ዶናልድ ትራምፕ የኦሃዮ ግዛቱን ጄዲ ቫንስን እጩ ምክትል ፕሬዝዳንት አደረጉ

ዶናልድ ትራምፕ ለ2024 ፕሬዝዳንታዊ የምርጫ ውድድር ለምክትል ፕሬዝዳንትነት የኦሃዮ ግዛቱን ጄዲ ቫንስን እጩ አድርገው አቅርበዋል።
የትራምፕ አዲሱ ዕጩ ምክትል ፕሬዝዳንት ምርጫ ግን በአውሮፓ ሕብረትና በዩክሬን ዘንድ ትልቅ ስጋትና ጭንቀት መፍጠሩ እየተሰማ ነው።
ሴናተር ቫንስ በሩሲያ-ዩክሬን ጉዳይ ያላቸውን አቋም ገና ከጦርነቱ ዋዜማ ጀምሮ ሲያንጸባርቁ ነበር። ጦርነቱ ከመጀመሩ ከአንድ ቀን በፊት በአንድ ፖድካስት ላይ በሰጡት አስተያዬት “በዩክሬን የሚካሄደው ጦርነት ባንድም በሌላም መንገድ ጉዳዬ አይደለም” ሲሉ ነበር የተናገሩት።
ጦርነቱ ከተጀመረ በኋላ አሜሪካ ለዩክሬን ልትሰጥ ያዘጋጀችውን የ60 ቢሊዮን ዶላር የጦር መሳሪያ እርዳታ በሴኔቱ እንዳይጸድቅ ከፍተኛ ጫናና ማግባባት በማድረግ ቁልፍ ሚና ተጫውተዋል።
አውሮፓ ሕብረት በቀደመው የፕሬዝዳንትነት ዘመናቸው ከሕብረት ጋር የንግድ ጦርነት ውስጥ የነበሩትና የማይገመት አቋም ያላቸው ዶናልድ ትራምፕ ፕሬዝዳንት ሆነው ለመመረጥ የሚያስችል ሁኔታ ላይ መሆናቸውን የተረዳ ይመስላሉ።
ምክትላቸው ማንም ይሁን ዶናልድ ትራምፕ ለሁለተኛ ዙር ፕሬዝዳንት ሆነው መመረጥ ምን ማለት እንደሆነ ጠንቅቀን እንረዳለን ያሉት አንድ የአውሮፓ ሕብረት ዲፕሎማት መጭው ጊዜ አስቸጋሪ እንደሚሆን ግምታቸውን አስቀምጠዋል።
ትራምፕ ወደ አሜሪካ በሚገቡ የአውሮፓ የብረትና ሌሎች ምርቶች ላይ የ10 በመቶ ታሪፍ ጥለው እንደነበር የሚታወስ ሲሆን አሁንም ሌላ ዙር የንግድ ጦርነት ይከፍታሉ የሚል ስጋት ተፈጥሯል።
ከዚህ ባሻገር የኔቶ አባል አገራት ለተቋሙ የሚጠበቅባቸውን በጀት ካላዋጡ አሜሪካ አባልነቷን እንደገና እንደምታጤነው ሲያስፈራሩ እንደነበር ይታወቃል።
በዚህ ሁኔታ ላይ ነው እንግዲህ ትራምፕ የተናጥልነት (isolationist) መርህ የሚያቀነቅኑ አዲሱ ምክትል ፕሬዝዳንታቸውን ያስታወቁት። አዲሱ ዕጩ ምክትል ፕሬዝዳንት በባይደን አገዛዝ የተሻለ የነበረውን የትራንስ አትላንቲክ ትብብር አደጋ ላይ እንዳይጥለው በአውሮፓዊያን ዘንድ ስጋት ፈጥሯል።
የሩሲያ – ዩክሬን ጦርነት እንዳይፈጠር ማድረግ እችል ነበር ያሉት ዶናልድ ትራምፕ አሁንም ከተመረጡ በቀናት ውስጥ ጦርነቱን እንደሚያስቆሙትና ሰላም እንደሚያሰፍኑ ተናግረዋል።
ይህን ደግሞ የትራምፕ ወዳጅ የሆኑት የሀንጋሪው ጠቅላይ ሚኒስትር ቪክቶር ኦርባን ለህብረቱ በጻፉት ደብዳቤ ትራምፕ በሩሲያና ዩክሬን መካከል የሰላም ድርድር ለማድረግ ዝርዝርና በሚገባ የተዘጋጀ ዕቅድ እንዳላቸው መግለጻቸውን ቢቢሲ ዘግቧል።
የአውሮፓ ሕብረትና የሕብረቱ አባል አገራት የሰላም ድርድር ሩሲያን አሸናፊ እንደሚያደርጋትና ወደፊትም ለአህጉሩ ስጋት ሆና ትቀጥላለች የሚል ስጋት አላቸው።
የአባል አገራቱ ፍላጎት ሩሲያ በጦርነቱ እንድትሸነፍ እና ሁሉም የሕብረቱ አባል አገራትና ወዳጆች ለዩክሬን እርዳታ መላክ እንዲቀጥሉ ነው።

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

ትስስር ይፍጠሩ

325,851FansLike
49,039FollowersFollow
13,194SubscribersSubscribe