ለንጉሱ ሐውልት ቆሞለታል!!
በአዲስ አበባ ከተማ ስድስት ኪሎ የተገነባው የክብር ዶክተር አርቲስት ጥላሁን ገሠሠ መታሰቢያ ሐውልት ሚያዝያ 27/2018 ዓ.ም ተመርቋል።
የኢትዮጵያ የሙዚቃ ንጉሥ የታላቁ ድምፃዊ ጥላሁን ገሠሠ ከ 50 ዓመት በላይ ለሚሆን ጊዜ በተለየ ድምፁና ስሜት በሚጭሩ ዘፈኖቹ የሙዚቃ ኢንዱስትሪውን በመምራት በብዙዎች የሚወደድ የጥበብ ሰው ነው ። የጥበብን ጉዞ ገና በልጅነቱ የጀመረ ሲሆን ከሃገር ፍቅር እስከ ዘበኛ ኦርኬስትራ፤ ከብሄራዊ ትያትር እስከ ካሴት ላይ ስራዎቹ አይረሴ ለመሆን ችሏል፡፡ ጥላሁን በሙዚቃ ሙያው ከተሰለፈበት ጊዜ
ጀምሮ ያልዳሰሳቸው ርዕሰ ጉዳዮች አልነበሩም፡ ፡ ስለእናት፣ ስለሃገር፣ ስለፍቅር፣ ስለጀግንነት፣ ስለውበት… ያልዘፈነበት ርዕሰ ጉዳይ ፈልጎ
ማግኘት ይከብዳል።
የሙዚቃ ሰራዎቹ የነፍስ መነጋገሪያ ቋንቋ ሆነው ከዘመን ዘመን ተሻግረው እስካለንበት ጊዜ ዘልቀዋል፡፡ ጥላሁን ገሠሠ ብዙዎቹ ስራዎቹ የአማርኛ ዘፈኖች ሲሆኑ ከዛም ባለፈ የተወሰኑ የሙዚቃ ሰራዎቸ ደግሞ በአፋን ኦሮሞ እና በሱዳንኛ ዘፍኗል። ለዘመናት የዘለቀ የሙዚቃ ስራው በአገር ውስጥና በውጭ አገር ከፍተኛ አድናቆትን አትርፏል። ጥላሁን ለኢትዮጲያ ሙዚቃ ላደረገው አስተዋጽኦ ከአዲስ አበባ
ዩኒቨርስቲ የክብር ዶክትሬት ዲግሪ ለማግኘት በቅቷል። በሌላ በኩል ህይወቱን በሙሉ ለሙዚቃ በማበርከቱ ከኢትዮጵያ ኪነጥበብና
የብዙህን መገናኛ ሽልማት ድርጅት «የሙሉ ዘመን» ሽልማት ተሸላሚ ለመሆን በቅቷል።
ክብር ለዶክተር ጥላሁን ገሰሰ የዘመኑ ንጉሥ”በሚል ቅጽል ስምም በመላው ኢትዮጵያ ህዝብ ዘንድ ከፍተኛ ክብር ተችሮታል ። ጥላሁን ገሠሠ ሚያዝያ 11 ቀን 2001 ዓ.ም. በ68 ዓመቱ ከዚህ ዓለም በሞት ተለይቷል ።
የመታሰቢያ ሐውልቱን የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤ በይፋ መርቀዋል። ሐውልቱን ወጣቱ ሰዓሊና ቀራፂ ብርሃኑ ታደሰ በሁለት ዓመት ውስጥ ሰርቶ ማጠናቀቁ ታውቋል፡፡ ኃላፊዎች እንዲሁም አርቲስቶች ተገኝተዋል።
የመሐሙድ አሕመድ መታሰቢያ ሞዛይክ አርት
የኢትዮጵያ ሙዚቃ ደማቅ አምባሳደር የሆነው የጋሽ መሐሙድ አሕመድ ሞዛይክ አርት በይፋ ተመርቋል። ይህ መታሰቢያ በከተማዋ እንዲቆም የተደረገው አንጋፋው አርቲስት ለሀገራዊ አንድነት፣ ለሰላምና ለኪነ ጥበብ ዕድገት ላበረከተው የማይተካ ሚና ዕውቅና ለመስጠት ታስቦ ነው። መሐሙድ አሕመድ የኪነ ጥበብ ጉዞውን በ1950ዎቹ አጋማሽ በክብር ዘበኛ ኦርኬስትራ ውስጥ የጀመረ ሲሆን
በተለይም በ60ዎቹና በ70ዎቹ የኢትዮጵያ ሙዚቃ ወርቃማ ዘመናት ውስጥ የትዝታ ስልት ንጉሥ በመባል ስሙን በታሪክ መዝገብ ላይ በደማቅ ቀለም አስፍሯል። በተለይ ሰላም የተሰኘው የሙዚቃ ሥራው የሀገር ፍቅርንና አንድነትን በመስበክ ረገድ በሕዝብ
ዘንድ እንደ ብሔራዊ መዝሙር የሚታይ ከፍተኛ ተወዳጅነትን ያተረፈ ነው።
ለሰው ልጆች ፍቅር ለሰው ልጆች ሰላም፣ ለሰው ልጆች በዓለም ዙሪያ ሁሉ፣ ሰላም ይሁን ምድሩ ሁሉ የሚሉት የእርሱ የዜማ ስንኞች ዛሬም ድረስ በብዙዎች ልብ ውስጥ የታተሙ ናቸው። ድንቅ የጥበብ ሰው መሐሙድ አሕመድ በሕይወት እያለ እንዲህ ዓይነት ታላቅ ክብርና ዕውቅና መሰጠቱ ለወጣቱ የኪነ ጥበብ ትውልድ ከፍተኛ መነሳሳትን ከመፍጠሩም በላይ አንጋፋ ባለሙያዎችን በሕይወት
እያሉ የማክበርን አዲስ ባህል የሚያጎለብት ነው።
አርቲስቱ በተለይም አረ መላ መላ በተሰኘው የሙዚቃ አልበሙ የኢትዮጵያን ባህልና ዜማ በዓለም አቀፍ መድረኮች በማስተዋወቅ ረገድ ግንባር ቀደም ተጠቃሽ መሆኑ ይታወቃል።
የ “አሊ ቢራ መታሰቢያ ሞዛይክ አርት
“አሊ ቢራ፤ ከድሬዳዋ እስከ ዓለም አቀፍ መድረኮች” አርቲስት አሊ መሐመድ ቢራ መስከረም 15 ቀን 1940 ዓ.ም በድሬዳዋ ከተማ ገንደ ቆሬ ተወለደ። ገና የሦስት ዓመት ሕፃን እያለ ወላጆቹ በመለያየታቸው በአባቱ እጅ ያደገው አሊ፣ በልጅነቱ የአገር ውስጥና ዓለም አቀፍ ሙዚቃዎችን በማዳመጥና ለቤተሰቦቹ በማንጎራጎር ነበር የሙዚቃ ፍቅሩን ያሳየው። በድሬዳዋ ከተማ ለነበረው የብዙ ቋንቋዎች
ተናጋሪነት ምቹ ሁኔታ ምስጋና ይግባውና በአረብኛ፣ በአፋን ኦሮሞ ፣ በአደርኛና በሶማሊኛ ቋንቋዎች ሙዚቃዎችን የመጫወት አቅም ነበረው። የአሊ ቢራ የሙዚቃ ጉዞ በይፋ የጀመረው በ1954 ዓ.ም ገና በ13 ዓመቱ የኦሮሞን ሙዚቃ ለማስተዋወቅ የተቋቋመውን
“አፍረን ቀሎ” የተሰኘውን የሙዚቃ ቡድን በመቀላቀል ነበር።
ሙዚቃዎቹ በዋናነት በአፋን ኦሮሞ ቋንቋ የቀረቡ ቢሆኑም፣ መልዕክቶቻቸው ግን ስለ ፍቅር፣ ስለ ሰው ልጅ መብት፣ ስለ እኩልነትና ስለ ሰላም የሚያጠነጥኑ ዓለም አቀፋዊ ይዘት ያላቸው ነበሩ። ለኢትዮጵያ ኪነ-ጥበብ ላበረከተው ከፍተኛ አስተዋፅኦ ከጅማና ከድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲዎች የክብር ዶክትሬት ዲግሪ የተሰጠው አርቲስት አሊ ቢራ፣ ለ56 ዓመታት በሙዚቃ ዓለም ውስጥ አገልግሏል።
ለረጅም ዓመታት በስደት በውጭ አገር ቆይቶ ወደ አገሩ ከተመለሰ በኋላ ጥቅምት 27 ቀን 2015 ዓ.ም በ75 ዓመቱ ከዚህ ዓለም በሞት ተለይቷል። በአዲስ አበባ ከተማ ኡራኤል አካባቢ የተገነባው የ “አሊ ቢራ መታሰቢያ ሞዛይክ አርት ሚያዝያ 27/2018 ዓ.ም ተመርቋል።
የሎሬት ጸጋዬ ገብረመድኅን የመታሰቢያ ሐውልት
ሎሬት ጸጋዬ ገብረመድኅን ለኢትዮጵያ ሥነ-ጽሑፍ እና ለቴአትር ጥበብ የቆመ የማይናወጥ ተራራ ነው። የእርሱ ዐርበኝነት በጠመንጃ ሳይሆን
በብዕር፣ በቃላት እና በሐሳብ ምጥቀት የተገነባ መሆኑ ይመሰከርለታል።
ሎሬት ጸጋዬ የኢትዮጵያን የሦስት ሺህ ዓመታት ታሪክ ከዘመናዊው ዓለም ጋር በማስተሳሰር፣ ኢትዮጵያዊነትን እንደ አንድ ታላቅ
የሥልጣኔ ማኅደር ለዓለም ያስተዋወቀ ድንቅ ጠቢብ ነው። በሥራዎቹ የሚሰብከው ዐርበኝነት “ራስን ማወቅ” ላይ የተመሠረተ ነው። በዚህም ኢትዮጵያ በታሪኳ ያለፈችባቸውን ፈታኝ ወቅቶች ወደ መድረክ በማምጣት፣ ሕዝቡ የታሪኩ ባለቤት
እንዲሆን አድርጓል።
በ”ጴጥሮስ ያቺን ሰዓት” ተውኔቱ ውስጥ፣ ብፁዕ አቡነ ጴጥሮስ ለኢትዮጵያ ነፃነት እና ለሃይማኖታቸው ሲሉ ለፋሽስት ጣሊያን ላለመገበር
የከፈሉትን መሥዋዕትነት በዝርዝር ሥሏል። በ”ቴዎድሮስ” ተውኔቱ ደግሞ የአፄ ቴዎድሮስን የአንድነት ራዕይ እና የመጨረሻውን የክብር
መሥዋዕትነት ሲተርክ፣ ዐርበኝነት ማለት ለሀገር ክብር ሲሉ ራስን አሳልፎ መስጠት መሆኑን በአንባቢው እና በተመልካቹ አዕምሮ ውስጥ አስርጿል። በግጥሞቹ ውስጥ ኢትዮጵያ ተራ መሬት ሳትሆን፣ ነፍስ ያላት እና ልጆቿን የምትንከባከብ “እናት” አድርጎ ይሥላታል።
በ”እሳት ወይ አበባ” መድብሉ ውስጥ ኢትዮጵያን እንደ ጥንታዊት የጥበብ ምንጭ፣ እንደ ኩሩ እናት እና እንደ መከራ ጽናት ይገልጻታል። የእርሱ ዐርበኝነት ሀገሩን ከነጉድለቷ እና ከነግርማዋ ወድዶ፣ ያንን ፍቅር በቃላት ሸምኖ ለዓለም ማሳየቱ ላይ ነው። “ሀ ሁ በስድስት
ወር” እና ሌሎችም ሥራዎቹ የኅብረተሰቡን ሕመም የሚያሳዩ እና ለለውጥ የሚጋብዙ ነበሩ።
ሀገርን መውደድ ማለት ሕዝቧን መውደድ እና ለሕዝቧ ሰላም መቆም መሆኑን በተግባር አሳይቷል። የሎሬት ጸጋዬ ገብረመድኅን ዐርበኝነት
“ኢትዮጵያዊነትን” እንደ ወርቅ አንጥሮ፣ እንደ ዕንቁ አሳምሮ ለትውልድ ማውረሱ ላይ ነው። ለእርሱ ኢትዮጵያዊነት ማለት የጎሣ ወይም የቋንቋ ድምር ሳይሆን፣ የጥቁር ሕዝቦች የነጻነት ተምሳሌት የሆነ ታላቅ የጋራ ቤት ነው። ጸጋዬ ዛሬም በሐውልቱ ቆሞ የሚያስተምረን፤ እውነተኛ ዐርበኝነት ሀገርን በጥልቀት ከመውደድ እና ታሪክን ጠንቅቆ ከመረዳት እንደሚመነጭ ነው። ትውልዱ በቃላት እና በሐሳብ
የመሸነፍ ሳይሆን፣ የመጠየቅ እና የመመራመር አቅሙን እንዲያሳድግ ጥሪ ያቀርባል። ሀገርን መገንባት የሚቻለው በጠብ ሳይሆን፣ እንደ ጸጋዬ በኪነ-ጥበብ አማካኝነት የጋራ ታሪካችንን በማድመቅ መሆኑን ያስገነዝበናል።
በአዲስ አበባ ከተማ የተገነባው የ ሎሬት ጸጋዬ ገብረመድኅን መታሰቢያ ሐውልት ሚያዝያ 27/2018 ዓ.ም ተመርቋል።
የደራሲ ስብሐት ገብረ እግዚአብሔር የመታሰቢያ ሐውልት
ደራሲ ስብሐት ገብረ እግዚአብሔር የኢትዮጵያ ሥነ-ጽሑፍን መልክ የቀየረ፣ የሐሳብ ነጻነትን እና የእውነትን ኃይል በአደባባይ ያስመሰከረ
ጠቢብ ነው። ስብሐት የኢትዮጵያን ሥነ-ጽሑፍ ከቤተ-መንግሥት እና ከትልልቅ አዳራሾች አውጥቶ፣ ወደ ሕዝብ እና ወደ ጎዳናው ሕይወት ያወረደ የታችኛው ማኅበረሰብ ድምፅ የሆነ ዐርበኛ ነው።
እንደ “ሌቱም አይነጋልኝ” እና “ሰባተኛው ሰማይ” ባሉ ሥራዎቹ፣ የሰውን ልጅ ውስጣዊ ትግል እና የኑሮን መራራ እውነታዎች በሥነ-ጽሑፍ ቀርጿል። ለእርሱ ዐርበኝነት ማለት የራስን ማንነት አለመካድ፣ ከይስሙላ ሕይወት መውጣት እና ሰውን በሰውነቱ ብቻ ማክበር
ነው። ለዚህ የእውነት ዐርበኛ በመሐል አዲስ አበባ የቆመው ሐውልት ለአሁኑ ትውልድ የሚያስተላልፈው መልዕክት አለ፤ “ራስህን ሁን” የሚል።
እውነተኛ ዐርበኝነት ሀገርን እና ሕዝብን ሳያታልሉ በእውነት ማገልገል መሆኑንም ይረዱበታል። ሐውልቱ ትውልዱ በጥላቻ እና
በሐሰት ትርክት ከመነዳት ይልቅ፣ እንደ ስብሐት ገብረ እግዚአብሔር እውነትን በመፈለግ እና ለሐሳብ ነጻነት ዋጋ በመስጠት ሀገሩን እንዲገነባ ጥሪ ያቀርባል። ዛሬ በአዲስ አበባ የቆሙት ሐውልቶች፣ ከተማዋን ከማስዋብ ባለፈ የሀገርን የጋራ ትውስታ የመገንባት ትልቅ ፋይዳ አላቸው።
በአዲስ አበባ ከተማ የተገነባው የ ደራሲ ስብሐት ገብረ እግዚአብሔር መታሰቢያ ሐውልት ሚያዝያ 27/2018 ዓ.ም ተመርቋል።
የአርቲስት ሀጫሉ ሁንዴሳ የመታሰቢያ ሐውልት
በአዲስ አበባ ከተማ አፍሪካ ፓርክ ውስጥ የተገነባው የአርቲስት ሀጫሉ ሁንዴሳ መታሰቢያ ሐውልት ሚያዝያ 27/2018 ዓ.ም ተመርቋል። የሐውልቱን የምረቃ ሥነ ሥርዓት የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤ በይፋ የፈጸሙ ሲሆን በመርሐ ግብሩ ላይ ከፍተኛ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች እና ታዋቂ የኪነ ጥበብ ባለሙያዎች ተገኝተዋል።
ከንቲባ አዳነች አቤቤ በማኅበራዊ ትስስር ገጻቸው ባስተላለፉት መልዕክት እንደገለጹት አርቲስቱ በኪነ ጥበብ ዘርፍ ለሀገሪቱ ላበረከተው ከፍተኛ አስተዋጽኦ እና ለሀገር ባለውለታነቱ ዕውቅና ለመስጠት በመዲናዋ ይህ የመታሰቢያ ሐውልት ሊቆምለት ችሏል። ከንቲባዋ አክለውም ጥበብ ሀገርን የመገንባት አቅም እንዳላትና ሀገርም የጥበብ ሰዎችን ማክበር እንዳለባት በመግለጽ ጥበብ ሀገር ትሠራለች ሀገርም ጠቢብን ታከብራለች የሚለውን መልዕክት አስተላልፈዋል።

