ሕንድና ፓኪስታን – ታሪካዊ ባላንጣዎች

ከሰሞኑ የሕንድ ተዋጊ ጀቶች የፓኪስታንን ድንበር ተሻግረው ጃይሽ ኢ – ሙሐመድ በሚባለውና ፓኪስታን ውስጥ የሚገኝ ታጣቂ ቡድን ላይ ቅድመ – ራስን የመከላከል ተግባር መፈፀማቸውን የሀገሪቱ የውጪ ጉዳይ ሚኒስቴር ማስታወቁ በሁለቱ ጠላት ሀገራት መካከል የነበረውን የረጅም ዘመናት ቁርሾ እንዳይቀሰቅስ ተሰግቷል፡፡ ፓኪስታንም በወታደራዊ ቃል አቀባይዋ በኩል በሰጠችው መልስ የሕንድ ተዋጊ ጀቶች ላይ በመጡበት ቅጽበት የመከላከል እርምጃ ወስጃለሁ ብላለች፡፡ ቪጄይ ጎክሀል የተባሉት የሕንድ የውጪ ጉዳይ ሚኒስትር ጀቶቹ ዒላማቸውን መምታታቸውንና የጃይሽ ኢ – ሙሐመድ ቡድንን አሸባሪዎች፣ ሰልጣኞችና ዋና አዛዦች እንዲሁም በቡድኑ የሚሰለጥኑ የሌሎች አሸባሪዎች አባላትን ተግባር ማምከኗን ነው የተናገሩት፡፡

የሀገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትር ናሬንድራ ሞዲ ሀገሪቱ በአስተማማኝ እጅ ላይ መሆኗን ተናግረው ‹ሕንድ አንገቷን እንድትደፋ እንደማላደርግ በዚህች መሬት ቃል እገባለሁ› ማለታቸው ተዘግቧል፡፡ ፓኪስታን በበኩሏ በጠቅላይ ሚኒስትሯ ኢምራን ካን የሚመራ የውጪ ጉዳይ ሚኒስትሮች፣ የመከላከያና የገንዘብ ሚኒስትሮች እንዲሁም ሌሎች ባለስልጣናት የተሳተፉበት ስብሰባ ካከናወነች በኋላ ሕንድ በየትኛውም ቦታና ሰዓት ለምታደርገው ጥቃት ፈጣን ምላሽ እንደምትሠጥ አሳስባለች፡፡ ከቀናት በኋላም በወታደራዊ ቃል አቀባይዋ በኩል ይፋ ባደረገችው መረጃ የአየር ክልሏን ጥሰው የገቡ ሁለት የሕንድ አውሮፕላኖችን መጣሏንና አንድ አውሮፕላን አብራሪ መያዟን ገልጻለች፡፡

የፓኪስታን ነዋሪዎችና ጋዜጠኞች በሕንድና በፓኪስታን ከምትመራው ካሽሚር ግዛት በስልሳ ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ በምትገኘው ማንሴህራ ከተማ የአውሮፕላኖችና የፍንዳታ ድምጽ መስማታቸውን ለአልጀዚራ ተናግረዋል፡፡ ካሽሚር ደግሞ ሁለቱ ሀገራት ካደረጓቸው አራት ጦርነቶች መካከል ሦስቱን ለማድረግ የመጣያ ምክንያታቸው የሆነች ግዛት ናት፡፡ በደቡብ ኤዥያ በሚገኙት ጎረቤት ሀገራት መካከል ያለው አለመግባባት መካረር የጀመረው ባለፈው የካቲት 14 ቀን (እ.ኤ.አ) በአንድ አጥፍቶ ጠፊ በተፈፀመ አደጋ 42 የሕንድ የደህንነት ሠራተኞች መገደላቸውን ተከትሎ ነው፡፡ ጥቃቱ የተፈፀመው በፓኪስታን ቁጥጥር ስር ነው በሚል ምክንያት ከዚያ ዕለት ጀምሮ ሕንድ ፓኪስታንን ስጋት ውስጥ የሚከቱ ተደጋጋሚ ወታደራዊ እንቅስቃሴዎች በማድረግ ላይ ትገኛለች፡፡ ጃይሽ ኢ – ሙሐመድ የሚባለው በፓኪስታን የሚገኝ የሽብር ቡድን ጥቃቱን መፈፀሙን አምኗል፡፡ ፓኪስታን በበኩሏ በድርጊቱ እጇ እንደሌለበት ነው የገለጸችው፡፡

ካሽሚር – የውዝግቧ ግዛት

ሁለቱ ሀገራት በካሽሚር ግዛት ወደ ውዝግብ የገቡት እ.ኤ.አ ከ1947 ጀምሮ ነበር፡፡ በወቅቱ የግዛቷ አስተዳዳሪ የነበሩት ሀሪ ሲንግ ወደ ሕንድ ለመጠቃለል መምረጣቸውን ተከትሎ በሀገራቱ መካከል ጦርነት ተካሔደ፡፡ በ1965 እና በ1999ኝም እንዲሁ በግዛቷ ‹ትገባኛለች› ሰበብ ጦርነት ውስጥ ገብተው ነበር፡፡ አብዛኞቹ የካሽሚር ነዋሪዎች በሕንድ ከመመራት ይልቅ ወይ በፓኪስታን መጠቃለል ወይም ነፃ መሆን ይመርጣሉ፡፡ ከጃሙ እና ካሽሚር ከተሞች ነዋሪዎች መካከል 60 በመቶ የሚሆኑት የእስልምና ዕምነት ተከታዮች መሆናቸውም ካሽሚርን ሙስሊም ዜጎች የሚበዙባት ብቸኛዋ የሕንድ ግዛት ያደርጋታል፡፡ ከፍተኛ የሥራ አጥ ቁጥርና በጸጥታ አካላት የሚደረጉ ጥብቅ ቁጥጥሮች የግዛቷ ነዋሪዎች ሕይወታቸውን በምሬት እንዲመሩ ያስገደደ በመሆኑ ከጸጥታ አካላት ጋር መጋጨትና ለጉዳትና ለሞት መዳረግ ለግዛቷ አዲስ ነገር አይደለም፡፡ ሕንድና ፓኪስታን ለረጅም ዓመታት በመካከላቸው የቆየውን ግጭት ለማርገብ እ.ኤ.አ በ2003 ወደ አዲስ ምዕራፍ የሚያሻግራቸውን የተኩስ አቁም ስምምነት ተፈራርመው የነበረ ቢሆንም ከ2014 ወዲህ በፓኪስታን የመሸገው የሽብር ቡድን በፑንጃቧ ሰሜናዊ ክፍል በምትገኘው ፓታንኮት ከተማ ላይ የፈፀመውን ጥቃት ተከትሎ ግጭታቸው መልሶ አገርሽቷል፡፡ እ.ኤ.አ በ2016ትም በግዛቷ በሚገኘው የሕንድ ወታደራዊ ቡድን ላይ ከፓኪስታኑ የሽብር ቡድን ተደጋጋሚ ጥቃቶች ሲሰነዘሩበት መቆየታቸው አይዘነጋም፡፡

ዘንድሮ ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ የሚጠብቃቸው የሕንዱ ጠቅላይ ሚኒስትር ናሬንድራ ሞዲ የካሽሚር ጉዳይ ላይ ቅንጣት የሚደራደሩ አይመስሉም፡፡ ‹‹ትግላችን ለካሽሚር እንጂ በካሽሚራውያን ላይ አይደለም፡፡ ካሽሚራውያን በሽብር ምክንያት ብዙ ተሠቃይተዋል፡፡ የሀገሪቱ ሌሎች ዜጎችም ከጎናቸው ሊቆሙ ይገባል›› ብለዋል፡፡ እ.ኤ.አ ከ1989 ጀምሮ በፓኪስታን የሚገኙ አሸባሪዎች በሕንድ ቁጥጥር ስር በሚገኝ የካሽሚር ግዛት ላይ በሚያደርሷቸው ጥቃቶች ሰባ ሺህ ያህል ሰዎች መሞታቸው ይነገራል፡፡

ወታደራዊ አቅማቸው

1.4 ሚሊየን ወታደሮች ያሏት ሕንድ እ.ኤ.አ በ2018 ብቻ ሃምሳ ስምንት ቢሊየን ዶላር ለወታደራዊ ኃይሏ መድባለች፡፡ 653 ሺህ 800 ያህል ወታደሮች ያሏት ፓኪስታን በበኩሏ 11 ቢሊየን ዶላር ነበር በተመሳሳይ ዓመት የመደበችው፡፡ በዚሁ ዓመት ከውጪ ወታደራዊ ድጋፍ ያገኘችው ገንዘብ 100 ሚሊየን ዶላር የሚደርስ ነው፡፡

ሁለቱም ኒውክሌር መሣሪያዎችን መተኮስ የሚችሉ ተወንጫፊ ሚሳዔሎች ባለቤቶች ናቸው፡፡ ሕንድ ዘጠኝ ዓይነት ሚሳዔሎች ያሏት ሲሆን ፓኪስታንም እንዲሁ በቻይና ድጋፍ የተሠሩ ከአጭር እስከ መካከለኛ ርቀት የሚደርሱ ሚሳዔሎች አሏት፡፡ ወደየትኛውም የሕንድ ግዛት መድረስ የሚችሉም ናቸው፡፡ የሕንድ ሚሳዔሎች ከሦስት እስከ አምስት ሺህ ኪሎ ሜትሮች የሚደርሱ ሲሆን የፓኪስታን ሚሳዔሎች ትልቁ ርዝመት ሁለት ሺህ ኪሎ ሜትር ይደርሳል፡፡

እነኚህ ለተመጣጣኝነት የቀረበ አቅም ያላቸው የኒውክሌር ባለቤቶች ወደ ጦርነት ከገቡ ጦሳቸው ለሌሎችም ሀገራት የሚተርፍ በመሆኑ ትርፍና ኪሳራቸውን አስቀድመው ሊያሰሉ ይገባል ይላሉ የቀጠናው ተንታኞች፡፡

ጠብ ያለሽ በዳቦ?

የሕንድ ቅኝ ገዢ የነበረችው ብሪታንያ እ.ኤ.አ በ1947 ሀገሪቱን የሒንዱ እና የሙስሊም ሀገራት ብላ ለሁለት መክፈሏን ተከትሎ ክፍፍሉ በዓለማችን ላይ ታይቶ የማይታወቅ የሰዎች ፍልሰትና በቀጠናውም የማይሽር የጠላትነት ጠባሳ ጥሏል፡፡ የመጀመርያው የሀገራቱ ጦርነት የተነሳው አወዛጋቢዋን የካሽሚር ግዛት ለመውረር የመጡ የፓኪስታን አሸባሪዎችን መግታት እንዲችል የግዛቷ አስተዳዳሪ የሕንድን መንግሥት ድጋፍ መጠየቁን ተከትሎ ነበር፡፡ በ1947 የጀመረው ጦርነት በ1949 በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት አማካኝነት በተካሔደ የተኩስ አቁም ስምምነት ነበር የተጠናቀቀው፡፡

እ.ኤ.አ በ1965 ሁለተኛ ጦርነታቸው ተጀመረ፡፡ በድጋሚ በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ሸምጋይነት የተኩስ አቁም ስምምነት ላይ ደርሰው የነበረ ቢሆንም ከስድስት ዓመት በኋላ ለሦስተኛ ጊዜ ጦርነት ውስጥ ለመግባት ተገደዋል፡፡ የሰሞኑን ወታደራዊ ትንኮሳ ተከትሎ ሀገራቱ ለአምስተኛ ጊዜ ወደ ጦርነት እንዳይገቡ ስጋት ያደረባቸው ሀገራት ከወዲሁ ምክራቸውን መለገሥ ጀምረዋል፡፡

ቻይና እና አሜሪካ

ቻይና የሁለቱ ሀገራት ሰሞነኛ ጉዳይ እንዳሠጋት በውጪ ጉዳይ ሚኒስትሯ በኩል ገልጻለች፡፡ ‹‹ሁለቱ ሀገራት ወደ መረጋጋት ሊመጡ ይገባል፡፡ ለውይይት አመቺ ሁኔታ በመፍጠር በደቡብ ኤዥያ ዘላቂ ሰላም እንዲፈጠር ማድረግ አለባቸው›› ብላለች ጎረቤታቸው ቻይና፡፡

የዩናይትድ ስቴትሱ ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ‹‹በጣም አደገኛ ሁኔታ›› ባሉት የሕንድና ፓኪስታን ሰሞነኛ ውጥረት ዙሪያ የተሰማቸውን ስጋት ገልጸዋል፡፡ ባለፈው ዓመት አሜሪካ፤ ፓኪስታን በስሯ ያሉትን አሸባሪዎች መዋጋት አልቻለችም በሚል ምክንያት ለወታደራዊ ድጋፍ ትሰጣት የነበረውን 300 ሚሊየን ዶላር ማስቀረቷ አይዘነጋም፡፡ የሁለቱ ሀገራት ሁኔታ ዘንድሮ እንደ አዲስ ከማገርሸቱ ጋር ተያይዞ በቀጣይ ወዴት ያመራ ይሆን የሚለው ጥያቄ የበርካታ የፖለቲካ ተንታኖች መነጋገሪያ ሆኗል፡፡

Kumneger Media
Kumneger Media
Kumneger Media is a News and Entertainment Website & Channel. Kumneger Media in addition to News and Entertainment it is the hub of Politics, Movies, Drama, Music, Comedy, Documentary and More!

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

ትስስር ይፍጠሩ

325,851FansLike
49,039FollowersFollow
13,194SubscribersSubscribe