የሲአይኤ መፈንቅለ-መንግሥት ምሥጢራዊ ኦፐሬሽን በአዲስ አበባ!

(ከራሱ ከኦፐሬቲቩ አንደበት)

በኢትዮጵያችን የቅርብ ዘመን ታሪክ፣ እጅግ ክፉ ክፉ የሚባሉት የታሪካችን ጠባሳዎች የደረሱብን ከ60ዎቹ እስከ 80ዎቹ ባሉት ከ20 ዓመት በማይበልጡ ዓመቶች ነው። ያሳዝናል። ይገርማልም። እና ያንን ሀገር የተቀበረችበትን፣ ትውልድ ያለቀበትንና ሌሎች ሀገሮች ኮስተር ብለው ሀገራቸውን ሲገነቡ ያሳለፉትን ጊዜ፣ እኛ ኮስተር ብለን የተሠራውን ሁሉ በማፈራረስና እርስበርስ በመጠፋፋት ማሳለፋችን ብዙ ጎድቶናል።

ከብዙው ዓለም ወደ ኋላ ያስቀረን አንድ ነገር ይሄ እኛ ስንጠፋፋ፣ ሌሎቹ ሲገነቡ ያሳለፍነው አጭር ጊዜ ይመስለኛል። ያለፈውን እያሰቡ የሆኑብንን ነገሮች ማሰስ፣ ማጥናት፣ ማወቅ… እንደ መቆዘም ሲቆጠር አያለሁ። ግን ስህተት ይመስለኛል። እርግጥ ነው የውድቀት ዘመናችንን ማሰብ ቁዘማ አለበት። የማይቆዝሙ ካሉ ውድቀታችንን ሆነ ብለው ያመጡት ብቻ ናቸው። እና በውድቀታችን ላይ ያበቡት። ነገር ግን ቁዘማችን በዚያው ቆዝሞ ለመቅረት አይደለም። ከትናንቱ ለመማር ነው። ማን ምን እንዳደረገ፣ ይሄኛው ወይም ያኛው የእነማን የእጅሥራ እንደሆነ ለማወቅ ነው። ለመቆጨትና ትናንት ከገባንበት ገደል በጥበብ ለመውጣት ነው። ያለፈውን የምናጠናው፣ አሁናችን ላይ እንዴት እንደተገኘን ትምህርት ለመውሰድ ነው። ለዚህ ይመስለኛል (ራሴን ጨምሮ) ብዙ ሰው፣ ያንን ያለፈውን የስብራት ዘመናችንን ለማወቅ የተሧሟሟቀ ፍላጎት ያደረበት የሚመስለኝ። ዛሬ ብዙ የቀደሙት የውድቀታችን ዘመን ትውልዶችና ተዋንያን፣ በርከት ያሉ ድርሳናትን እየፃፉልን ነው። እማኝ ቃላቸውን እየሰጡን ነው። የእኛም ፍላጎት፣ የእነሱም ተነሳሽነት፣ እሠየሁ ነው። በእኔ አመለካከት፣ ኢትዮጵያችንን እንደ ሀገር በቁሟ ገንዞ ወደ መቃብሯ ውስጥ የጨመራት፣ እና አሁን ለምንገኝበት ቀላል መዳኛ የሌለው የውርዴ ዘመን የዳረገን፣ ትልቁ ምክንያቱ ውጫዊ ነው። ከሌሎች ጋር በመወዳጀታችን፣ አሊያም በመቃቃራችን የመጣብንን መቅሰፍት ነው አሁን እያወራረድን ያለነው! ከምንም በላይ፣ ሀገራችን በዚህ ወሳኝ የታሪክ ምዕራፍ ላይ፣ ከተሸናፊው የዓለም ጎራ፣ ማለትም ከምሥራቁ ዓለማቀፋዊ የኮሙኒስት ጎራ ተሰልፈን መገኘታችን፣ ትልቁን ዛሬ የገባንበትን ገደል በራሳችን ላይ የጠራ፣ ትልቁ ገደቢስነታችን ነው። በአጋጣሚ ሆነና፣ ከተሸናፊው ወገን ተገኘን! አፈራረሱን። ረጋገጡን። ተረግጠንም ቀረን።

የኮሙኒስቷ ሀገራችን ባላንጣዎች የነበሩት የምዕራቡ ካፒታሊስት ሀገሮች (ወይም በዘመኑ አጠራር ኢምፔሪያሊስት ኃይሎች ይባሉ የነበሩት)፣ በእነዚያ ዓመታት በሀገራችን ላይ ያራመዱትን የጠላትነት ፖሊሲና፣ የሠሩብንን ሸፍጥ፣ ብዙውን ደብቀውታል። ሌላ ቀርቶ ለሕዝብ ይፋ ከተደረጉ የምዕራቦቹ የደህንነት ፋይሎች ውስጥ፣ አሊያም በውጭ ጉዳይ ሰነዶቻቸው ውስጥ፣ በእነዚያ 20 ዓመታት በኢትዮጵያችን ላይ የፈፀሙትን ደባ ለማግኘት የሞከረ ሰው እንደሚረዳው፣ ብዙውን ነገር እስካሁን እንደቀበሩት ነው። ብዙው ነገር በጥቁር ማርከር የተደለዘ ነው። ብዙው የሚያሠራጯቸው መረጃዎች የተምታቱና ቅጥፈት የተሞላባቸው፣ እንደ ጲላጦስ እጃቸውን ከደሙ ንፁህ ለማድረግ የታለሙ ናቸው። የኛ የታሪክ ፀሐፊዎች ድኩማኖች ናቸው። የታሪኩ ምንጭ ባለበት ቦታ ሄደው መፈተሽ፣ መመርመር፣ ማጣራት፣ ሞት ይመስላቸዋል። የአድርባይነትና የፍርሃት፣ ከፍ ሲልም የአሽቃባጭነትና ከዘመኑ ጋር መስሎ የመገኘት፣ የመገዛት ምርኮኞች ናቸው! የጀርመን ሪሰርቸሮች ስለ ናዚ ዘመን ብዙ ነገርን ዘልቀው ለመፈልፈል እንደሚፈሩት ማለት ነው። ወይ የፋሺስት ዘመንን የሚያጠኑ ታሪክ ተመራማሪዎች፣ ያሁኖቹን የዓለም ገዢዎች የሚያስከፉ እውነቶችን ለመምዘዝ እንደሚሸማቀቁት ማለት ነው። የተሸነፈ ታሪክ የለውም። ካለውም የጠለሸ፣ የተጎነዳደሸ፣ የተንሻፈፈ ነው።

በጌቶች ፈቃድ የተፈቀደለት ታሪብቻ ነው የሚነገርለት። የኛ ሀገር ያ የ20 ዓመት በሽንፈት የተጠናቀቀ ታሪክም እንደዚሁ ነው። ታሪከ ፀሐፊ ተብዬዎቻችን እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ፣ የኢትዮጵያችንን ታሪክ ይፅፉ ይፅፉና ልክ ያሁኑ ዘመን ላይ ሲደርሱ፣ እንደ ቤርሙዳ ትራያንግል አስምጦ ያስቀራቸው ይመስል፣ ዙሪያውን ይሽከረከሩታል። ከሩቁ ይሸሻሉ። ፈሪዎች ታሪክን ሊፅፉ አይችሉም። እውነትን ያላፈቀሩ ሰዎች ለምን እውነትን ወደሚጠይቅ የሙያና የዕውቀት መስክ እንደሚገቡ ሁሌም እንደተገረምኩ ነው። የኛን ያንን የ20 ዓመት ታሪክ ከእኛ ታሪክ ፀሐፊዎች ማግኘት የማይታሰብ ነው። በወቅቱ ከነበሩት ተዋናዮች አፍ ቢያንስ ግማሹን ብስል፣ ግማሹን ጥሬ አንገዋልሎ ለመቀበል ይቻለን ይሆናል። በተረፈ፣ ከዚህም ከዚያም የምናገኛቸውን ቅንጭብጫቢ የታሪክ ማስረጃዎችና እማኝነቶች መዝግበን ማኖር፣ ማሰባሰብ ግድ ይለናል። ዛሬ አቀናጅቶ የሚፅፋቸው ባይኖር፣ ነገና ከነገወዲያ የሚፅፋቸው እውነትን ፈላጊ ትውልድ መምጣቱ አይቀርም ብለን ተስፋ እናደርጋለን! ይህን ካልኩ ባጭሩ ከዚህ መፅሐፍ ስላገኘሁት ሀገራችንን የተመለከተ መረጃ አስቀምጬ ልሰናበት። የመፅሐፉ ደራሲ ቲም ዌይነር የታወቀ (ፑሊትዘር የተሸለመ) መርማሪ ጋዜጠኛ ነው። በተለይ የአሜሪካኖችን የስለላና ደህንነት ተቋማት ውስጠ ምስጢር ለ30 ዓመት ያጠና፣ የተመራመረ፣ ውስጣቸውን የበረበረ ምሁር ነው። በዚህ መፅሐፉ ምዕራፍ 40 ላይ (ከገፅ 456 ጀምሮ) የሚፅፈው፣ በ1983 በፈረንጆቹ አቆጣጠር (በእኛ በ1975/76 ላይ ይመስለኛል) በአሜሪካው ፕሬዚደንት ሮናልድ ሬገን ፊርማ ፀድቆ፣ ወደተግባር ተሸጋግሮ ስለነበረው፣ በኢትዮጵያ የነበረውን ኮሙኒስታዊ ወታደራዊ መንግሥት የማስወገድ ምሥጢራዊ የሲአይኤ ኦፐሬሽን ነው የሚነግረን። ይህን ደራሲው የሚነግረንን የመሠሉ ታሪካዊ መረጃዎችን ለማግኘት በበኩሌ፣ ብዙ ጥረት ያደረግኩበት ወቅት ነበር። በሆነ ወቅት የወቅቱን የምዕራቦቹንና ምሥራቆቹን መሪዎችና የሚሊቴሪና ደህንነት አርካይቮችን ለማሰስ የቻልኩትን ጥሬያለሁ። የእነ ሄንሪ ኪሲንጀርንና የመሳሰሉትን የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ ነዳፊዎችና አስፈፃሚዎች ሥራና ታሪክ ለመመርመርም ሞክሬያለሁ። ሌላም ሌላም። ግን ያገኘኋቸው መረጃዎች እዚህ ግባ የሚባሉ አልነበሩም። ብዙዎቹ ተሰውረዋል።

በውሸት ቃሎች ተደልዘዋል። ስለሆነም ሆነ ብሎ ሙሉ ጊዜውን ሰጥቶ የሚመረምር ሰው ይፈልጋሉ። በእኔ አቅም፣ በእግረመንገድ ፍለጋ የሚሞከር አልነበረምና ተስፋ ከመቁረጥ በማይተናነስ ደረጃ ፍለጋዬን ተውኩት። ጆሮዎቼ ግን ሁሌም ንቁ ናቸው። ድንገት ባጋጣሚ፣ ያን ዘመን የሚመለከት ስለ ኢትዮጵያ አንዳችም ነገር ሹክ ከተባለ፣ ጆሮዎቼ እንደ አህያ ጆሮ ተቀስረው አየሩን ማነፍነፋቸውን አልተዉም። ታዲያ የዚህ “የአመድ ውርሶች – የሲአይኤ ታሪክ” የተሰኘው በዓለም የተጨበጨበለትና ለብዙ የጋዜጠኝነት ሽልማቶች ያበቃው መፅሐፍ ደራሲ፣ ቲም ዌይነር፣… በቆይታቸው ብዛት ለህዝብ ይፋ በሆኑ ሰነዶችም ውስጥ እንኳ ምንም ዓይነት ማስረጃ ያላገኘሁለትን፣ ይህን በኢትዮጵያ መንግሥትን (ወይም መንግሥቱን – መንግሥቱ ኃይለማርያምን) የመፈንቀል የሲአይኤ ፕሮጀክት ታሪክ፣ በአጋጣሚ ዘክዝኮት አላገኘውም? ጉድ! አልኩ! ጉድ፣ ጉድ! ጊዜ የማያወጣው ሃቅ ምን አለ? ይህ ያስደነቀኝ ታሪክ፣ በቀደሙት ዓመቶች በቬትናም ዘማች የነበረውና ኋላም በሲአይኤ ውስጥ ተመልምሎ የፊልድ ኦፊሰር ለመሆን የበቃው፣ የአሜሪካ የደህንነት ሰው፣ ቲሞቲ ዌልስ ደራሲው ከራሱ ከባለታሪኩ አንደበት ያገኘው፣ እውነተኛ ታሪክ ነው። ባጭሩ ታሪኩ እንዲህ ነው። ሲአይኤ በሌ/ኮ መንግሥቱ ኃይለማርያም የሚመራው ኮሙኒስታዊ መንግሥት፣ ልክ አንደ ሶቭየት ራሺያኖቹ ሁሉ፣ ለመላው አፍሪካና ለቀጣናው የአሜሪካ የበላይነት እጅግ አደገኛ ስለሆነ፣ ሲአይኤ በሚታወቅበት ምሥጢራዊ መፈንቅለ-መንግሥት እንዲወገድ የሚል ፕሮፖዛል ለፕሬዚደንት ለሬገን ያቀርባል። ሬገን ያፀድቀዋል። በዚህም መሠረት ዝርዝር ፕሮግራሙ ተዘጋጅቶ፣ በኢትዮጵያ የሚገኙ የመንግሥቱ ተቃዋሚዎች በምሥጢር ተደራጅተው፣ አስፈላጊው ግብዓት ሁሉ ተሟልቶ ሲያበቃ፣ መንጌን የሚፈነቅለውን ቡድን እንዲመራ፣ ይህ የሲአይኤ ኦፐሬቲቭ የ34 ዓመቱ ቲሞቲ ዌልስ፣ በዲፕሎማቲክ ከቨር ወደ አዲስ አበባ ይመጣል።

ቲሞቲ ዌልስ ታሪኩን ሲናገር፣ በሚገባ የሠለጠነ የማሪን ወታደር ነው። ኢትዮጵያ ከመምጣቱ በፊት በፕሬዚደንት ኒክሰን የሥልጣን ዘመን፣ በሱዳን የአሜሪካ ኤምባሲ ተመድቦ ሠርቷል። ከዚያ ደሞ ተመልሶ አሜሪካ በሲአይኤ የደህንነት ኮሌጅ ገብቶ ለ18 ወራት ሠልጥኗል። ያን ሲጨርስ፣ በንግድ አታሼነት የውሸት ከቨር ተሰጥቶት፣ በዩጋንዳ በሚገኘው የአሜሪካ ቆንሲላ ውስጥ ተመድቦ ሲንቀሳቀስ ነበር። በዚያም ሆኖ በኢትዮጵያ ላይ ስለሚያካሂደው የመፈንቅለ መንግሥት ኦፐሬሽን ከዩጋንዳ እስከ ሱዳን፣ ከበረሃዎች እስከ ደርግ ማዕከላዊ ኮሚቴ ያሉ ሜሥጢራዊ አባሎችን ሲያደራጅና ሲያሤር ቆየ። በመጨረሻም የሲአይኤው ፈንቃይ፣ ቲሞቲ ዌልስ፣ ዕቅዱ ወደ ተግባር የምትሸጋገርበት ቀን ደርሰችና፣ አዲስ አበባ ላይ ከተፍ አለ! ቲሞቲ ስለዚያ የሬገን የመንግሥት ግልበጣ ፕሮጀክት ሲናገር፣ የተመደበልን ባጀት በብዙ ሚሊየን ዶላሮች የሚቆጠር ነበር ይላል። በውጭ በስደት ከሚኖሩ የኢህአፓና መኤሶን የቀድሞ አባሎች ጀምሮ፣ በኢትዮጵያ ውስጥ እስከሚገኙ የዩነቨርሲቲ ፕሮፌሰሮች፣ የንግድ ማኅበረሰብ አባላትና ኢንቬስተሮች፣ ምሁራንና የሚሊቴሪ ሰዎችም ነበሩበት ይላል። ግን ቲሞቲ ዌልስ የሚጠረጥረው፣ ደርግ የአሜሪካኖቹን ሤራ አስቀድሞ ጠርጥሮ ወይም ከእንቅቃሴያቸው ባንኖ፣ የራሱን ሰዎች፣ በሲአይኤው ኦፐሬሽን ውስጥ አስርጎ አስገብቷል ብሎ ነው። ሌላም ግምት ነበረው። ኋላ እውነት መሆኑን የተረዳው። የደርግን መንግሥት ፀረ-ሰርጎገብ እንቅስቃሴዎች የሚያማክሩት ሰዎች ከሶቭየት ራሺያ የመጡ የኬጂቢ ሰዎች ነበሩ። ያ ብቻም አይደለም።

የመንጌን ቤተመንግሥትና እንቅስቃሴ በመምራትና በመቆጣጠር ላይ የተሠማሩት፣ ከደርጉ ደህንነት ጋር ተቀናጅተው እንዲሠሩ የተመደቡ፣ የምሥራቅ ጀርመን የስለላ ድርጅት (የስታሲ) ሰዎች ነበሩ። እና እኔ ሀገር አማን ብዬ ገና አዲሳባ ስደርስ፣ ሠርገኛው መጣ በርበሬ እንቀንጥስለት ብለው፣ አሸወይና እያሉ ነው ለካ የተቀበሉኝ ይላል በአግራሞትና በቁጭት፣ ዌልስ አዲስአበባ መጥቶ የገጠመውን ታሪኩን ለዚህ ደራሲ ሲነግረው። ይሄ የሲአይኤ ሰው የሚናገረውንም ሙሉ በሙሉ ማመን አያስፈልግም። ይመስለኛል። ምክንያቱም ሲናገር፣ የራሱን ሚና ፍፁም ሠላማዊ አስመስሎ ነው። ለማንኛውም ይሄ የሲአይኤ ኤጀንት (ዌልስ) ሲናገር፣ በወቅቱ አዲስአበባ በሚገኘው የአሜሪካ ኤምባሲ በዲፕሎማቲክ አባልነት ከሚሠሩት የስቴት ዲፓርትመንት ሠራተኞች ተብለው ከተመዘገቡት ብዙዎቹ የሲአይኤ ወኪሎች ነበሩ። (ሬሺዮውን ዌልስ ሲገልፀው “2 to 1” ነበር ይለዋል። መቶ ሰዎች ቢኖሩ፣ ወደ 70 የሚሆኑት የሲአይኤ ቅጥረኞች ናቸው እንደማለት ነበር!) ዌልስ የራሱን ሚና ሲገልፅ፣ ኢትዮጵያ ውስጥ ያደራጀናቸውን አባሎች በቢዝነስ ግንኙነት ሰበብ መገናኘትና፣ በአሜሪካ ከሚኖርና ለሲአይኤ ከሚሠራ የቀድሞ የኢትዮጵያ መከላከያ ሚኒስትር በኩል እየተዘጋጁ በዲፕሎማቲክ ሳጥኖች ታሽገው በድብቅ ሳጥኖች የሚገቡለትን የፕሮፓጋንዳ ፅሑፎች፣ የቅሰቀሳ ወረቀቶች፣ ፖሰተሮችና ገንዘቦች ለኢትዮጵያው ግሩፕ ማቀበል ነበር ሥራው። አገናኝ መኮንን ብቻ ነበርኩ ባይ ነው። ከዚያ ግን በዲሴምበር 20 ቀን፣ 1983 እኤአ፣ የሲአይኤው ኦፐሬቲቭ ቲሞቲ ዌልስ፣ በአንድ የአዲሳባ የሞጃ ሰፈሮች በአንዱ አፓርትማ ውስጥ፣ ከሰበሰባቸው የሤራው አባላት ጋር ድብቅ ስብሰባ እያደረገ እያለ፣ የደርግ ምሥጢራዊ የደህንነት ቡድን አባላት፣ ባልታሰበ ቅፅበት፣ የክፍላቸውን በር በረቃቅሰው ገቡ!

በዚያች ክፍል ከተሰበሰቡት መሐል፣ በቀኃሥ ዘመን የጃንሆይ አማካሪ የነበሩ የ78 ዓመት ባለፀጋ ነበሩበት። ዕድሜው 50 ዓመት የሚሆነው የታወቀ የአዲሳባ ነጋዴ። እና የእሱ ዘመድ (የአክስቱ ልጅ የሆነ) የባዮሎጂ ዶክተር። እና የሤራው አባላት ተደርገው የተመለመሉ የተቃዋሚ መሪዎች ይገኙበታል። በአጋጣሚ ሆኖ (ወይም በችሎታው) የደርግ ደህንነት ሰዎች የመሰብሰቢያ ክፍሉን ደርምሰው ሲገቡ፣ ቲሞቲ ዌልስ ወዲያው አልተያዘም! ወደ የት ተነነ? አስቂኝ ነበር። በጓዳ በነበረ የልብስ ቁምሳጥን ውስጥ፣ የቅሰቀሳ ፓምፍሌቶቹን ከያዘው ቦርሳዬ ጋር ዘልዬ ገባሁና በሩን ቀረቀርኩት ይላል። በቁምሳጥኑ ተደብቆ ሁለት ቀን ቆየ። በመጨረሻ ኮ/ል መንግሥቱ የራሱን የቤተመንግሥት ጠባቂዎች ወደተደበቀበት መኖሪያ ቤት ላካቸው። ምን መረጃ አግኝቶ አንደሆነ አይታወቅም። ሁሉም የተያዙት ሰዎች ቶርቸር ሲደረጉ ነበር። የጠቆሙት ነገር ይኖራል። መጡና ዳግመኛ ደግሞ የቁምሳጥኑን በር በርቅሰው ከነዶኪመንቶቹ ያዙት። እጅ-ከፍንጅ። ማንቁርቴን ይዘው፣ በናዝሬት ከተማ ወደሚገኝ የደህንነቶች ሴፍሃውስ ወሰዱኝ ይላል። እዚያ ስደርስ፣ ከመፈንቅለ መንግሥት አድራጊ ግብረሐይሎች ውስጥ የቀረ ሰው የለም ይላል። ይህ ኦንዴት ሊሆን ቻለ? ቲሞቲ ዌልስ የሚለው ደርግ አስርጎ ባስገባቸው ሰዎቹ አማካይነት፣ አጠቃላይ የሤራችንን ፕሮግራም ቀድሞ በልቶታል የሚል ነው። ከውስጣችን ባሉ ሰዎች ተክደናል ነው የሚለው። የደርግ የደህንነት ሰዎች አሜሪካዊ ነው ብለው አልማሩትም። ለአምሰት ሣምንቶች በሴፍሃውሳቸው አስረው፣ እየገረፉ ሚስጥሩን አስዘከዘኩት። በምርመራው ወቅት ጭንቅላቱ ላይ በደረሰበት ቅጥቀጣ ሁለት ቦታ የጭንቅላቱ አጥንት ተበርቅሶ (ተፈንክቶ) ነበረ። የትከሻው አጥንቶች እንኪወልቁ ነበር የቀጠቀጡት። በመጨረሻ በእናቱ ሆድ ያያትን ሁሉ ሳይናዘዝ አይቀርም። ያልተጠየቀውን ሁሉ። ጭራሽ በሰፖርት ግሩፕ ውስጥ የነበሩ፣ (በአክቲቭ ኦፐሬሽን ላይ ያልነበሩ፣ እና ስለሆነም ደርግ አስርጎ ያስገባቸው ሰዎች ራሱ ሊያውቋቸው የማይችሉ) ሰዎችን ሳይቀር በቶርቸር ብዛት ዘክዝኮ ለደርጉ ደህንነቶች ሰጠ። ሁሉም በኢትዮጵያ የነበሩ የሬገን ፕሎት ተሳታፊዎች፣ ከትንሹ እስከ ትልቁ ከያሉበት እየታደኑ ተለቀሙ። ተቀጠቀጡ፣ ታሠሩ። አንዳንዶቹም በተኩስ ልውውጥና በእሥር ላይ በተፈፀመባቸው ጭካኔ ህይወታቸውን አጡ። እንደ ምስኪን ቀብር በተፋጠነ ሶነሥርዓት እንዲረሸኑ ተደርገውም ይሆናል።

በመጨረሻ የመንጌ ሰዎች የሚፈልጉትን ሁሉ ከሰውየው ላይ አሟጠው ማግኘታቸውን ሲያረጋግጡ፣ በጦርነት የቆሰለ የሆሊውድ አክተር የሚመስለውን የሲአይኤ ሰው፣ ቲሞቲ ዌልስ፣ በእጃቸው እንደሚገኝ፣ በኬንያ ናይሮቢ በሚገኘው የኢትዮጵያ ኤምባሲ በኩል፣ በዚያው ናይሮቢ ለሚገኘው የእስራኤል ኤምባሲ ሰዎች ሹክ አሏቸው! ዜናው ሲሰማ በሲአይኤ ካምፕ የመሬት መንቀጥቀጥ ተከሰተ። እና እርስበርስ መካሰስ ተጀመረ። ኩኩ መለኮቴ። ሮናልድ ሬገን በዋይት ሃውሰ አስቸኳይ ስብሰባ ጠሩ። እና በጣም በአስቸኳይ፣ በሰዓቱ አፍሪካ ውስጥ “በጉብኝት ላይ” የነበሩትን የፕሬዚደንሺያል ሙሉ መልዕክተኛ፣ ጄነራል ቬረነን ዋልተርሰን፣ ሥራቸውን አቋርጠው፣ ወደ አዲስ አበባ በመብረር፣ ከጓድ መንግሥቱ ጋር አንዲደራደሩ አዘዙ (ላኳቸው)። በወቅቱ የአሜሪካ ኤምባሲ ዴፒዩቲ ቺፍ ኦፍ ሚሽን የነበሩት የ67 ዓመቱ ዲፕሎማት፣ ጆሴፍ ፒ. ኦኔይል፣ የሬገንን መልዕክተኛ ከመንጌ ጋር የማገናኘቱን ምልጃ ተወጡ። ጊዜ ቢወስድም ጥረታቸው ተሳካ። ከመንጌ ጋር በወታደራዊ መስክ በትብብር ይሠሩ የነበሩት የእስራኤል ሰዎችም በአማላጅነቱ ሥራ ውስጥ ሳይኖሩበት አልቀረም። መንጌ ደሞ በበኩሉ፣ አዲሳባ ላይ ሲጠበቅ፣ የት እንዲያገኙት ቀጠራቸው ጄነራል ዋልተርስን? – አስመራ በሚገኘው ቤተመንግሥት እንዲያገኙት። አይ መንጌ! አንበሣ እኮ ነበር! ሳይወዱ ወደ አስመራ በረሩ ጄነራሉ። ቀኑ ፌብርዋሪ 3፣ 1984 እኤአ ነው። ቲሞቲ ዌልስና ግብረአበሮቹ አዲሳባ ላይ ከተያዙ 45 ቀናት ሆኗቸዋል። የአሜሪካው ፕሬዚደንት ልዩ መልዕክተኛና የኢትዮጵያው ፕሬዚደንት መንግሥቱ ኃይለማርያም በአስመራ ቤተመንግሥት በቀጠሯቸው መሠረት ተገናኙ። ጄነራል ዋልተርስ ያን ገጠመኛቸውን ሲናገሩ፣ መንግሥቱ ኃይለማርያም ለ3 ሰዓት ያህል ስለ ኢትዮጵያ የተጋድሎ ታሪክ ሌክቸር ሲሰጠኝ ቆየና፣ በትዕግሥት አዳምጬ ስጨርስ፣ ምን እንደምፈልግ ጠየቀኝ።

የሳአይኤ አባላችንን ቲሞቲ ዌልስን ይዤ ለመመለስ እንደመጣሁ ነገርኩት። ቀጥተኛ አነጋገሬ መንግሥቱን ሳያስደንቀውም፣ ሳያስደስተውም አይቀርም። ሰውየው በህይወት አንዳለና እንደሚለቀቅ ነገረኝ። በምትኩ ግን ስለፕሮግራሙ ዝርዝር መረጃ ከኤምባሲው እንዲሰጠው፣ የተደበቁ አባላት መረጃ ተላልፎ እንዲሰጠው ጠየቀ። ተስማሙ። በማግሥቱ አዲስ አበባ ለሚገኘው የአሜሪካ ኤምባሲ ፕሬዚደንሺያል ትዕዛዝ ተላለፈለት፦ የመፈንቅለ መንግሥት ኦፐሬሽኑ ተርሚኔትድ ሆኗል። የኛ ሰዎች ያሉባቸው ሰነዶች ይቃጠሉ። የኢትዮጵያውያኑን ዝርዝር ግን ለመንግሥቱ ስጡ። በዚያ ዝርዝር የተነሳ፣ ብዙ ሰዎች ታሠሩ፣ ተገረፉ፣ ተገደሉ ይላሉ ኋላ ማስታወሻቸውን የፃፉት ዲፕሎማቱ ኦኔይል እያዘኑ። የሲአይኤው ሰው፣ ሁለት ወር ባልሞላ ጊዜ፣ፀጉሮ ሸብቷል። ጭንቅላቱ ተፈነካክቷል። አንዱ ትከሻው እንዳለ ወልቋል። ፊቱ በልዟል። ሲአይ ኤ ለዚሁ ተልዕኮ ባዘጋጃት የሊር አውሮፕላን ወደ አሜሪካ ዋሺንግተን ይዘውት በረሩ። ቲሞቲ ዌልስ ታሪኩን ሲናገር፣ ወደ አውሮፕላኑ ስገባ የጠበቀኝ አቀባበል፣ ለሀገሩ ሲሠራ በጠላት እጅወድቆ በህይወት እንደተረፈ የሲአይኤ አባል ሳይሆን፣ እንደ ከሃዲ ነበር። ቅዝቅባለ ፊት፣ እና በንቀትና በጥላቻ ዓይን ተቀበሉኝ ይላል። ዋሺንግተን ዲሲ እንደደረሱ፣ የተወሰነ ህክምና ተደርጎለት ገና በአግባቡ ሳያገግም፣ ሲአይኤ ዳሜጅ አሰስመንቱን ጀመረ ይላል። ቲሞቲ ዌልስ በቨርጂኒያ ገጠር ውስጥ ወደሚገኝ ምሥጢራዊ የሲአይኤ ሴፍሃውስ ተወስዶ በሲአይኤ መርማሪዎች ቃለመጠይቅ ይደረግለት ጀመር። ሁለት ሳምንት ሙሉ እየተፈራረቁ መረመሩት። እና ምን አረጋገጡ? ቲሞቲ ለኢትዮጵያ የደህንነት ሰዎች (ስለሆነም በተዘዋዋሪ ለኬጂቢና ለስታሲ ሰዎች) የሌሎች በኢትዮጵያ በህቡዕ የሚንቀሳቀሱ አራት የሲአይኤ ኦፐሬቲቮችን ስም አሳልፎ ሰጥቷቸዋል። ቲሞቲ የሚለው በተፈፀመበት ቶርቸር አስገዳጅነት ነበር መረጃዎቹን ያወጣው። ሲአይኤዎች ደሞ በራሳቸው ሰው እንደ ተካዱ ቆጠሩት። ቲሞቲ ዌልስ፣ አጠቃላይ ምርመራ ከተካሄደበት በኋላ በገዛ ፈቃዱ እንዲለቅ ተደረገ። እሥርና ውርደት ይሻልሃል? ወይስ በክብር ከነጡረታህ መሠናበት? ለብዙ መስዋዕትነትና አደጋ ራሱን አጋልጦ ከሠራለት ተቋም፣ ክብሩ ተገፍፎ፣ ፈረመና ለቀቀ! በኢትዮጵያን ሄራልድ ጋዜጣ የፊት ገፅ ላይ፣ አብዮቱን በሤራ ሊቀለብሱ የነበሩ ፀረ-አብዮተኞች ተያዙ ከሚል ርዕስ ጋር፣ የ18 በድብደባ የተገጣጠቡ ኢትዮጵያውያን ፎቶ ወጣ ይላል።

ብዙዎቹ አልተረፉም። ቲሞቲ ለዚህ መፅሐፍ ደራሲ፣ ለመርማሪ ጋዜጠኛው ቲም ዌይነር ሲነግረው ምን ይለዋል? – “እኔኮ የህይወቴን ሁሉነገሬን ትቼ፣ ወደ ኤጀንሲው (ወደ ሲአይኤ ማለቱ ነው); የገባሁት፣ ኤጀንሲው የራሱን ሰዎች አሳልፎ አይሰጥም፣ እሰከመጨረሻው ከጎናቸው ይቆማል፣ በማንኛውም ዋጋ ይታደጋል፣ … ብዬ አምኜ ነበረ! ሁሉም ነገር፣ ተረት ተረት እንደነበረ በአሳዛኝ መንገድ ተረዳሁት።… “ከሃዲ ብሆን ኖሮ እዚያው ኢትዮጵያ እቀር ነበር፣ እንጂ አሜሪካ አልመጣም ነበር፣ አልገባቸውም፣ በፖለቲካ ውሳኔያቸው ለመጣባቸው ቅሌት፣ እኔን ህይወቴን ሸጬ ሀገሬን ያገለገልኩትን አንድ ምስኪን ሰው፣ ዳጣ አደረጉኝና፣ አነሱ ከደሙ ነፁ..። “ያ ቅሌት የማንም ሳይሆን ሬገንን ያሳሳተው ጀብደኛው የሲአይኤ የመፈንቅለ-መንግሥት ፕሮግራም ነዳፊዎች ናቸው። ሬገን ሲአይኤ የተካነበት ሥራው ነበማለት አምኖ ፈረመ። ያንን ፕሮጀክት ያስጀመረው ጂሚ ካርተር ነበር፣ እሱ ግን በትንሽ በጀትና ጊዜ ተወስዶ በትዕግሥት እንዲፈፀም ነበር የፈለገው፣ ሬገንን ሲያገኙ ዘለው አስፈረሙት፣ እና የሆነው ሆነ፣ ድመት ልጇን እንደምትበላ፣ እኔም በገዛ ድርጅቴ ተበላሁ!” ይህን ታሪክ ስፅፍ ለአንባቢ እንደሚረዝምበት፣ ሊያሰለችም እንደሚችል አውቃለሁ። እገምታለሁ። ነገር ግን የምፅፈው ነገ የሚሆነውን ስለማናውቅ ነው። አሁን እያለን፣ ቢረዝምም ፅፈነው ለትውልድ፣ ለታሪክ አጥኚዎች፣ ከትናንቱ የውድቀታችን ምሥጢር ተምረው የነገውን ትንሣዔያችንን ማብሠር ለሚፈልጉ ወገኖቼ፣ ታሪኩ ተሰውሮ፣ ተዘንግቶ እንዳይቀር ነው የምፅፈው። (ከአሰፋ ሃይሉ  የፌስ ቡክ ገዕ የተገኘ)

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

ትስስር ይፍጠሩ

325,851FansLike
49,039FollowersFollow
13,194SubscribersSubscribe