ከ 17 ዓመት በፊት ልክ መስከረም 8 ቀን 2001 ዓ.ም በዛሬዋ ቀን ባለ ዘርፍ ብዙ ባለሙያ አርቲስት ሲራክ ታደሰ ባደረበት ሕመም በሕክምና ሲረዳ ቆይቶው በተወለደ በ 62 ዓመቱ ከዚህ ዓለም በሞት የተለየበት ዕለት ነበር።
አርቲስት ሲራክ ታደሰ የግጥምና ዜማ ደራሲ ፣ የመድረክ ቲያትር ተዋንያን ፣ ብዙ የቴሌቭዥን እና የሬዲዮ ድራማዎችን እንዲሁም ፊልሞች የሠራ አንጋፋና ባለብዙ ዘርፍ ባለሙያ ተወዳጅ አርቲስት ነበር አርቲስት ሲራክ ታደሰ።
የተወለደው በ 1939 ዓ.ም በወሎ ክፍለ ሀገር በዋድላ ደላንታ አውራጃ ልዩ ስሙ ወገል ጤና በተባለ ቦታ ነው። እድሜው ለትምህርት ሲደርስ በሀገሩና ባህል መሠረት የቤተ ክህነት ትምህርት ዜማና ቅኔ ፣ ድጓና ጾመ ድጓ ከአቋቋም ጋር የቤተክርስቲያን አብነት የሆነውን ያሬዳዊ ዜማ ተምሮ ጨርሷል።
ሲራክ ወደ አዲስ አበባ ጠፍቶ በመምጣት በግቢ ገብርኤል ሲያገልግል ቆይቶ ከዚያ በኋላ በምድር ጦር የሙዚቃ ክፍል በግጥምና ዜማ ደራሲነት በ 1959 ዓ.ም ተቀጠረ። በምድር ጦር በቆየበት አስር ዓመታት ለክፍሉም ሆነ ከክፍሉ ውጭ ላሉ በርካታ ድምጻውያን የግጥምና ዜማ ድርሰቶችን ሠርቷል። ከነዚህም ውስጥ ጥቂቶቹ…
➺ ለጥላሁን ገሰሰ
➺ ለመሀሙድ አህመድ
➺ ለዓለማየሁ እሸቴ
➺ ለኃብታሙ ሽፈራው
➺ ለታምራት ሞላ
➺ ለአባይ በለጠ
➺ ለፀዳለ ገ/ማርያም
➺ ለገሰ ቀናው…… ግጥምና ዜማዎች ደርሷል።
ሲራክ ምድር ጦር እያለ በብሔራዊ ቲያትር የሚሰጠውን የእጩ ተዋንያን ኮርስ በመውሰድ በ1969 ዓ.ም በብሔራዊ ቲያትር ተቀጠረ። በብሔራዊ ቲያትር በርካታ ቲያትሮችን የተጫወተ ሲሆን በርካታ ግጥሞችና ዜማዎችም ደርሷል።
ከተጫወተባቸው ቲያትሮች በጥቂቱ…..
➺ ሀሁ በስድስት ወር
➺ እናት ዓለም ጠኑ
➺ የአዛውንቶች ክበብ
➺ አምታታው በከተማ
➺ በቀይ ካባ ስውር ደባ
➺ አሉላ አባነጋ
➺ የአመፃ ልጆች
➺ ነፃ ወንጀለኞች
➺ መርዛማ ጥላ
➺ እርጉም ሐዋርያ
➺ ሻጥር በየፈርጁ
➺ ተሀድሶ
➺ ዋዜማ
➺የክት ነሽ (በVCD የተቀረጸ)….ጥቂቶቹ ናቸው።
የአርቲስት ሲራክ ታደሰ አሻራዎች ካረፉባቸው ድንቅና ዘመን አይሽሬ ዜማዎች ውስጥ ጥቂቶቹ…
⩩ ለጥላሁን ገሰሰ
➺ ትንፋሼ ተቀርጾ…ግጥም
➺ የኔ ሸበላ………..ግጥም
➺ አይ ዘመን ጊዜ…ግጥም
⩩ ለመሐሙድ አህመድ
➺ አልማዝ እንቁ መሳይ……………ግጥም
➺ ዓለም ዓለም ምን ይመስልሻል…ግጥም
⩩ ለታምራት ሞላ
➺ ማን ነበር…ግጥም
➺ ስንዋደድ…ግጥም
⩩ ለዓለማየሁ እሸቴ
➺ ምንድነው ፈገግታ….ግጥም..
⩩ ለመልካሙ ተበጀ ከዚህ በታች ላሉት በሙሉ ግጥምና ዜማ
➺ ኧረ መላ ምቱ
➺ ቸብ ቸብ አርጉላት
➺ ማሜ ገላ
➺ ፎቶሽ ይናፍቃል
➺ በቀን አስር ጊዜ
➺ አንቺን ነው
➺ እሷ እኔን እያለች
* ስቀርብሽ አትራቂ
⩩ ለፍቅር አዲስ ነቃጥበብ
➺ ሳብ በለው…ግጥም
➺ አትርሳኝ…….ግጥም
➺ ያነቃል……….ግጥም
⩩ ለጌራ ወርቅ ነቃጥበብ
➺ አመጣኝ መውደድሽ……ግጥም
የአርቲስት ሲራክ ታደሰ አሻራዎች ካረፉባቸው ድንቅ ሥራዎቹ ውስጥ ጥቂቶቹ ናቸው።
አርቲስት ሲራክ በብዙ የሬዲዮና የቴሌቭዥን ድራማዎች ውስጥም ተጫውቷል። ከእነዚህ ውስጥም በጋዜጠኛ ታደሰ ሙሉነህ የተደረሰው “የደሞዝ ሰሞን” የሬዲዮ ድራማ ተጠቃሽ ነው።
አርቲስት ሲራክ ታደሰ ከ 1959 እስከ 1969 ዓ.ም በምድር ጦር የሙዚቃ ክፍል ከ 1969 ዓ.ም ጡረታ እስከወጣበት 1997 ዓ.ም ድረስ በብሔራዊ ቲያትር እንደተወደደ እና እንደተከበረ በቅንነት ያለውን ሙያ ሳይደብቅና ሳይሰስት አገልግሏል። ሲራክ ሙያውን አክባሪና ወዳጅ እሱም ተወዳጅ እንደነበር በሙያ አጋራቹ ይነገርታል የጡረታ መውጫው ለአምስት ዓመት የተራዘመውም በሙያው ምን ያህል ተወዳጅ እንደነበር ማሳያ ነው።
አርቲስት ሲራክ ታደሰ በአደረበት ሕመም በሕክምና ሲረዳ ቆይቶ መስከረም 8 ቀን 2001 ዓ.ም በተወለደ በ 62 ዓመቱ ከዚህ ዓለም በሞት ተለይቷል የቀብር ሥነ ሥርዓቱም ወዳጅ ዘመዶቹ ፣ ቤተሰቦቹ ፣ አድናቂዎቹና ጓደኞቹ በተገኙበት በወይብላ ማርያም ተፈጽሟል።
አርቲስት ሲራክ ባለትዳርና የሁለት ሴትና የሦስት ወንዶች ልጆች አባት ነበር። እርሱ ቢያልፍም ጥሎልን ባለፈው ጊዜ በማይሽራቸው ሥራዎቹ ሲታወስ ይኖራል።

