በመካከላችን መቅረፅ ድምፅ አስቀምጠን ከሠለሞን ተካልኝ ጋር ለቃለ-መጠይቅ ሸራተን ሆቴል እንገኛለን፡፡ ከሌሎች ጋር እንደተለመደው ከሰለሞንም ጋር እንጨዋወታለን፡፡ በጠረጴዛው ዙሪያ ተጠያቂው ድምፃዊ፣ እኔ (ቴዎድሮስ ተ/አረጋይ)፣ የመፅሔቱ ዋና አዘጋጅ ታምራት ኃይሉና ጋዜጠኛ አንተነህ አብርሃም ተቀምጠናል፡፡ ግንኙነታችን ለሁላችንም ያልታሰበና ድንገተኛ በመሆኑ ስለ ሠለሞን መረጃዎች ለማሰባሰብ ጊዜ አልነበረም፡፡ መፅሔቱ ወደ ህትመት በሚላክበት የመጨረሻዎቹ ሰዓታት በዚህ ወቅት እንደ ሠለሞን አይነት አነጋጋሪ ሰው ሲገኝ ማንኛውም ጋዜጠኛ ምን ሊሰማው ይችላል? ጋዜጠኛነት በባህሪው እንዲህ ነው፡፡ ወሬው ለነገ ቢያድር የተሻለ መረጃ ሊገኝበት ይችላል ፤ ለዛሬ ሲሆን ደግሞ ይበልጥ ትኩስ ይሆናል፡፡ በዚህ ስሜት ነው ለቃለ መጠይቁ የተቀመጥነው፡፡ ገና በ6 ዓመቱ ባደገበት መቱ ከተማ የጥላሁን ገሠሠን ‹‹የጀግና ሰው ክብሩ፣ ዳርድንበሩ››ን ሰምቶ በቀጣዩ ዓመት የወላጆች ቀን በዓል ላይ መዝፈኑን የሚናገረው ድምፃዊ ሠለሞን ተካልኝ ‹‹ፋጡማ›› በሚለው ዘፈኑ ከህዝብ ተዋውቋል፡፡ ድንገት ፖለቲካዊ ዘፋኝ የሆነው ይህ ሰው አሁን ደግሞ ድንገት ከፖለቲካው መስመር መውጣቱን አውጇል፡፡ ለምን? ለመሆኑ የቀድሞውና የአሁኑ ሠለሞን ማን ነው? ለምን ከኪነ ጥበብ ፖለቲካን ተጠጋ? ለምንስ ራሱን ከፖለቲካ አገለለ?.. በእዚህና በመሳሰሉት ጉዳዮች ላይ ለ1፡30 ሰዓት ተጨዋውተናል፡፡

ቴዎድሮስ፡- ሙያህ ምንድነው?
ሠለሞን፡- በአሁኑ ወቅት?.. ከዚህ በኋላ ያለውን ነው የምትለው?
ቴዎድሮስ፡- እሺ ከመጨረሻው ጀምርልኝ፡፡
ሠለሞን፡- ከዚህ በኋላ የሠለሞን ተካልኝ ሙያ የኢትዮጵያን መንግሥት ሳልነቅፍ፣ ህዝቡ ለተቃውሞ ቢወጣም ሳልደግፍ፣ ህዝብና መንግሥትን የሚያስታርቅ፣ ሰላማዊ የሆኑ (ስለ ፍቅርና ሰላም የሚሰብኩ) ዘፈኖች የምዘፍን አርቲስት ነኝ፣ እድሜ ሰጥቶኝ ከቆየሁ፡፡
ቴዎድሮስ፡- ቀድሞ የነበረው ሙያህስ?
ሠለሞን፡- በፊትማ ለተለያዩ ሚዲያዎች እንደገለፅኩት (ባልገልፅም ህዝቡ ያውቀዋል) በመንግሥት ጭፍን ተቃዋሚነት ተሰልፌ መንግሥትን የሚቃወሙ ዜማዎችን ነበረ የማቀነቅነው፡፡ የመጣሁበት መንገድ ጥሩ አልነበረም፡፡ የእብደት ዘመን ነበር፡፡
ቴዎድሮስ፡- መንገዱ ለአንተ ጥሩ ስላልሆነ ነው አሁን የቆምክበት ቦታ ላይ የተገኘኸው?
ሠለሞን፡- ለእኔ ብቻ አይደለም ጥሩ ያልሆነው ፤ ለህዝቡም ጭምር ነው፡፡ ከእንግዲህ ህዝቡ የሚያስፈልገው ሠላም፣ መቻቻልና እርቅ ነው፡፡ እኔ ስዘፍናቸው የነበሩ ዘፈኖች ግን ‹‹ውጣ! ተቃወም! ድንጋይ ወርውር! ጠመንጃ አንሳ!›› ነው፡፡ ይህን ህዝብ ነው መልሼ ስለ ሰላም የማስተምረው፡፡
ቴዎድሮስ፡- ተቃውሞ አያስፈልግም ብለህ ታምናለህ?
ሠለሞን፡- ያስፈልጋል፡፡ ስንቃወም ግን በምን መልኩ ነው? ይህ መንግሥት በግልፅ የሚታዩ ብዙ ጥሩ ሥራዎችን ሠርቷል፡፡ በመንገድ፣ በቴሌኮሙኒኬሽን፣ በት/ቤት… የሚታይ ግልፅ ለውጦች አሉ፡፡ የማትደብቃቸው ለውጦች ናቸው፡፡ ይህን ለማወቅ አዲስ አበባ መምጣትና ከዚያም ወደ ክልሎች መውጣት አለብህ፡፡ ዛሬ በየክልሉ ያሉ አውሮፕላን ማረፊያዎችን ብታያቸው ትገረማለህ፡፡ ከዛሬ አስር ዓመት በፊት በኢትዮጵያ ቴሌቪዥን አማካኝነት ጎንደር ስንሔድ አውሮፕላኑ ለማረፍ ተቸግሮ ባህር ዳር አርፏል፡፡ አሁን ግን ፓላስ ሆኗል፡፡
ቴዎድሮስ፡ የት የት ክልሎች ሔደሀል?
ሠለሞን፡- ባህርዳር ሔጃለሁ፡፡ ወደ ጅማም ሔጃለሁ፡፡ የምሔድባቸው ቦታዎች ይኖራሉ፡፡
ቴዎድሮስ፡- የመጀመሪያ ካሴትህ ገበያ ላይ የዋለው መቼ ነው?
ሠለሞን፡- 1978 ዓ.ም
ቴዎድሮስ፡- ከመጀመሪያው ካሴትህ በኋላ ምን ያህል ካሴቶችን ሰራህ? ሠለሞን፡- ከ‹‹ፋጡማ›› በኋላ ኢህአዴግ አዲስ አበባ ሊገባ አካባቢ ደርግ ሰዓት እላፊ ያወጀ ጊዜ ‹‹አራዳ›› የሚለው ዘፈን ያለበት ካሴት ወጣ፡፡ ወቅቱ ችግር ነበር፡፡ በኋላ ግን በየሚዲያው ስለቀረበ ውጤታማ ሆኗል፡፡ ሽያጩም ጥሩ ነበር፡፡ ከራሔል ዮሐንስ ጋርም ካሴት ሰርተናል፡፡ ከዚያ ‹‹ዜሮ ዜሮ›› መጣ፡፡
ቴዎድሮስ፡- በካሴትም ሆነ በነጠላ ዜማ ከሰራሀቸው የእስካሁን ዘፈኖችህ ሁሉ በተለየ ሁኔታ ዝና አግኝቼበታለሁ የምትለው የቱን ነው?
ሠለሞን፡- ውጤታማ የነበረው ካሴት ‹‹ዜሮ ዜሮ›› የተባለው ነው፡፡ ከዚያ በኋላ የሠራኋቸው ለገበያ ሳይሆን ለፖለቲካዊ ዓላማ ድጋፍ የሚሰጡ ናቸው፡፡ ይዘታቸውም ሙሉ በሙሉ ፖለቲካዊ ነው፡፡ ዘፈኖቹ ምናልባት 30 ሊሆኑና ሊበልጡም ይችላሉ፡፡ አሁን የማላስታውሳቸው ወቅታዊ ሥራዎች አሉ፡፡ በዚያ ተጠቃሚ የሆንኩት እኔ ሳልሆን የተቃዋሚው ጎራ ነው፡፡
ቴዎድሮስ፡- አንተም የተቃዋሚ ጎራ አንድ አባል ነበርክ እኮ ።
ሠለሞን፡- ልክ ነህ ነበርኩ፡፡
ቴዎድሮስ፡- ስለዚህ አልተጠቀምክም ማለት ይቻላል? ባይሆን ጥቅሙ ለግሌ መሆኑ ቀርቶ ለጋራ ሆነ ካላልክ በቀር፡፡
ሠለሞን፡- በገንዘብ ከሆነ አልተጠቀምኩም፡፡ በሙያዬና በተሰጥኦዬም አልተጠቀምኩም፡፡ የእኔ ዘፈኖች የሚሸጡ አይደሉም፡፡ ሙዚቃ ቤት ብትገባ አታገኛቸውም፡፡
ቴዎድሮስ፡- የተቃውሞ ዘፈኖቹን በአንድ ላይ አድርጎ (በተለይ በውጭ ሀገር) ለገበያ ማቅረብ አይቻልም ነበር?
ሠለሞን፡- አይቻልም፡፡ ነጋዴው ሽጥልኝ ብትለው አይሸጥልህም፡፡ ለምሳሌ እዚያ ሆኜ ‹‹አዋጅ›› የሚለውን ካሴት (ዲግሪ አድርጌና እስረኛ ሆኜ ፎቶ የተነሳሁበት ፖስተር ያለበት) አሜሪካ ሀገር ነጋዴዎች እንዲያከፋፍሉልኝ ሰጥቼ ነበር፡፡ ነጋዴው ግን ለመቀበል አልፈለገም፡፡
ቴዎድሮስ፡- ለምን?
ሠለሞን፡- ‹‹የፖለቲካ ዘፈን ስለሆነ ማንም አይገዛንምና አንወስድም›› ነው ያለኝ፡፡ ከዚያን ጊዜ ጀምሮ ‹‹ሰው ፖለቲካ ካልፈለገ እኔም አቋሜን መቀየር አለብኝ›› ብዬ አስብ ነበር፡፡ አርቲስት ስትሆን ተቀባይነት ማግኘት አለብህ፡፡ ውጭ ያለው ሰው ፖለቲካውን ትቶታል፡፡ ሠላማዊውን መንገድ እየመረጠ..
ቴዎድሮስ፡- እዚህ ጋር ላስቆምህ ነው፡፡ በመጀመሪያ አሜሪካ ያለው ህዝብ የፖለቲካ ዘፈኖች አይፈልግም የሚለውን አልቀበለውም፡፡ እሱን እናቆየውና ግን ሰው ‹‹አይገዛም›› ስለተባለ አቋም መቀየር እንዳለብህ ከገለፅክ በሌላ አባባል ስራው ከፍተኛ ገበያ ቢኖረው አትቀይርም ነበር ማለት ነው፡፡ (ይህ ከሆነ ጉዳዩ የእምነት ሳይሆን የጥቅም ይሆናል)
ሠለሞን፡- አአ! ይህን ስልህ እንዳትሳሳት፡፡ ጋዜጠኞች አንዳንዴ በቀጥታ አትሔዱም፡፡ የእኔን አባባል ስነግርህ… (አደራህን በኋላ ስትፅፈውም እንዳታሳስተው) ነጋዴዎቹን ሔጄ ስጠይቃቸው ‹‹ህዝቡ የፖለቲካ ዘፈን ስለማይገዛ አንቀበልም›› ሲሉ ህዝቡ ፖለቲካ አይፈልግም ማለት ነው ወይ? የሚል ጥያቄ መጣብኝ ነው ያልኩት፡፡ ህዝቡ የፖለቲካ ዘፈኖችን ካልፈለገ ወደፊት ሥራዎቼ ምን ሊሆኑ ይችላሉ? አርቲስት በሁለት እግሩ የሚቆመው እኮ ህዝብ ሲደግፈው ነው፡፡ ህዝብ ካልወደደው የእኔ ድካም ብቻውን ዋጋ የለውም፡፡
ቴዎድሮስ፡- ይህን ጉዳይ አሁኑኑ አጥርተን እንለፍ መሰለኝ፡፡ ህዝቡ በአሁኑ ወቅት ‹‹ተረጋግቷል፤ ፖለቲካውን ትቶታል›› የሚለው አባባልህ አላሳመነኝም፡፡ ያም ቢሆን እንኳን የፖለቲካው መረጋጋት ያንተን ካሴት እንዳይሸጥ እስከ ማድረግ ደርሷል ማለት የተጋነነ አይሆንም?
ሠለሞን፡- ህዝቡ አይደለም ይህን ያለኝ፡፡ አሁንም አትሳሳት፡፡ እኔ እኮ ሥራውን ለህዝብ ሳይሆን ለነጋዴው ነው የማቀርበው፡፡ አልቀበልም ያለኝ ነጋዴው ነው፡፡
ቴዎድሮስ፡- አንዱ እምቢ ቢል ሌላው ጋር መሞከር አይቻልም? ሠለሞን፡- እዚያ ይህ እድል የለም፡፡ ቴዎድሮስ፡- አንድ አከፋፋይ ብቻ ነው ያለው?
ሠለሞን፡- ሁለት አከፋፋዮች ናቸው ያሉት፡፡ ቴዎድሮስ፡- በመላው አሜሪካ? ሠለሞን፡- አዎን፡፡ በዚያ ላይ መደብሮቹን ብታያቸው ለሙዚቃ ብቻ ሳይሆን ሽሮ፣ እንጀራ… መሸጫዎች ናቸው፡፡ እዚያ ውስጥ ነው ሲዲዎቹ የሚቀመጡት፡፡ ባለመደብሩ በስውር ቅንጅትን ወይም ህብረትን ሊረዳ ይችላል፡፡ በአደባባይ ግን እኔ እጄ ላይ ሰንሰለት አስሬ መንግሥት የተቃወምኩበትን ዘፈን ሊሸጥ አይችልም፡፡
ቴዎድሮስ፡- ይህ ካሴት ግን ገበያ ላይ ውሏል አይደል?
ሠለሞን፡- እሱማ ህዝቡ ከፈለገ መሸጡ አይቀርም፡፡ ማንም ሰው አባዝቶ መውሰድ ይችላል፡፡ በየኢንተርኔቱ ላይ ተለቋል፡፡
ቴዎድሮስ፡- ኧረ እንደማንኛውም የንግድ ካሴት ተሸጧል ነው የምልህ፡፡
ሠለሞን፡- በሽያጭ ደረጃ መጨረሻ ላይ ‹‹ኢትዮ ሳውንድ›› የሚባል ሙዚቃ ቤት ሽጦታል፡፡ ሠው በኢንተርኔት መነጋገር ሲጀምርና ስለዘፈኑ ሲወራ ወሰደው፡፡
ቴዎድሮስ፡- ሽያጩ እንዴት ነበር? ሠለሞን፡- ያን ያህል አጥጋቢ አይደለም፡፡ ቴዎድሮስ፡- መነጋገሪያ የሆነ ዘፈን እንዴት ገበያ አይኖረውም? ሠለሞን፡- አሜሪካ ሀገር ሔደህ ‹‹የሠለሞን ተካልኝን ካሴት ስጠኝ›› ብትል ማንም ሰው የለውም፡፡ እኔ አሜሪካ ሀገር በሙዚቃ ስራ የምተዳደር ሰው አይደለሁም፡፡ ማንም ሰው እኔን ጠርቶ አያሰራኝም፡፡ ሬስቶራንቶች ውስጥ እንኳን መስራት አልችልም፡፡
ቴዎድሮስ፡- ለምን?
ሠለሞን፡- ፖለቲካዊ ዘፋኝ ነኝ፡፡ ክረምት ላይ የተወሰኑ ሰርጎችን እሰራለሁ፡፡ የፖለቲካ ፓርቲዎች የውይይት መድረክ ሲኖራቸው በየስቴቱ እየጠሩኝና እየከፈሉኝ እዘፍናለሁ፡፡ ስብሰባው ከመጀመሩ በፊትና በኋላ በሚኖረው የመዝናኛ ፕሮግራም እኔ ነኝ የምዘፍነው፡፡ ቴዎድሮስ፡- ግን… ምሽት ክበቦች ሥራ ብትባልስ ለዚያ ቦታ የሚመጥኑ ዘፈኖች አሉህ?
ሠለሞን፡- የሉኝም፡፡ እዚያ ብሔድ ልዘፍን የምችለው የሰው ዘፈን ነው፡፡ ምክንያቱም አስር ዓመት ሙሉ ስጮህ የነበረው ሌላ መንገድ ላይ ነው፡፡ የሰው ዘፈን ልዝፈን ብል እንኳን የእኔ እዚያ ቦታ ላይ መገኘት ሥራውን ያበላሸዋል፡፡ ምክንያቱም እኔ ከጥበብ ሳይሆን ከፖለቲካ ጋር ተያይዤ ነው የምታሰበው፡፡ ቴዎድሮስ፡- የራስህን ባህሪ እንዴት ነው የምትረዳው?
ሠለሞን፡- እንዴት?
ቴዎድሮስ፡- ምን አይነት ሰው ነኝ ብለህ ታስባለህ?
ሠለሞን፡- ምላሹ ምንም ይሁን ምን ላመንኩበት ነገር እሞታለሁ፡፡
ቴዎድሮስ፡- በፊትም፣ ዛሬም ይህ እምነት አለህ?
ሠለሞን፡- ባለፈው አስር ዓመት ያመንኩበትን ሰርቻለሁ፡፡ አልፏል፡፡ ያ ያመንኩበት ነገር ግን አሁን ተቀምጬ ሳስበው ጥፋት እንደነበር አምኜበታለሁ፡፡ በፍርድ ቤት የተከፈተብኝ ክስ ሲነሳልኝ ህዝብንና መንግሥትን ይቅርታ ጠይቄ ለመስራት ሀገሬ ገብቻለሁ፡፡ ‹‹ለምን ይቅርታ ጠየቅህ›› የሚለኝ ካለ፣‹‹ሙት›› የሚለኝ ካለ አልሞትም፡፡ እኔ ከእንግዲህ ህዝብና መንግሥትን ለማራራቅ ሳይሆን ለማቀራረብ ነው የምዘፍነው፡፡ ከዚህ በኋላ እኔ ፖለቲከኛ አይደለሁም፡፡ እንድትፅፈውና የኢትዮጵያ ህዝብ እንዲያውቀው የምፈልገው ከአሁን በኋላ ፖለቲከኛ አይደለሁም፡፡ እንደማንኛውም ዘፋኝ ወጥቶና ገብቶ መስራት ነው የምፈልገው፡፡ እኔ ነፃ ሰው ነኝ፡፡ የኢትዮጵያ ህዝብ ከዚህ በፊት የሰራኋቸውን ሥራዎች እንደ መልካም ተግባር የሚቆጥርልኝ ከሆነ ዱሮ እንደሚወደኝና እንደሚያከብረኝ ይቀጥልበት፡፡ ‹‹ሠለሞን ተካልኝ ለምን ሀገሩ መጣ?›› የሚል ሆኖ ከጠላኝ ደግሞ የእኔን ማንነት ወደፊት ያውቀዋል፡፡
ቴዎድሮስ፡- ግን አሁንስ ቢሆን ህዝቡ ከተቃዋሚዎች መስመር መውጣትህን እንጂ ከፖለቲካ መራቅህን ማመን ይችላል?
ሠለሞን፡- በተቻለ መጠን በሥራዎቼ ለማሳመን እሞክራለሁ፡፡ ሰሞኑን የተለቀቁ ሁለት ዘፈኖች አሉኝ፡፡ ለህዝብ በነፃ ነው የታደሉት፡፡ አንዱ ስለሚሊኒየም የዘፈንኩት ነው፡፡ ሌላው ደግሞ ‹‹አባ ፀበል እርጩን›› የሚለው… ‹‹አባ ፀበል እርጩን እስቲ ቢያስታርቀን ወንድማማቾቹ ቀረን ተራርቀን…›› የሚል ነው፡፡ እንዲህ ያለ ሥራ መስራት ነው የምፈልገው፡፡
ቴዎድሮስ፡- ህዝቡ እንዴት ይቀበለዋል ብለህ ነው የምታምነው?
ሠለሞን፡- የኢትዮጵያን ህዝብ አልበደልኩም፡፡ ከህዝቡ ጋር ግጭት የለኝም፡፡ የህዝብ ልጅ ነኝ፡፡ እንደ ዱሮው ይቀበለኛል ብዬ ነው የማምነው፡፡ ቴዎድሮስ፡- ባለፈው መጥተህ በመሀል ተመልሰህ ሄደሀል፡፡ የመሔድህ ምክንያት ምንድነው?
ሠለሞን፡- መጀመሪያ ስመጣም 15 ቀናት ለመቆየት ነው፡፡ እዚያ የያዝኩቸው ሦስት የሠርግ ሥራዎች ነበሩኝ፡፡ ሌላው የልጄ 1ኛ ዓመት ጁን 6 ነበር፡፡ ይህን ማክበር አለብኝ፡፡
ቴዎድሮስ፡- ግን እኮ ልጅህና ሥራው ያሉት አሜሪካ ሆኖ አንተ የሔድከው ግን እንግሊዝ ነበር፡፡
ሠለሞን፡- አይደለም፡፡ በለንደን በኩል ሔድኩ እንጂ እዚያ አልቀረሁም፡፡ ቲኬቱ ለንደን ይሁን እንጂ አሜሪካ ሔጄ ሬዲዮ ኢንተርቪው ሰጥቻለሁ፡፡ ጆርጂያ ነው የሔድኩት፡፡ ለንደን የሦስት ቀን ቆይታ አድርጌ በአራተኛው ቀን አሜሪካ ነው የሔድኩት፡፡
ቴዎድሮስ፡- ከመሔድህ በፊት ተደብድበሀል የሚባለው እውነት ነው?
ሠለሞን፡- ማንም አልነካኝም፡፡ የምደበደብበት ምክንያም የለም፡፡ ይህ አሉባልታ ነው፡፡
ቴዎድሮስ፡- አሁን ባለትዳርና የልጅ አባት ነህ፡፡ እዚህ ውሳኔ ላይ ስትደርስ ለባለቤትህ አማክረሀታል?
ሠለሞን፡- አዎን፡፡ እሷም የዓላማዬ ደጋፊ ናት፡፡
ቴዎድሮስ፡- ግን እንዴት ተዋውቃችሁ ለትዳር በቃችሁ?
ሠለሞን፡- የእኔና የእሷ ለዚህ መብቃት የራሱ አስገራሚ ታሪክ አለው፡፡ ባለቤቴ ሣራን የማውቃት አዲስ አበባ ከተማ የዛሬ 13 ዓመት ገደማ ስቴዲየም አካባቢ ነው፡፡ በወቅቱ መኪና አቁሜ ክላክስ አደረኩላት፡፡ (ያው ለከፋ ማለት ነው) ሰድባኝ ሄደች፡፡ ምክንያቱም ዘፋኝ ዱርዬ ተደርጎ ነው የሚወሰደው፡፡ ከዚያ በኋላ ዓይኗን አይቻት አላውቅም ፡፡ የዛሬ 7 ዓመት ገደማ የስፖርት ውድድር ካናዳ የተከበረ ጊዜ መድረክ ላይ ዘፍኜ ወርጄ ከኤልያስ ተባባል ጋር ምግብ ልንበላ ስንሔድ ሳራ በዲቪ መጥታ ከእህቷ ጋር ምግብ ቤቱ ጎጆ ውስጥ አገኘችኝ፡፡ ከዚህ ከሔደች ገና 6 ወሯ ነው፡፡ ጉዳዩን እሷ አንስታ ተነጋገርን፡፡ ኤልያስ በወቅቱ ‹‹ተባባል ምን አለ በለኝ ታገባታለህ›› አለኝ፡፡ ስልክ ተለዋውጠን ተለያየን…. ከዚያ እኔና ሳራ ስንጋባ ኤልያስ ሚዜያችን ነበር፡፡ ታማኝ በየነ፣ ንዋይ ደበበ፣ ፀሐይ ዮሀንስ፣ ፀጋዬ እሸቱ፣ አረጋኸኝ ወራሽ፣ ፋሲካ ዲሜትሪም ሚዜዎቼ ነበሩ፡፡ እንደ ወላጅም፣ እንደ ቤተሰብም፣ እንደ ወንድምና ጓደኛም ሆነው ድረውኛል፡፡
ቴዎድሮስ፡- ለመሆኑ የምግብ ምርጫህ ምንድነው?
ሠለሞን፡- ሽሮ በስጋ እወዳለሁ፡፡
ቴዎድሮስ፡- እዚያ የሀበሻ ምግብ እንደልብ ይገኛል?
ሠለሞን፡- አለ፡፡ እኔ ግን በጣም ነው መስራት የምችለው፡፡ እኔ የምሰራውን ምግብ (የፈረንጅም ሆነ የሀበሻ) የትኛዋም ሴት አትሰራውም፡፡ በተለይ የሀበሻ ምግብን ምግብ ቤት ገብቼ አልበላም፡፡ ከዶሮ ወጥ ሌላ ሁሉን እሰራለሁ፡፡ ቤት ስውል ምግብ መስራት እንደ ‹‹ሆቢ›› ነው የማየው፡፡
ቴዎድሮስ፡- ስንት ኪሎ ነህ?
ሠለሞን፡- 210 ፓውንድ፡፡
ቴዎድሮስ፡- አርቲስት ፖለቲካ ውስጥ መግባት አለበት/የለበትም የሚለው ሐሳብ አከራካሪ ነው፡፡ በአባባሉ ላይ ያንተ አቋም ምንድነው? ሠለሞን፡- አሁን ላይ ሆኜ ሳስበው መግባት የለበትም ነው የምለው፡፡
ቴዎድሮስ፡- ጥያቄውን ያነሳሁት ለምን መሰለህ? አንተ ‹‹ዜሮ ዜሮ›› የሚለውንና ከዚያ በኋላ የዘፈንካቸውን ዘፈኖች ሰምቶና አምኖ (ከሌሎች ጉዳዮች በተጨማሪ) ወደ ፖለቲካው የገባ ወጣት አለ፡፡ አንተ ‹‹መንገዱ ልክ አይደለም›› ብለህ ስትመለስ እነዚያን ወጣቶች ታስባቸዋለህ? ሠለሞን፡- አስባቸዋለሁ፡፡ ግን እነሱም መመለስ አለባቸው፡፡ የሠለሞን መንገድ መምረጥ አለባቸው፡፡ ለምሳሌ ‹‹ዜሮ ዜሮ›› የሚለው ዘፈኔ ላይ… ‹‹ካፎቱ ይውጣ ጎራዴ ሳንጃው ደም በደም ይሁን መረማመጃው እሪ በል መርኬ እሪ በል ፒያሳ ይጭስ ይጫጫስ አንዴ ተነሳ›› ይላል፡፡ ይህ ማለት ምን ማለት ነው? አሁን በረጋ መንፈስ ሳስበው ትልቅ መልዕክት ያለውና ሰውን ‹‹ውጣ!›› የሚል ነው፡፡ በወቅቱ ወጣትነትም ስላለ ላይታወቀኝ ይችላል፡፡ በእድሜ መብሰልና ማንበብ ሲመጣ ግን ስህተቱ ታይቶኛል፡፡
ቴዎድሮስ፡- በዚያን ጊዜ በአፍለኛነት ስሜት ዘፈንከው እንዳይባል እስከ ቅርብ ጊዜ ቆይተህበታል፡፡ ስህተትህን ለማረም አስር ዓመት ብዙ አይሆንም?
ሠለሞን፡- የነበርኩበት ቦታና ሁኔታ ከዚያ መስመር በቀላል እንድወጣ አላደረገኝም፡፡ ከመስመሩ ለመውጣት ብዙ ትግል ይጠይቅሀል፡፡ አሁን እዚህ ቦታ ያገኘኸኝ ብዙ ፈተና አልፌ ነው፡፡ እዚያ ሆነህ የምትሰማው ተቃውሞ ብቻ ነው፡፡ ዙሪያህ በተቃውሞ የታጠረ ነው፡፡ አሁን እዚያ ያለውን ህዝብ አስሮ የያዘው ይህ ነው፡፡ ያን አልፎ መውጣት በራሱ ትግል ይጠይቃል፡፡ እኔ አሁንም ትግል ውስጥ እኮ ነው ያለሁት፡፡ የአሁኑ ትግል ግን የአመፅ ሳይሆን የሰላም ነው፡፡
ቴዎድሮስ፡- ስለአንተ የተባሉ ሁለት ነገሮችን ላንሳልህ፡፡ አንዱ የአመጣጥህ ጉዳይ ነው፡፡ ወደዚህ ሀገር ስትመጣ አንተ ‹‹ክሱ ስለተነሳልኝ›› የሚል ምክንያት ነው የምትሰጠው፡፡ ሌሎች ግን ጉርሻ የሰጠህ ክፍል እንዳለ ነው የሚናገሩት፡፡ ነገሩን ሰምተኸዋል?
ሠለሞን፡- አዎን ሰምቼዋለሁ፡፡ እውነቱ ግን ጨርቄንና ጫማዬን አንጠልጥዬ መምጣቴ ነው፡፡ አሜሪካ ወዳለው የኢትዮጵያ ኤምባሲ ሔጄ ‹‹ሀገሬ መግባት እፈልጋለሁ›› ስል ቪዛ ሰጡኝ፡፡ እዚህ ሀገር ሆነው የሚቃወሙ የሉም እንዴ? በሰላም ከመኖር አልፈው ከአቶ መለስ ጎን ተቀምጠው እየሰሩ እኮ ነው፡፡ አሜሪካ መሆን ብቻውን የተለየ ትርጉም የለውም፡፡
ቴዎድሮስ፡- ሁለተኛው ጉዳይ ደግሞ ሠለሞን ቀድሞውን ፖለቲከኛ የሆነው ሙዚቃው አላዋጣ ሲለው ነው (ፖለቲካ አንዳንዴ አትራፊ ንግድ የሚሆንበት ሁኔታ አለና) የሚሉ አሉ፡፡ በሙዚቃው የከሰረውን በፖለቲካ ማካካስ ፈለገ ለሚሉት ያንተ ምላሽ ምንድነው?
ሠለሞን፡- እኔ ለዚህ መልስ የለኝም፡፡ ሰው የፈለገውን ማለት ይችላል፡፡ እኔ ተሰጥኦዬን አውቀዋለሁ፡፡ በአሁኑ ወቅት 14 የፍቅር ግጥምና ዜማዎች ሰብስቤ እየሰራሁ ነው፡፡ እነዚህ ዘፈኖች ለህዝብ ሲደርሱ ጥያቄውን ይመልሱታል ብዬ አምናሁ፡፡ አሁን ደግሞ ለሚሊኒየሙ መድረክ ላይ ወጥቼ እዘፍናሁ ብዬ አስባለሁ፡፡
ቴዎድሮስ፡- ህዝቡስ ይቀበለኛል ብለህ ታስባለህ?
ሠለሞን፡- እሱን ከወዲሁ መገመት አልችልም፡፡ ግን ሚሊኒየሙ የኢህአዴግ በዓል እንዳልሆነና የኢትዮጵያ ልዩ በዓል እንደሆነ አምናሁ፡፡ ደርግ ቢኖር ወይም ቅንጅት ስልጣን ላይ ሆኖም በዓሉ ቢደርስ እንደዚያው ነው፡፡ የሙያ ጓደኞቼም ለምን ይህን እንደማይረዱት አይገባኝም፡፡ ቴዎድሮስ፡- እምነታቸው ልክ ነውና አይደለምን እንተወውና አንተ ሙያህን ትተህ ከፖለቲከኞቹ ፊት ሆነህ ስትጮህ የነበርክ ሰውዬ ድንገት በጎርፍ እንደተወሰደው ሰው ያልታሰበ ቦታ ላይ ስትገኝ….
ሠለሞን፡- (አቋረጠኝ) አአ! ይሔን አባባልህን አስተካክለው፡፡ እኔ አስቤበትና አምኜበት እንጂ ድንገት አይደለም የመጣሁት፡፡ ይሄ አሉባልታ ነው፡፡ አንተም በጋዜጠኝነትህ መዋጋት ያለብህ ይህን አሉባልታ ነው፡፡ አሉባልታ ነው የጎዳን፡፡ አንድ ሰሞን አንድን ሰው የሚናገረውን ብቻ አምነን ሰማይ እንሰቅለዋለን፡፡ ‹‹ማንዴላ›› እንለዋለን፡፡ ‹‹ጀግና›› እንለዋን፡፡ ‹‹አንበሳ›› እንለዋለን፡፡ ያን ሰውዬ አውቀኸው ነው እንዲህ የምትለው? የኢትዮጵያ ህዝብ እኔን አውቆኝ ነው ሲያሞግሰኝ የነበረው? የሙያ ጓደኞቼ ስለ እኔ ምን ያውቃሉ? በዘፈንኩት ዘፈን ብቻ ነው ጀግና እና አንበሳ የሚሉኝ፡፡ ስለ እኔ ማንነት የሚያውቅ ሰው የለም፡፡ ልቤ ውስጥ ምን እንዳለ ማንም አያውቅም፡፡ ‹‹ዜሮ ዜሮ›› ብዬ ስዘፍን ለብር ይሁን ለእምነቴ የዘፈንኩት ማንም አያውቅም፡፡ ሁሉም ዝም ብሎ ነው የሚቀበልህ፡፡ ከዚያ ደግሞ ‹‹መንገዴ ልክ አይደለም… እስቲ ደግሞ በሌላ መንገድ ልሂድ …›› ስትል ዘራፍ የሚል ይመጣል፡፡ ነገ እኮ እኔ ሀሳቤን ልቀይር እችላለሁ፡፡
ቴዎድሮስ፡- እንደገና ደግሞ? ለስንተኛ ጊዜ?
ሠለሞን፡- ኖኖ! በፖለቲካው አይደለም፡፡ እሱ ውስጥ እንደማልገባ አስረግጬ ነግሬሀለሁ፡፡ ይህ የማይለወጥ ቃሌ ነው፡፡ ይህም መንግሥት ይኑር፣ ሌላውም ይምጣ በምንም አይነት ከእንግዲህ ወደ ፖለቲካ አልገባም፡፡ ይህን በደንብ እንድትጽፈው ነው የምፈልገው፡፡ በቃ! ግን በሕይወትህ ውስጥ፣ ሰው ነህና አቋምህን ልትቀይር ትችላለህ፡፡ እኔ ሀገሬ ገባሁ እንጂ ከመንግሥት ጋር አልተገናኘሁም፡፡ እንደሌላው ኢትዮጵያዊ መሆን እፈልጋለሁ፡፡ እዚያ ከእኛ ጋር ለተቃውሞ ሰልፍ እየወጣ እዚህ መጥቶ ፎቅ የሚሰራ አለ፡፡ እዚህ ከመጣሁ በኋላ የስንቶቹን ጉድ አይቻለሁ፡፡ እዚህ መጥቼ ፎቅ መስራት ባልችል እንኳን ከወንድሞቼ ጋር ትኩስ ሽሮ እባላለሁ፡፡ እናቴ እዚያ ሆኜ ነው የሞተችው፡፡ አልቀበርኳተም፡፡ አባቴ አሁን 67 ዓመቱ ነው፡፡ ስመጣ በግራ ዓይኑ ነው ያየኝ፡፡ ቀኝ ዓይኑ ጠፍቷል፡፡ ነገ ቢሞት አልቅሼ እቀብረዋለሁ፡፡ ይህን እድል ለምን አጣለሁ?
ቴዎድሮስ፡- የፖለቲካውን መስመር ‹‹ተውኩት›› ስትል መንግሥትን ላለመደገፍና ላለመቃወም ነው፡፡ አሁን ፊቴ ያለው ሠለሞን ግን መቃወሙን ትቶ መደገፉን የያዘ መስሎ ነው የሚታየኝ፡፡ (ቅር ካሰኘሁ ይቅርታ)
ሠለሞን፡- ደጋፊ ላለመባል ያየሁትን መካድ ነበረብኝ? አዲስ አበባ ላይ ያለውን ፎቅና ሌሎች መሠረት ልማቶች መሠራታቸውን መናገር እውነቱን መመስከር እንጂ መደገፍ አይደለም፡፡ ካሁን በፊት በሰጠሁት ኢንተርቪው ያየሁትን ድክመት ተናግሬያሁ፡፡ ይህ መንግሥትን መንቀፍ ማለት ነው? አይደለም፡፡
ቴዎድሮስ፡- ለምሳሌ ምን ምን አልክ?
ሠለሞን፡- የኤች አይ ቪ/ኤድስ ህሙማን መብዛታቸውን፣ የቤት እጥረት መኖሩን፣ ሥራ አጥ መብዛቱን ተናግሬያለሁ፡፡
ቴዎድሮስ፡- ለዚህማ ገዢው ፓርቲ ራሱ ‹‹ስህተቴ ናቸው›› ብሎ በማመን የመልካም አስተዳደር ችግሮች እንደታዩበት ሲናገር አድምጠናል፡፡ ስለዚህ ያንተ ነቀፌታ ባለቤቱ ስለ ራሱ ከተናገረው አንፃር ትንሽ ነው፡፡ ቁጥር ውስጥም የሚገባ አይደለም፡፡
ሠለሞን፡- እንግዲህ ዝርዝር ፖለቲካዊ ጉዳዮች ውስጥ ጠለቅ ብዬ እንደማልገባ ተናግሬሀለሁ፡፡ ከጭፍንነት ወጥቻለሁ፡፡
ቴዎድሮስ፡- ለእኔ ግን አሁንም ሌላ ጭፍንነት ውስጥ እየገባህ ነው፡፡ ሠለሞን፡- ምን አይነት ጭፍንነት?
ቴዎድሮስ፡- በመጣህ በአጭር ቀናት ውስጥ ያለውን መልካም ነገር በስፋት ተናግረሀል፡፡ እንደበፊቱ መቃወም ብቻ አይገባህ ይሆናል፡፡ ወደ ውስጥ መግባትን ወይም በውስጡ መኖርን ይጠይቃል፡፡ ዳር ቆመህ ካመሰገንክ (በተለይም በዚህ ሀገር ያልነበረክ ነህና) ጭፍንነት አይባልም?
ሠለሞን፡- አይባልም፡፡ የምለው ለምን እንደማይገባህ አላውቅም፤ እኔ ውስጥ መግባት አልፈልግም፡፡ ካለፈው ስህተቴ ተምሬያለሁ፡፡ ወደፊት ስለሚመጣው ደግሞ እንደ ባህታዊ ገብረ መስቀል መተንበይ አልችልም/ሳቅ/ እኔ የተናገርኩት ከመጣሁበት ጊዜ ጀምሮ ስላለው ሁኔታ ነው፡፡ ወደ ውስጥ ለመግባት እንደ ዱሮው ፖለቲከኛ ልሆን ነው፡፡ አልፈልገውም እሱን፡፡ አንተ እኮ እዚያ ስላልነበርክ ነው፡፡ ጨርቆስ ሰባት ሰው ተገደለ፣ ፒያሳ ሀያ ሰው ተገድሎ ተጣለ ሲባል ሰምተህ እዚህ መጥተህ የምታየው ተዓምር ነው የሚሆንብህ፡፡ ብዙዎች ለሚሊኒየሙ ወደ ሀገራቸው ሲመጡ በሰሙትና በሚያዩት መካከል ያለውን ልዩነት እንደሚረዱት አምናለሁ፡፡
ቴዎድሮስ፡- ከተቃዋሚነት ሰልፍ ወጥተህ አዲስ አበባ የተገኘህበት የራስህ ምክንያት ይኖርሀል፡፡ መቼም ማታ በሰላም ተኝተህ ጠዋት ስትነሳ እዚህ ውሳኔ ላይ አልደረስክም፡፡ ለዚህ ውሳኔ ያበቃህ ትክክለኛ ምክንያት ምንድነው?
ሠለሞን፡- ፖለቲካው በጠቅላላ ማብቃቱን ያወቅኩት ከኤርትራው ጉዞዬ በኋላ ነው፡፡ አስመራ ሄጄ በረሀ ውስጥ አንድ ወር ከ15 ቀን ስቀመጥ ለኢትዮጵያ ጥቅም የቆመ ወታደር እዚያ ቦታ ላይ አጣሁ፡፡ ይህን ዋሽንግተን ዲሲ ወደ 700 ሰው በተሰበሰበበት ካሜራ የቀረፅኩትን አሳይቻለሁ፡፡
ቴዎድሮስ፡- የአቋም ለውጥ ለመምጣትህ የአስመራ ጉዞህ ምክንያት መሆን አንተ በገለፅከው መንገድ የተፈጠረ አይመስለኝም፡፡ አስመራ ደርሰህ አሜሪካ ስትመለስ ህዝቡ ፊት ስለነሳህ ነው ይባላል፡፡
ሠለሞን፡- እኔ ለዚህ ምንም መልስ አልሰጥም፡፡
ቴዎድሮስ፡- ወደዚህ ለመምጣት ስትወስን ከቅርብ ጓደኞችህና ሚዜዎችህ ጀምሮ እስከ ሌሎች ያለው ስሜት ምን ይመስል ነበር? አውርተሀቸዋል?
ሠለሞን፡- ከዚህ በፊት ስሰራ ከማንም ጋር ተወያይቼ አላውቅም፡፡ ለዚህ ነው የምንቀሳቀሰው፡፡ አሁንም ለማደርገው ሁሉ ማንንም ግራና ቀኝ ማማከር አያስፈልገኝም፡፡ በእምነቴ ነው የምንቀሳቀሰው፡፡
ቴዎድሮስ፡- ቀድሞውንም ሙያህን ትተህ ወደ ተቃዋሚነት መሔድህን (ሙያህን ለተቃውሞ ማዋልህን) ያልተቀበሉህ የሙያ ጓደኞች አልነበሩም?
ሠለሞን፡- ነበሩ፡፡ ብዙዎቹ የእኔን ሥራና ውሳኔ አይደግፉም ነበር፡፡ ‹‹እንደ እኔ በሙያህ ብቻ ለምን አትሰራም?›› የሚሉኝ አርቲስቶች ነበሩ፡፡ በጠቅላላው ማለት ትችላለህ፡፡ ‹‹ይቅርብህ›› ያሉኝ ነበሩ፡፡ አሁን ታዲያ ይህን ሰላማዊ መንገድ ስመርጥ ምንድነው ችግሩ? በእኔ እዚህ መምጣት በውጭም እዚህም ‹‹ሠለሞን ከኢህአዴግ ጋር እጅ ለእጅ ተጨባበጠ›› የሚሉ አሉ፡፡ እዚህ ሀገር ያሉ ዘፋኞች ህዝብ አደባባይ ወጥቶ ሲጮህ፣ ተቃውሞውን ሲያሰማ ለምን በራቸውን ዘግተው ተቀመጡ? እውነት ህዝቡን የሚወዱት ከሆነ ለምን ከጎኑ አልቆሙም? ይሔን በደንብ እንድትፅፈው እፈልጋለሁ፡፡ ‹‹አርቲስት ፖለቲካ ውስጥ መግባት የለበትም›› የሚሉኝ ነበሩ፡፡ አሁን እነሱ ወደሚፈጉልት ስመጣ ለምን ይከፋቸዋል? እኔ ከእንግዲህ በኋላ የቤተሰብ ኃላፊ ነኝ፡፡ ይህን ለማድረግና ከህዝብ ጋር ለመገናኘት ሰለማዊውን መንገድ መምረጥ አለብኝ፡፡ ከእነሱ ጋር አንድ ቀን ፊት ለፊት ተገናኝተን ያሉትንና የሆነውን እናወራዋለን፡፡
ቴዎድሮስ፡- እንደው የልጅን ነገር ስታነሳ ልጅህ ገና 1ኛ ዓመቱን ነው ያከበረው፡፡ እንደው ምናልባት ባለ ልጅ ስትሆን የመኖር ፍላጎት በጣም አድሮብህና ሕይወት አጓጉቶህ ይሆን ትግሉ ይቅርብኝ ያልከው?
ሠለሞን፡- ኖኖ! ስለ ልጅ ጉዳይ አይደለም፡፡ አንተ ከባድ ጥያቄ ነው የምታመጣው፡፡ ቴዲ (ቴዎድሮስ ነው ያልከኝ ስምህን አይደል?) ዙሪያውን፣ ዳርዳሩን ትዞራለህ፡፡ ኃይለኛ ነህ (በጠረጴዛው ዙሪያ የነበርነውን ሁሉ ተሳሳቅን) የቱን ከየቱ ነው ልታገናኘው የፈለከው? እኔ ከልጅም በላይ እድሜ ት/ቤት ሆኖኛል፡፡ ይሔ ህዝብ በሰላም መኖር እንደሚፈልግ እዚህ ከመጣሁ በኋላም ተረድቻለሁ፡፡ እኛ ነን በሠላም የተቀመጠውን ሕዝብ ‹‹ተነስ›› የምንለው፡፡ አሁን ለምሳሌ ከመጣሁ በኋላ ወዳጆቼ ምሳ ሊጋብዙኝ ወስደውኝ ምግብ ቤቱ ውስጥ ያገኘሁት አስተናጋጅ ሲያየኝ ‹‹ሠሌ መጣህ? እግዚአብሔር ይመስገን፡፡ ከዚህ በኋላ መንገድ ላይ ውጣ የሚለኝ ሰው የለማ! እኔ የአንተን ዘፈን እየሰማሁ አራት ጊዜ ለተቃውሞ ወጥቻለሁ›› አለኝ ።
ቴዎድሮስ፡- ይህን ሲልህ ምን ተሰማህ?
ሠለሞን፡- እምባዬ ዓይኔ ላይ መጣ፡፡ ‹‹ሌሎቹም ይምጡልን›› ነው ያለኝ፡፡ እውነቴን ነው፡፡ ‹‹የአንተን ዘፈን ስሰማ በል በል ይለኛል›› አለ፡፡ ‹‹ሌሎቹም ዘፋኞች ይምጡ፡፡ እኛ ሠላም ነው የምንፈልገው፡፡ እዚህ አስተናግጄ አምስትና አስር ብር ማግኘት ነው የምፈልገው›› አለ፡፡ ተመልከት እንዴት ጭንቅላትህ እንደሚነካ፡፡
ቴዎድሮስ፡- ወደዚያ ከሄድክማ ከእሱ ይልቅ ጭንቅላት የሚነካ ሌላ ጉዳይ አለ፡፡ ይህ ልጅ በአንተ ዘፈኖች ተገፋፍቶ ወጥቶም ዛሬ በሰላም መኖሩን ቀጥሏል፡፡ ግን ከእሱ በተመሳሳይ ያንተን ዘፈኖች አምነው ለተቃውሞ ወጥተው የሞቱና የታሰሩ አሉ፡፡ እነሱንስ ታስባቸዋለህ?
ሠለሞን፡- እ . . . ለዚህ የምሰጠው መልስ የለኝም፡፡ በእኔ ዘፈን የሞተ ሰው መኖሩን መናገር አልችልም፡፡ መኖሩንም አላውቅም፡፡
ቴዎድሮስ፡- እናመሰግናለን፡፡
ሠለሞን፡- ለእኔም እግዚአብሔር ይስጥልኝ፡፡
(‹‹ቁምነገር›› መጽሔት ቅጽ 6 ቁጥር 66 ሐምሌ 1999 ዓ.ም)

