ ሊባኖስን አይመለከትም ማለታቸው ይታወሳል፡፡
አሜሪካ እና እስራኤል የሊባኖስ መንግስት ቡድኑን ትጥቅ እንዲፈታ ጫና እንዲያሳድር የሚገልጹ ቢሆንም፤ቡድኑ ግን ይህንን ውድቅ አድርጓል፡፡
ምንአልባትም የሊባኖስ መንግስት በሃይል ሄዝቦላህን ትጥቅ ወደማስፈታት የሚገባ ከሆነ የእርስ በርስ ጦርነት ሊቀሰቀስ ይችላል ተብሎ ይሰጋል፡፡

