የፌዴራል የገቢ ግብር አዋጅን ለማሻሻል በቀረበው ረቂቅ አዋጅ ላይ፣ የኑሮ ውድነትን ታሳቢ በማድረግ የገቢ ግብር መነሻ ገቢ ከ2,000 ብር ወደ 5,000 ብር ከፍ እንዲል ጠንካራ ጥያቄ ቀርቧል።
ጥያቄው የቀረበው የፌዴራል የገቢ ግብር አዋጅን ለማሻሻል በቀረበው ረቂቅ አዋጅ ላይ በፓርላማው የፕላን፣ በጀትና ፋይናንስ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ዛሬ ባደረገዉ ዉይይት ላይ ነው።
በአሁኑ ረቂቅ አዋጅ መሰረት፣ ከ2,000 ብር በላይ በሚገኝ ገቢ ላይ 15 በመቶ ግብር እንዲከፈል የሚለው ሀሳብ ቀርቧል።
ይህ የገቢ ግብር አዋጅ ከዘጠኝ ዓመታት በላይ ስራ ላይ መዋሉ የተገለጸ ሲሆን፣ አሁን በማሻሻያው ከግብር ነፃ የሚሆነው ከመቀጠር የሚገኝ ገቢ በ300% በማሳደግ ወደ 2,000 ብር ከፍ እንዲል ተደርጓል።
በተጨማሪም፣ ከፍተኛው የማስከፈያ መጣኔ የሆነው 35% ግብር የሚያርፍበት ገቢ ደግሞ ወደ 14,000 ብር ከፍ እንዲል ሆኗል።
የቋሚ ኮሚቴው ሰብሳቢ አቶ ደሳለኝ ወዳጄ፣ የአዋጁ መሻሻል መንግስት ግብር በመሰብሰብ የህዝቡን የልማት ጥያቄዎች ለመመለስ እንደሚረዳ ገልጸዋል።
ከግብር ከፋዩ ህብረተሰብ የሚነሱ ” ግብር በዝቷል ይቀነስ ” የሚሉ ሀሳቦች ሚዛናዊ በሆነ መልኩ እንደሚታዩም አክለዋል።
በውይይት መድረኩ ከተነሱት አስተያየቶች መካከል፣፦
– የገቢ ግብር መነሻው ከአምስት ሺህ ብር ጀምሮ እንዲሆን፣
– ለአካል ጉዳተኞች በተለየ መልኩ ግብር እንዲቀነስ፣
– በተለያዩ የሙያና የንግድ ዘርፎች አንፃር በደንብ እንዲታይ የሚሉ ሀሳቦች ቀርበዋል።

