ከአሜሪካ ጋር የተደረሰ ምንም አይነት ስምምነት አለመኖሩን ኢራን ይፋ አድርጋለች፡፡ የኢራን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አባስ አራግቺ ከአሜሪካ ጋር የሚደረገው ውይይት እስካሁን ምንም አይነት ውጤት ላይ እንዳልደረሰ በይፋ ተናግረዋል፡፡
ይሁን እንጂ የውይይቱ በር አሁንም ክፍት መሆኑን ከመግለጽ ወደኋላ አላሉም፡፡ ቴህራን በአሜሪካ አጋሮች ላይ የሰነዘረችውን ጥቃት ራስን የመከላከል እርምጃ ሲሉ የጠሩት ሚኒስትሩ ማዕቀብና ጦርነት ያላስቆመውን የኢራን አቋም ተጨማሪ ጦርነት በመክፈት ሊቀይሩት አይችሉም በማለት ለዋሽንግተን ጠንካራ ማስጠንቀቂያ አስተላልፈዋል፡፡
በሌላ በኩል የኢራን የሚሳኤልና የድሮን ጥቃት ቀጠናውን እያወከው ቀጥሏል፡፡ የኩዌት የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር እንዳስታወቀው በኢራን ጥቃት ምክንያት የአገሪቱ ዓለምአቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ የወደመ ሲሆን፤የአንድ ሰው ህይወት አልፎ 60 ሰዎች ደግሞ ቆስለዋል፡፡
ፕሬዝዳንት ትራምፕ በበኩላቸው ከኢራን ጋር ያለው ድርድር በመልካም ሁኔታ ላይ መሆኑን ገልጸው፤ጦርነቱን የሚያበቃ ስምምነት በቅርቡ እንደሚደረስ በመግለጽ ላይ ናቸው፡፡ እንዲያውም ምንአልባትም በሳምንጡ መጨረሻ የሚፈጠር አዲስ ነገር ይኖራልም እያሉ ነው፡፡
ዓለምአቀፍ ተንታኞች እንደሚሉት ከሆነ ግን ይህ ተስፋ የተጣለበት የተኩስ አቁም ስምምነት በበርካታ ግንባሮች ከባድ ፈተና ገጥሞታል፡፡ ዋሽንግተን በቴህራን ላይ ጥቃት ስትሰነዝር፤በአንጻሩ ኢራን በኩዌትና ባህሬን በሚገኘው የአሜሪካ ጦር ሰፈሮች ላይ የፈጸመችው አጸፋዊ ጥቃት ስምምነቱን ዳግም ጥርጣሬ ውስጥ ጥሎታል፡፡ በሌላ በኩል የእስራኤሉ ጠቅላይ ሚኒስትር የኢራን ባለስልጣናት በእሳት ጨዋታ ይዘዋል አሉ፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ኔትንያሁ ኢራን በእሳት እየተጫወተች ነው፤የእኛና የአሜሪካ ሃይሎች ደግሞ ዝግጁ ናቸው በማለት ገልጸዋል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለመገናኛ ብዙሃን በሰጡት ልዩ ቃለ ምልልስ ኢራን ያላትን የዩራኒየም ክምችት ለማስወገድ ፈቃደኛ አለመሆኗን ይፋ አድርገዋል፡፡ ይሁን እንጂ በቴህራን ላይ እየበረታ የመጣው ጫና ከፍተኛ መዳከምን እየፈጠረባት መሆኑንም ጠቁመዋል፡፡
ከኢራን ጋር ዳግም ወደ ሙሉ ጦርነት የመግባቱ ጉዳይ በፕሬዝዳንት ትራምፕ ውሳኔ ላይ የተመሰረተ መሆኑን አንስተዋል፡፡
ባለፉት ቀናት በሁለቱ መሪዎቹ መካከል አለመግባባት መኖሩ ሲዘገብ የነበረ ሲሆን፤ፕሬዝዳንት ትራምፕ ራሳቸው ጉዳዩን በይፋ አረጋግጠዋል፡፡ ስለ ሁኔታው ሲያብራሩም አዎ በጣም ጠንካራ ውይይት አድርገናል፡፡ በጣም ተናድጄ ነበር፤ሊባኖስ ውስጥ ባለው ያልተቋረጠ ጦርነት ተረብሼ ነበር በማለት አብራርተዋል፡፡//
ዋሽንግተን እና ቴህራን ከዲፕሎማሲው ጀርባ ወደ ከባድ ፍጥጫ አምርተዋል

