6ሺ ይደርሳሉ የተባሉ ኢትዮጽያዊያን ዜጎች በሞዛምቢክ ታግተው ይገኛሉ ተባለ፡፡ እነዚሁ ታግተዋል የተባሉ ዜጎች ወደ ሀገር ለመመለስም የገንዘብ እጥረት ገጥሟቸዋል ሲል የሴቶችና ማህበራዊ ሚኒስቴር ይፋ አድርጓል፡፡
የሚኒስቴሩ የሰዎች ዝውውር ማስተባበሪያ የተመላሽ ዜጎች ክትትል እንዳስታወቀው በሞዛምቢክ ከሚገኙት 6ሺ በላይ ኢትዮጽያዊያን በተጨማሪ ቁጥራቸው ይህ ነው ያልተባሉ ኢትዮጽያዊያንም በተመሳሳይ ሁኔታ በዛምቢያ እስር ቤቶች እንዳሉ ጠቅሷል፡፡
በእስር ላይ ይገኛሉ የተባሉት ኢትዮጽያዊያኑ የሰብዓዊ መብት ጥሰት እያጋጠማቸው እንደሚገኝ መረጃው ለሚኒስቴር መስሪያቤቱ እንደደረሰው ይፋ አድርጓል፡፡
መንግስትም ለጉዳዩ ምላሽ ለመስጠት ጥረት ላይ ነው የተባለ ሲሆን የሚያስፈልገው የትራንስፖርት ወጪ ከፍተኛ ስለሆነ ይህንን ከሚሸፍኑ አጋር ድርጅቶች ጋር ንግግር ላይ መሆኑም ተመላክቷል፡፡
በዚህ ወቅት ወደ ሀገር ወስጥ የሚመለሱ ዜጎች ቁጥር ከፍተኛ ሆኗል የተባለ ሲሆን፤መንግስት ከስደት ተመላሽ ለሆኑ ዜጎች ማቋቋሚያ የሚሆን በሚል ከያዘው በጀት ጋር አለመጣጣም እንዳመጣም ተነግሯል፡፡
ከዚሁ መረጃ ጋር በተገናኘ በሁለት ሳምንታት ጊዜ ውስጥ በማይናማር በታጣቂዎች እጅ የነበሩ 477 ኢትዮጽያዊያን ዜጎች መመለሳቸውን የተመላሽ ወላጆች መግለጻቸው ተሰምቷል፡፡
ወደ 300 የሚደርሱ የአውሮፕላን ትኬት መቁረጥ ያልቻሉ ዜጎች አሁንም በማይናማር እንደሚገኙ ነው የተነገረው፡፡ እነዚሁ ዜጎች መቼ እና እንዴት ይመለሳሉ የሚለው አልታወቀም፡፡
ባለፉት ሦስት ዓመታት ጊዜ ውስጥ ከ300ሺ በላይ ኢትዮጽያዊያን ከሳውዲ አረቢያ፡ከሱዳን፡ከየመን፡ከቤሩትና ሌሎች ሀገራት ተመልሰዋል ነው የተባለው፡፡

