የብአዴን ኑዛዜ በአቶ ላቀ አያሌው

ከሰሞኑ የፌዴራል የብአዴን ባለስልጣናት ስለወቅታዊ ጉዳይ ተወያይተው ነበር፡፡ ብዙዎች አይተገብሩትም እንጂ ጥሩ ሀሳብ አንስተዋል፡፡ የእያንዳቸውን ሀሳብ AMN የሚያቀርብ ሲሆን፣ የዛሬን የአቶ ላቀ አያሌውን ሀሳብ አቅርበናል፡፡
አቶ ላቀ አያሌው በስብሰባው ያነሱት የኑዛዜ ሀሳብ!!

በቅድሚያ የዛሬን መድረክ በመድፌ ቀዳዳ የመሽሎክ ያህል ቢሆንም እንድንገናኝ እድሉን ለፈቀደልንና ለአስተባበረን ሁሉ አመሰግናለሁ፡፡

በመቀጠል መግለፅ የምፈልገው እኛ የድሮው ብአዴን/አዴፓ- የአሁኑ የአማራ ብልፅግና ወኪሎች በፖለቲካው ገበያና በገበያው ሥርዓት ውስጥ እየተጎማለልን ያለን ነገር ግን ሻጭም ሆነ ሸማቾች ዋጋችን ስንት እንደሚያወጣ በድፍረት ለመግለፅ የሚቸገሩብን ስብስቦች ነን ብዬ ብናገር ማጋነን አይደለም ፡፡

ይህን የምልበት ምክንያት በወያኔ ዘመንም ሆነ አሁናዊ ሁኔታችንን በማገናዘብ ነው ። በወያኔ ዘመን እስከመጨረሻው ድረስ የወያኔ የበላይነትየለም ፀረ-ኢትዮጵያ አቋም ያላቸው፤ ሀገር ለማፍረስ የሚያካሂዱት ዘመቻ ነው በማለት ከትህነግ በላይ ትህነግ ሆነን ስንከራከር ኖረን መጨረሻ ጥለውን ሄዱ፡፡ በእርግጥ መንከስ የሚችለው ጥርሳቸው ከወለቀ በኋላ ብዙ…. ብለናል ይህን አልክድም ፡፡
እኛ ከትህነግ በላይ ትህነግ ሁነን የህዝባችንን አንገት ስናስደፋ በማናውቀው ነገር ሁሉ ያዙኝ ልቀቁኝ ስንል ኑረናል ።

ነገር ግን ህዝባችን ቀድሞ ተረድቶ፡-
1. ንብረት ወደ ትግራይ እየተጓዘ ነው፤
2. መሠረት ልማት ፍትሐዊ አይደለም፤
3. በጀት ድልድሉ ኢ-ፍትሀዊ ነው፤
4. መሬታችንና ህዝባችን እየተወሰደ ነው፤
5. በመላ ሀገሪቱ የተመዛባ ትርክት ስለአማራ እየተነገረ ነው፤
6. የፌደራል ተቋማት በወያኔ አምሳል እየተቀረፀ ነው፤
7. አማራ የሚተዳደረው በትገራይ እና በኤርትራ ሰዎች ከእኛ ሰው ጠፍቶ ነው ወይ ??
8. እጅግ በጣም አሰቃቂ የሆነ የሰብዓዊና የዴሞክራሲያዊ መብቶች ጥሰት እየተፈፀመ ነው፤
… ወዘተ እየተባለ በህዝቡም ሆነ በብአዴን አባላት የማይነሳ አልነበረም፡፡ ነገር ግን የትህነግ ወኪሎችና የእነሱ ዙፋን አስጠባቂዎች ይህ የትምክህትና የጠባብነት አስተሳሰብ ነው ሲሉን እኛም ይህን ሳናላምጥ በመዋጥ በተራችን ወደ አርሶ አደሩ እየሄድን ከመሬቱና ከበሬዎች እንዲሁም ከጎጆው ውጭ የማያውቅን አርሶ አደር ትምክህትና ጠባብነት የሀገራችን ቀንደኛ ጠላቶች ናቸው እንለው ነበር፡፡

አንዳንዴም ብሔርን እንደቁሳቁስ በመቁጠር አንዱን እሳት ሌላውን ጭድ በማድረግ ቢገናኙ የሚቀጣጠሉ ነገር ግን ሀገር ለመበተን ሲሉ አንድ የሚሆኑ የፀረ-ዲሞክራሲ መገለጫዎች ሀገር አፍራሽ ናቸው በማለት እንድናወግዝ እየተነገረን እኛም ህዝብን እያደነቆርን መሄጃ አሳጥተን በትህነግ የፖለቲካ ገበያ ውስጥ አልፈን ብልፅግና ገበያ ደርሰናል ፡፡
ይህን የማነሳው ያለፈውን እያነሳሁ ጊዜ ለማጥፋት አይደለም ፡፡ ህዝቡ ከፖለቲከኞችና ከወኪሎች በተሻለ መንገድ ተገንዝቦ ሲነግረን ጆሯችን ድፍን እንደነበረ መለስ ብለን እንድናስታውስና ለዛሬም ትምህርት እንዲሆነን ለማስገንዘብ ነው፡፡

በብልፅግና የፖለቲካ ገብያስ አቶ ላቀ አያሌው ቀጥለዋል፡፡
***************************
በእኔ አስተሳሰብ በዛሬው የፖለቲካ ገበያም ህዝባችንን ሊጠቅም የሚችል በፖለቲካው ገበያ ላይ ዋጋ እያወጣን አይደለም ፡፡ ይህን የምልበት ምክንያት፡-
1. ያለፉት 46 ዓመታት ትህነግ መራሽ ሰቆቃ አልበቃ ብሎ ከለውጡ ማግስት ጀምሮ የአማራ ህዝብ በብዙ አካባቢዎች በማንነቱ ምክንያት ብቻ የዘር ማጥፋት ጭፍጨፋ እየተፈፀመበትና ሀብት ንብረቱ እየወደመበት ስለሆነ ነው ።
ለምሳሌ፡-
 በመተከል ዞን በተደጋጋሚ
 በማይካድራ
 በኦሮምያ ክልል በተለያዩ ወቅቶችና ቦታዎች
 በጉራ ፈርዳ —- ወዘተ

ይህ ሁሉ ማንነትንና እምነትን ብቻ ማዕከል ያደረገ የዘር ማጥፋት ወንጀል ሲፈጸም ከወንጀሉ ክብደትና ዓለም አቀፋዊነት አንፃር ሁሉም የብልፅግና አባላት ማውገዝ ነበረብን፡፡ ነገር ግን የአህያ ባል ከጅብ አያስጥልም ሆነና ነገሩ የዘር ማጥፍቱ ተጠናክሮ ቀጥሏል፡፡
2. ማንነትንና ዘርን መሠረት ተደርጎ የሚፈፀመውን የዘር ማጥፋት ወንጀል እኛ የአማራ ህዝብ ወኪሎች ነን የምንል ሁሉ የዘር ፍጅቱን ልንከላከለው ይቅርና አጀንዳ አድርገን ጠንከር ያለ ተመሳሳይ አቋም እንኳን መያዝ አልቻልንም ፡፡ እንዲያውም የሰብዓዊ መብት ኮሚሽን ከእኛ በእጅጉ የተሻለ ሁኗል፡፡

3. በተደጋጋሚ በአማራ ህዝብ ላይ የዘር ማጥፋት ሲፈፀም በአማራ ክልል ም/ቤትም ሆነ በፌደራል የህዝብ ተወካዮች ም/ቤት ወንጀሉን በሥሙ ጠርተው የዘር ማጥፋት (Genocide) ወንጀል መፈፀሙን ተቀብለው አቋም ሊወስዱ ይቅርና ብሔራዊ የሀዘን ቀን እንኳን ማወጅ አልቻሉም፡፡ይህ መሆኑ የእነርሱ ጥፉት ሳይሆን የእኛ የፖለቲከኞቹ ግዴለሽነት ነው ።

4. በየቦታው የዘር ማጥፋትና የዘር ማፅዳት እየተፈፀመባቸው ያሉትን ወገኖቻችንን ከአሰቃቂ ግድያ ባንታደጋቸውም እንኳን በማህበረሰባችን ባህልና ወግ መሠረት በክብር ግብዓተ መሬታቸው እንዲፈፀም ማድረግ ሲገባን ከውሻ ሞት በአነሰ መንገድ የቀብር ጉድጓድ በዶዘር እየተቆፈረ፣ አስከሬን ከየጫካው እየተለቀመና እንደ ቆሻሻ በቡል ዶዘር እየተዛቀ ከኢትዮጵያውያን ባህልና እምነት ውጭ አንዱ በአንዱ ላይ ተደራርቦ ጉድጓድ ውስጥ እንዲገባ ተደረገ፡፡ እውነት የህዝቡ ወኪሎች ከሆን ሞታቸውን ማዳን ባንችል እንኳን ቢያንስ የሟቾችን አስከሬን እንዴት በክብር ማሳረፍ አቃተን? ይህንስ ምን እንበለው?

5. እንደሚታወቀው ማነኛውም ሰው በህይወት የመኖር፣ የአካል ደህንነትና የነጻነት መብት አለው በሚል በሕገ መንግሥቱ በአንቀፅ 14፣ 15ና 16 ተቀምጧል፡፡ ነገር ግን ሕገ መንግሥቱ ለአማራ ህዝብ ሲሆን እየተተገበረ አይደለም፡፡ ነገር ግን እኛ የአማራ ወኪሎችም በዚህ ጉዳይ ምንም እያልን አይደለም፡፡ ሲሆን በእኛ ጀማሪነት ሁሉም ክልል ህገ መንግስት ተጥሷል እንዲል ማድረግ ነበረብን ምልናያቱም እውነት ነዋ ።

6. እኔ እስከገባኝ ድረስ ብልፅግና ማለት በመላ ኢትዮጵያ ያሉ የብልፅግና አመራሮችንና አባሎችን በጋራ እየገመገምንና እየተራረምን እንመራለን ብዬ አስብ ነበር፡፡ ነገር ግን ዛሬም በየክልሎች ህዝብና መንግሥት የሰጣቸውን ኃላፊነት በመተው ህዝብን እንደ በግ የሚያሳርዱ፣ ለሰብዓዊነትና ለሰው ልጅ ቅንጣት ያህል ክብር የማይሰጡ፤ የሚመሩት ክልል የደም መሬት ሲሆን የማይደነግጡ አካላትን መገምገምና ከኃላፊነት ማንሳት ቀርቶ ቀና ብለን ማየት አልተፈቀደልንም፡፡ ይባስ ብሎ እኛ ሳንፈቅድላችሁ በማህበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ሀዘናችሁን እንኳን አትጻፉ እንዲሁም በመገናኛ ብዙኃን አትናገሩ ተባልን፡፡ ታዲያ የእኛ በዚህ የብልፅግናም የፖለቲካ ገበያ ውስጥ ዋጋ እያወጣን ነው ብዬ እንዳላስብ እየተገደድሁ ነው፡፡

7. በሕገ መንግሥቱ አንቀፅ 39 (3) የኢትዮጵያ ብሔር፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች በክልልና በፌደራል አስተዳደሮች ውስጥ ራሳቸውን በራሳቸው ማስተዳደር እንዲሁም መኖር ብቻ ሳይሆን ሚዛናዊ ውክልና የማግኘት መብት እንዳላቸው ይደነግጋል፡፡ ይህ ሕገ መንግሥት ደግሞ የሕጎች ሁሉ የበላይ ነው፡፡ ነገር ግን ይህ የሕጎች ሁሉ የበላይ የሆነው ሕገ መንግሥት ተጥሶ ከአማራ ክልል ውጭ የሚኖሩ አማራዎች በየትኛውም የአስተዳደር እርከን ውክልና የላቸውም፣ በአፍ መፍቻ ቋንቋቸውም አይዳኙም፣ አይማሩም፣ አይተዳደሩም፡፡ ታዲያ እኛ ምን እየሰራን ነው?

8 .ማነኛውም ኢትዮጵያዊ በፈለገው ቦታ የመኖር፣ የመንቀሳቀስና የግል ንብረት ባለቤት የመሆን መብት እንዳለው እንዲሁ በሕገ መንግሥቱ ተደንግጓል፡፡ ነገር ግን አማራ ኢትዮጵያውያን አማራ በመሆናቸው ብቻ በኦሮምያ ክልልና በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል እራሳቸውን ከተደራጀ ጥቃት ለመከላል መሳሪያ እንዲይዙ አይፈቀድም፡፡ ሌሎች ብሔሮች ግን አይከለከሉም፡፡ እኛ በጥቅሉ ሕገ መንግሥቱ ይቀየር እንላለን እንጂ ሕገ መንግሥቱ ላይ በግልፅ የተቀመጡት ድንጋጌዎች እንኳን አማራ ላይ ሲሆን ተግባራዊ እየተደረጉ አይደለም፡፡
9 . በብልጽግና ውስጥ መግባታችን ለመሆኑ አማራ ምን ያህል እኩል ተጠቃሚ እየሆነ ነው? ዛሬ የመናገር ነፃነት፣ የመፃፍ ነፃነት፣ ሰላማዊ ሰልፍ የማድረግ ነፃነት ምን ያህል በተግባር ለህዝባችን ተረጋግጠዋል፡፡ እንኳን ህዝባችን እኛ ምን ያህል ነጻ ነን? ልክ እንደ አሳለፍነው ትህነግ/ሕወሓት መራሹ ኢህአዴግ ዛሬም በብልፅግና የሚቀጥል ይመስለኛል፡፡ እኛስ ይህንን ለማረም ምን ያህል ቁርጠኛ ነን? ይህንን ለማረምስ በተደራጀ መንገድ ምን ያህል እየታገልን ነው የሚል ጥያቄ አንስተን በሰፊው መገምገም ይገባናል እላለሁ፡፡ እኛ በዕቅድ እና በጀትና ሰው ተመድቦ በንቃት በአውራጃ እና በጎጥ እንድንከፉፈል እየተደረገ አይደለም ወይ ?? እኛስ ይህን እንደመሸሸጊያ እየተጠቀምንበት አይደም ወይ ?? በተለይ ነባሮችና ትልልቆች ይህ ክፍፍል እንዲኖር አትፈልጉም ወይ ይቅታ ግምት ነው ምክናያቱም ለምን አንድ እንድንሆን አታደርጉም ጥፉተኛንስ ለምን እርምጃ እትወስዱም መነሻዪ ይህን ለማለት ነው :::

10. አሁን እንደ ብልፅግና የምንመራበት የተረቀቀው ሕገ ደንብና ፕሮግራም ሚዛን የሚያስጠብቅና ስህተትን ለማረም የሚያስችል አይደለም፡፡ በአጭሩ check and balance የለውም፡፡ ሁሉንም ነገር ጠቅልሎ ለፓርቲው ፕሬዝዳንት የሚሰጥና ጥቅል ማዕከላዊነትን የሚያሰፍን ነው፡፡ ለምሳሌ ሚኒሰቴሮች ሲሾሙም ሆነ ከሹመት ሲነሱ የብልፅግና ሥራ አስፈፃሚ አባላት እውቅና የላቸውም፡፡ የፓረቲው ሥራ አስፈጻሚ አባላት እንደማነኛውም ዜጋ ከመገናኛ ብዙኃን ነው የሚሰሙት፤ መገናኛ ብዙኃንን የማይከታተሉ ከሆነ ደግሞ ጭራሹንም አይሰሙም፡፡ ሌላው ኃላፊ ደብዳቤ ይዞ ሲመጣ ብቻ ነው የሚያውቀው፡፡
ለምሳሌ፡- የአቶ ደመቀ መኮነን፣
የአቶ ገዱንና የሌሎችን ሹመት የሰማነው ከመገናኛ ብዙኃን ነው፡፡

11. የፖለቲካ መታገያ ሜዳ እጅግ በጣም የጠበበ ነው፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ ተጋፍጠን እየታገልን አይደለም፡፡ እኛ ሲበዛ ይሉኝታ፣ አድርባይነትና ዘገምተኝነት እያጠጠቃን ነው፤ ወይንም እኛ የእነዚህ ስብዕናዎች ባሪያ ሆነናል፡፡ ይህ ደግሞ ከነባራዊው የፖለቲካ አሰላለፍ አንጻር እጅግ ተቃራኒ ስለሆነ ከትግል ሜዳው እያስወጣን ነው፡፡ የሀገራችን አርሶ አደር የማይጠቅምን ሰው ሲሳደብ “በዋለበት የሚያድር፣ እርባና ቢስ፣ ሰው የዋለበት” ይላል፡፡ ይህ አባባል እኛን በጥሩ ሁኔታ የሚገልፅ ይመስለኛል፡፡ ምክንያቱም ከትላንቱ አልተማርንምና ነው፡፡ በተለይ ነባር አመራሮች (አቶ ደመቀ መኮነን፣ አቶ ገዱ አንዳርጋቸው፣ አቶ ብናልፍ አንዷለም፣ አቶ ተፈራ ደርበው:: የስም ዝርዝሩን የጨመርነው እኛ ነን፡፡ ነባር የሚባሉት እነሱ ስለሆኑ፡፡)
የኢህአዴግ ሥራ አስፈፃሚ ነበራችሁ፤ አሁንም በብልፅግና አላችሁ፡፡ ሌሎቻችን እንኳ ለውጡ ያመጣን ወፍዘራሾች ነን፡፡ ለምን ዛሬ እንኳን ታግላችሁ አታታግሉንም? እናንተ ነባር ናችሁ፤ ዛሬም ህዝባችሁን ለመታደግ ከሚያስችል ቦታ ላይ ናችሁ፡፡ ምንድን ነው ችግሩ? ወይስ እኛ አዲሶቹ የማንረዳው ችግር ይኖር ይሆን? ይህንን የምለው ለአማራ ህዝብ ብቻ በማስብ ሳይሆን ለሁሉም ኢትዮጵያውያንና ለሁሉም የሰው ልጅ እኩልነት መታገል ያለብን ሰለሆነ ነው፡፡
ለማጠቃለል ያህል፡-
 ከትላንት የማንማር፤
 ለህዝብ ሰቆቃና ብሶት የማንገበገብ፤
 የወከልነው ህዝብ መነካት የለበትም ብለን ለመናገር አንደበታችን የሚተሳሰር፤
 የፖለቲካውን ገበያ ተቆጣጥረን በገበየው ሥርዓት ውስጥ ሁሌ የምንገኝ ተራ እንኳ የማንሰጥ ነገር ግን በየትኛውም አካል ጎን ስንት ዋጋ እንደምናወጣ የማንገመት ሚዛነ ቀላል የድኩማኖች ስብስብ መሆናችንን አምነን ካልተቀበልን በፍፁም ለውጥ አናመጣም ብቻ ሳይሆን የዛሬውንም ሆነ የመጪውን ትውልድ
ተስፉየለሽ እናደርገዋለን ።
እመኑኝ አትጠራጠሩ ለሌላ 50 አመታት ህዝባችንን ለባሰ ሰቆቋ እንዳርገዋለን ።

አመሰግናለሁ
በመናገሬ ቢያንስ ትንሽ ያልፍልኛል ብየ ነው፡፡ እኔ ቦታየ የፖለቲካ ሳይሆን የሙያ ነው፡፡ ግን የሚቻለኝን አደርጋለሁ፡፡

አቶ ላቀ አያሌው ጥር 5 ፣ 2013 ዓ.ም
አዲስ አበባ ኢትዮጵያ

Kumneger Media
Kumneger Media
Kumneger Media is a News and Entertainment Website & Channel. Kumneger Media in addition to News and Entertainment it is the hub of Politics, Movies, Drama, Music, Comedy, Documentary and More!

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

ትስስር ይፍጠሩ

325,851FansLike
49,039FollowersFollow
13,194SubscribersSubscribe