ከተመሠረተ 15 ዓመታትን የተሻገረው ኃይሌ ሆቴሎች እና ሪዞርቶች ግሩፕ አስረኛውን መዳረሻ ባለ 4 ኮከብ ሆቴል በጅማ ከተማ አገልግሎት መስጠት መጀመሩን በዛሬው እለት አብስሯል።
በጅማ ከተማ የተገነባው 1.7 ቢሊዮን ብር በላይ ወጪ የወጣበት ባለ 4 ኮከብ ኃይሌ ሆቴል ጅማ በይፋ ስራ መጀመሩን አስመልክቶ ዛሬ ታህሳስ 24 ቀን 2017 ዓ.ም በሆቴሉ ጊቤ አዳራሽ ለመገናኛ ብዙሃን ባለሙያዎች መግለጫ ተሰጥቷል።
በጋዜጣዊ መግለጫው መርሐግብር ላይ ሻለቃ ኃይሌ ገብረሥላሴ እንደገለጹት ለጅማ እና አካባቢው ዘርፈ ብዙ ትርጉም ያለው አስረኛው መዳረሻችንን የሆነውን ኃይሌ ሆቴል ጅማ ስንከፍት ታላቅ ደስታ ይሰማናል ብሏል
የሀይሌ ሆቴልና ሪዞርቶች ዋና ስራ አስኪያጅ የሆኑት አቶ ጋዲሳ ግርማ እንደገለፁት ኃይሌ ሪዞርት ጅማ የተለያየ አይነትና ስፋት ያላቸዉ
ከ106 ዘመናዊ አገልግሎት የተሟላላችዉ እና በተለያዩ መጠን እና ደረጃ የሚገኙ የመኝታ ክፍሎች ፣ 2 ለቪአይፒ እንግዶች አገልግሎት የሚሰጡ ቪላዎች ፣ 5 የኦዲዮ ቪዥዋል መሳሪያዎች የተሟሉላቸዉ የስብሰባ አዳራሾች ፣
4 ዘመናዊ እና ባህላዊ ምግቦችን የሚያቀርቡ ሬስቶራንቶች እና ለመዝናናትም ሆነ ጤንነትን ለመጠበቅ የሚያስችሉ የመዋኛ ገንዳ ፣ጂምናዚየም፤ የስፓ፤የስቲም ባዝ፣ ሳዉና ባዝ ፤ ሞሮኮ ባዝ እና የውበት ማዕከላት እንዳሉት ተናግረዋል፡፡
ከ206 በላይ ለሚሆኑ የአካባቢው ነዋሪዎች የስራ እድል እንደፈጠረ የተገለፀ ሲሆን ወደፊት 400 ለሚደርሱ ሰዎች የስራ እድል እንደሚፈጥር ተገልጿል
በስራ ማስጀመሪያ መርሐግብሩ ላይ ተገኝተው ንግግር ያደረጉት የጅማ ከተማ ከንቲባ ጣሀ ቀመር የቱሪስት መዳረሻ እየሆነች ባለችው በጅማ ከተማ ላይ ከፍተኛ መዋለ ንዋይ በማፍሰስ ሪዞርት በመገንባት አስተዋጽኦ ያበረከተውን ሻለቃ ኃይሌ ገብረሥላሴ እና ቤተሰቦቹን አመስግነዋል።
በተጨማሪም የጅማ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ኢጃሌ ናስር እንዳሉት ሆቴሉ የአባጅፋርን ታሪክን በማስታወስ በውስጡ ላካትተው ታሪካዊ ቅርስ ምስጋና ይገባዋል ብለዋል።

