አርቲስት ኪዳኔ ምስጋናው ዛሬ ማለዳ ከዚህ አለም በሞት ተለየ። አሰልጣኝና ኬሮግራፈር እንዲሁም የውዝዋዜ አማካሪ አርቲስት ኪዳኔ ምስጋናው በ1958 ዓ.ም በአዲስ አበባ ከተማ ተወለደ። ትምህርቱንም እስከ 12ኛ ክፍል ካጠናቀቀ በኻላ ለኪነ ጥበብ በነበረው ፍቅር ምክንያት በት/ቤትና በተለያዩ ክበባት በውዝዋዜ ሙያ ሲሰራ ቆይቶ በ 1977 ዓ.ም በአዲስ አበባ ቴአትርና ባህል አዳራሽ በተወዛዋዥነት ተቀጠረ። ከጊዜያት በኻላም የተቋሙ ሃላፊዎች የሙያ ፍቅሩንና የፈጠራ ክህሎቱን በመመልከት ከ 1983 ዓ.ም ጀምሮ እስከ 1990 ዓ.ም በረዳት አሰልጣኝነት እንዲሰራ ተደርጓል፡፡
ከ1991 ዓ.ም እሰከ 1992 ዓ.ም የቋሚ አሰልጣኝነቱን ቦታ ተረክቦ በርካታ ባለሙያዋችን አሠልጥኗል። ከ1992 ዓ.ም እሰከ 2007 ዓ.ም ከቴአትርና ባህል አዳራሽ ወደ ሀገር ፍቅር ቴአትር ቤት ተዛውሮ በዋና አሰልጣኝነትና በኬሮጋራፈርነት የሰራ ሲሆን ከ 2007 ዓ.ም እስከ 2017 ዓ.ም ወደ አዲስ አበባ ቴአትርና ባህል አደራሽ በመመለስ በአሰልጣኝነትና በኬሮግራፈርነት እየሰራ የሰራ ሲሆን በ2018 ዓ.ም በድጋሚ ወደ ሀገር ፍቅር ቴአትር ቤት ተመድቦ እስከ ህይወቱ ፍፃሜ ድረስ እየሰራ ይገኝ ነበር።
አሰልጣኝና ኬሮግራፍር እንዲሁም የውዝዋዜ አማካሪ አርቲስት ኪዳኔ ምስጋናው በሞያው በሰራባቸው አመታት በርካታ ባለሙያዎችን ከማፍራት ባሻገር ከህዳሴው ግድብ ጀምሮ እስከ መንግስት በአለ ሲመት፣ ከባህል ሳምንት እስከ ብሄር ብሄረሶቦች ቀን ክብረ በአላት፣ ከአድዋ እስከ የካቲት 12 የአደባባይ ስራዎች፣ ከፉና ቴሌቭዥን የዳንስና የውዝዋዜ ውድድር እስከ በየክሎች በመጓዝ የብሄረሰቦችን ቱባ ባህልን እስከ ማጥናት፣ ከአዲስ ከበባ እስከ ክልል ከተሞች፣ ከሰው ሰራሽ ችግር እስከ ተፈጥሮ አደጋዎች የማስተባር ስራ፣ ከአለም አቀፍ የመንግስታትና የዲፕሎማቶች አቀባበል፣ ከከንቲባ ፅ/ቤት እስከ ቤተመንግስት ድረስ በኬሮግራፈርነት፣ በአሰልጣኝነት፣ በዳኝነትና በአማካሪነት የሙያ አስተዋፅኦውን ያበረከተ ድንቅ የጥበብ ሰው ነበር።
አርቲስቱ ለነዚህ ሙያዊ አስተዋፅኦዎቹም ከአዲስ አበባ ዩንቨርስቲ፣ ከኤፊድሪ ባህልና ቱሪዝም ሚንስቴር፣ ከአዲስ አበባ ባህል ኪነ ጥበብና ቱሪዝም ቢሮ፣ ከኤፊድሪ ፊዴሬሽን ምክር ቤት፣ ከታላቁ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ማስተባበሪያ ጽ/ቤት፣ ከሀገር ፍቅር፣ ከቴአትርና ባህል አደራሽ፣ ከራስ ቴአትር፣ ከብሔራዊ ቴአትር እና ከሌሎችም በርካታ ተቋማት የምሰጋና ሰርተትኬት አግኝቷል፡፡
አሰልጣኝና ኬሮግራፈር እንዲሁም የውዝዋዜ አማካሪ አርቲስት ኪዳኔ ምስጋናው ሙያው እንዲያድግና ባለሙያውም እንዲጠቀም በነበረው ፍላጎትና ቁጭት ምክንያት የባህል ውዝዋዜ በተለያዩ ትልልቅ ሆቴሎችና የባህል ምሽቶች እንዲሰራና ባህላችን የበለጠ እንዲተዋወቅ በማማከርና በማስጀመር የአንበሳውን ድርሻ ይወስዳል፡፡
በከተማ ደረጃም በቀረቡ ታላልቅ ህዝባዊ በአላትና የሙዚቃ ኮንሰርቶች ላይ የኬሮግራፈር ስራዋችን ታዋቂና አንጋፋ ድምጻውያን ሙዚቃ በማጀብ ስራዋቹን አቅርቧል ከሰራባቸው መድረኮችም መካከል
• በሸራተን አዲስ ሆቴል
• በሚሊንየም አዳራሽ
• በኤግዚብሽን ማዕከል
• በመስቀል አደባባይ
• በአዲስ አበባ ስታድየም
• በጊዮንና ሂልተን ሆቴሎች
• በስካይ ላይት ሆቴል እና በሌሎችም ትልልቅ የቀጥታ የቴሌብዥን ስርጭት የነበራቸውን የኬሮግራፈር ስራዎቹን አቅርቧል፡፡
አሰልጣኝ፣ ኬሮግራፍር እንዲሁም የውዝዋዜ አማካሪ አርቲስት ኪዳኔ ምስጋናው በተለያዩ ቴአትሮችና ሙዚቃዊ ቴአትሮች ላይም በትወናና በዝግጅት ሰርቷል። በትወና ከተሳተፈባቸው ቴአትሮች መካከል
* ጤና ያጣ ፍቅር
* ሮሚዮና ዡልየት
* የቀለጠው መንደር
በሙዚቃዊ ድራማ ኬሮግራፈር ዝግጅት የተሳተፈባቸው ደግሞ
* ፎርፌ
* ኢትዮጵያዊነት ጥልቅ ነው
* ከልሽን አውልቂ
* የሊስሮ ኦፔራ
* ሉሲ
* ሀገር ማለት ሰው ነው..እና በሌሎችም ላይ ተሳትፏል።
አርቲስት ኪዳኔ ምስጋናው ከመድረክ ስራዎቹ በተጨማሪም በተለያዩ ታዋቂና አንጋፍ እንዲሁም ወጣት ድምጻውያን የሙዚቃ ክሊፖች ላይ በኬሮግራፈርና በአማካሪንት ሰርቷል ለምሳሌ የኤፍሬም ታምሩና የዶ/ር ጥላሁን ገሰሰን ስራዎች በዋናነት መጥቀስ ይቻላል።
አሰልጣኝና ኬሮግራፍር እንዲሁም የውዝዋዜ አማካሪ አርቲስት ኪዳኔ ምስጋናው ከሙያው ጋር በተያያዘ ከዱባይና ከታይላንድ በተጨማሪ በበርካታ ሀገራት ስራዋቹን በማቅረብ ባህሉን ሀገሩን ያስተዋወቀ የጥበብ አምባሳደር ነበር።
በ 2017 ዓ.ም የኢ.ፌ.ዲ.ሪ ባህልና ስፖርት ሚኒስቴር ባዘጋጀው ሀገር አቀፍ “የክብር ለጥበብ” የዕውቅና መርሀ ግብር አርቲስት ኪዳኔ ምስጋናው በ “ባህላዊ ውዝዋዜ” ዘርፍ ለሀገሩ ላበረከተው ትልቅ አስተዋፅኦ ከታላቅ ምስጋና ጋር ሰርተፍኬት ተበርክቶለታል።
አርቲስት ኪዳኔ ምስጋናው በህክምና ሲረዳ ቆይቶ ግንቦት 22/2018 ዓ.ም በ 60 ዓመቱ ከዚህ አለም በሞት የተለየ ሲሆን ባለትዳርም ነበር።
የዚህ ታላቅ የጥበብ ሰው ቤተሰቦቹ፣ የሙያ አጋራቹ አድናቂዎቹና ታላላቅ ሰዎች በተገኙበት የክብርና የሽኝት መርሀ ግብር በሀገር ፍቅር ቴአትር ቤት ግንቦት 25/2018 ዓ.ም ጠዋት ከ3:00-6:00 ሰአት የሚደረግ ሲሆን የቀብር ስነ ስርአቱም በዕለቱ 7:00-8:00 በ መሣለሚያ አማኑኤል ቤ/ክርስቲያን የሚፈፀም ይሆናል።
የአዲስ አበባ ቴአትርና ባህል አዳራሽ አመራሮችና ሰራተኞችም ለአርቲስቱ ቤተሰብ፣ ጓደኞች፣ አድናቂዎችና ባልደረቦች መፅናናቱን ይሰጣቸው ዘንድ ይመኛል።

