ማንኛውም በትዳር ውስጥ ያለ ሰው ለትዳሩ ታማኝ እንደሚሆንና ከአጋሩ ጋር አብሮ መኖር ከጀመረ በኋላ ለሁለትዮሽ ደስታ የድርሻውን የሚያበረክት መሆኑን ገና በሠርጉ የመጀመርያ ዕለት በሚገባው ቃል ይገልጻል፡፡ ይህ ብቻም አይደል፡፡ ትዳር በየጊዜው ልናስታውሳቸው የሚገቡና አብሮነታችን ጥንካሬ ኖሮት እንዲዘልቅ የሚያግዙ ቅመማት ያሉት መኾኑን ማስታወስም ተገቢ ነው፡፡ ከእነኚህ ቅመማት መካከል ሦስቱን በአጭሩ ለማስታወስ እንሞክር፡፡
- ቤተሰቡን አክብሪለት (ቤተሰቧን አክብርላት)
የአጋርዎን ቤተሰብ ማክበር በሌላ መንገድ ራሱን አጋራችሁን ማክበር ማለት ነው፡፡ የባል ወይም የሚስት ቤተሰብ ከባለትዳሮች ጋር ሊኖረው የሚገባ የቅርበት መጠን እንደተጠበቀ ሆኖ መከባበርና መደጋገፍ ወሳኝ ነው፡፡ እነኚህ አካላት ትዳራችሁን በአዎንታዊም ሆነ በአሉታዊ ተፅዕኖ ውስጥ የመክተት ኃይል አላቸውና በጥንቃቄ ይያዟቸው፡፡
- ስለቀድሞ አጋራችሁ ተነጋገሩ
በትዳር ውስጥ ችግር ከሚፈጥሩት ነገሮች አንዱ ስለ ቀድሞ የፍቅር ወይም የትዳር ጓደኛችሁ የሚኖር አስተሳሰብና በዚህ ወቅት ከዚያ/ች ሰው ጋር የሚኖራችሁ ግንኙነት ነው፡፡ ስለዚህ ከቀድሞ የፍቅር ወይም የትዳር ጓደኛችሁ ጋር በተያያዘ የሚነሱ ጥያቄዎችን በእርጋታና በግልጽነት ተነጋገሩባቸው፡፡
- ሁልጊዜ ከሳሽ አትሁኑ
ያለፉ ነገሮችን እንደ አዲስ እያነሳችሁ ከመነጋገር ተቆጠቡ፡፡ ስሜታዊ በሆናችሁበት ወቅትም ክፉ ቃል ከአንደበታችሁ ሊወጣ ይችላልና ባትናገሩ ይመረጣል፡፡ ከምንም በላይ በእያንዳንዷ ጉዳይ በሥርዓት መመካከር ሲቻል ‹ከሳሽ› ሆኖ መቅረብም ትዳር ዕድሜው በአጭሩ እንዲቀጭ ያደርጋል፡፡ ባል እሳት ለብሶ እሳት ጎርሶ ሲመጣ ሚስት ነገሮችን ቀለል አድርጋ እንዳላየ ለማለፍ መሞከር ወይም በተለየ መንገድ ስሜቱን አብርዳ ወደቀደመ ጸባዩ መመለስ ይገባታል፡፡ ሚስት የተለየ ጸባይ ያመጣች እንደሆነም ከባል የሚጠበቀው በማረጋጋት ወደ ቀደመ ስሜቷ ለመመለስ መሞከር ነው፡፡ ይህ ሳይሆን ቀርቶ አንዳችሁ ሌላችሁ ላይ ጣት የምትቀሳሰሩ ከሆነ ግን ከስህተታችሁ እየተማራችሁ ወደ ተሻለ ነገ ከመጓዝ ይልቅ ትዳራችሁ በአሸዋ ላይ እንደታነፀ ቤት ወደማዝመሙ ማምራቱ አይቀሬ ነው፡፡