በየመን የሑቲ ታጣቂዎች ፍርድ ቤት የአሜሪካውን ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕንና የሳኡዲውን ልዑል መሐመድ ቢን ሳልማንን በሌሉበት ሞት ፈረደውባቸዋል።
ፍርድ ቤቱ በነዶናልድ ትራምፕ መዝገብ ተከሰው የነበሩ ዘጠኝ ሰዎች ከትናንት በስቲያ በአደባባይ በሞት ቀጥቷቸዋል፡፡በሞት ከተቀጡት ዘጠኝ ሰዎች መሀል በሚያዝበት ወቅት አዳጊ የነበረ አንድ ልጅ ይገኝበታል፡፡
በሰንዓ አደባባይ ላይ በመቺ ኃይል ከጀርባ እየተተኮሰባቸው እንዲገደሉ የተደረጉት ዘጠኝ የመናዊያን በ2018 አንድ ከፍተኛ የሑቲ አመራርን በሳኡዲ መራሹ ኃይል የአየር ጥቃት እንዲገደል መረጃ አቀብላችኋል በሚል ጥፋተኛ ተብለው የተፈረደባቸው ናቸው፡፡
7ኛው ተከሳሽ የሳኡዲው ልኡል መሐመድ ቢን ሰልማን እና የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ በሌሉበት ሞት ተፈርዶባቸዋል፡፡9ኙ ሰዎች የተገደሉት በሰንአ ታህሪር አደባባይ ሕዝብ በተሰበሰበበት ነበር፡፡
ተመድ ይህን የአደባባይ ግድያ በጥብቅ ያወገዘ ሲሆን አሜሪካ ፣ ዩኬ ፣ እንዲሁም የአውሮጳ ኅብረት ድርጊቱን ኮንነዋል፡፡
ተመድ የፍርድ ሂደቱ ዓለም አቀፍ ደረጃን የማያሟላ ነበር ሲል ፤ አሜሪካ ደግሞ የተፈፀመድን ድርጊት አሳፋሪ ብላዋለች፤ የአውሮጳ ኅብረት በበኩሉ ቅጣቱ ኢሰብአዊና ነውረኛ ብሎታል፡፡

