4ኛው የዩኔስኮ የአርቴፊሻል ኢንተለጀንስ (AI) ሥነ-ምግባር ዓለም አቀፍ ፎረም (GFEAI 2026) ከመስከረም 14 እስከ 17 ቀን 2026 በሳዑዲ ዓረቢያ ሪያድ እንደሚካሄድ ዩኔስኮ አስታወቀ።
ፎረሙ በዩኔስኮ እና በሳዑዲ ዓረቢያ በሳዑዲ ዳታ እና ኤአይ ባለሥልጣን (SDAIA) እና በአለም አቀፍ የAI ምርምርና ሥነ-ምግባር ማዕከል (ICAIRE) በጋራ የሚዘጋጅ ሲሆን፣ የዘንድሮው ዋና መሪ ሃሳብ “ለሥነ–ምግባራዊ AI አስተዳደር ዓለም አቀፍ ትብብርን መለወጥ” የሚል ነው።
የፎረሙ ዋና ዓላማ የAI ሥነ-ምግባር መርሆችን ከንድፈ ሃሳብ ወደ ተግባራዊ ፖሊሲና አስተዳደር ማሸጋገር ሲሆን፣ የAI ልማት ከሰብዓዊ መብቶች፣ ከፍትሃዊነት፣ ከማካተትና ከኃላፊነት ጋር እንዲጣጣም የሚያስችሉ አቅጣጫዎች ይመከራሉ።
በፎረሙ የAI አስተዳደር፣ የAI ዝግጁነትና የተቋማት አቅም፣ የAI ቁጥጥርና ተጠያቂነት፣ AI በመንግሥት አስተዳደር፣ የፆታ እኩልነት፣ ትምህርት፣ ጤና፣ ባህልና ቋንቋዎች፣ የAI ደህንነት፣ ዘላቂነት እና ዓለም አቀፍ ትብብር የመሳሰሉ ጉዳዮች ይነሳሉ።
ፎረሙ የዩኔስኮ የ2021 የAI ሥነ–ምግባር ምክረ ሃሳብ በአባል ሀገራት ተግባራዊ እንዲሆን የሚደረገውን ሥራ ለማጠናከርም ያገለግላል። ዩኔስኮ ይህንን ምክረ ሃሳብ በAI ሥነ-ምግባር ዙሪያ የመጀመሪያው ዓለም አቀፍ የመመሪያ ማዕቀፍ እንደሆነ ይገልጻል።
የ2026 ፎረም ከGlobal AI Summit 2026 ጋር በተያያዘ የሚካሄድ ሲሆን፣ ሁለቱ ዝግጅቶች በሳዑዲ ዓረቢያ Global AI Week አካል ናቸው።
ለአፍሪካ ሀገራት ፎረሙ በተለይ ጠቃሚ ሲሆን፣ የAI ቴክኖሎጂ በማህበረሰብና በኢኮኖሚ ላይ የሚያመጣቸውን ዕድሎችና ተግዳሮቶች በሚመለከት የአፍሪካ አቅጣጫና ፍላጎት እንዲካተት ዕድል ይፈጥራል።

