የመደ ወላቡ ዩኒቨርሲቲ መምህራን ካቀረቧቸው 104 የጥናት ጽሑፎች መካከል 95ቱን ውድቅ ማድረጉን አስታውቋል። ፕሮፖዛሎቹ ውድቅ የተደረጉት ሙሉ በሙሉ በሰው ሰራሽ አስተውሎት (ኤ.አይ) በመሠራታቸው ነው ተብሏል።
ዩኒቨርሲቲው መምህራን እና ተማሪዎች ሰው ሰራሽ አስተውሎትን አላግባብ እየተጠቀሙ መሆኑን አስታውቋል።
የዩኒቨርሲቲው የሕግ ትምህርት ክፍል መምህር አቶ ዓለሙ ባልቻ እንደገለጹት፤ ከቀረቡት 104 ፕሮፖዛሎች ውስጥ ዘጠኙ ብቻ ኤ.አይን ሳይጠቀሙ ወይም ኤአይን በአግባቡ በመጠቀም የተዘጋጁ ናቸው።
ዩኒቨርሲቲው ዲጂታል ቴክኖሎጂን በሥርዓተ-ትምህርቱ ውስጥ ለማካተት እየሰራ እንደሆነ ተገልጾአል።
ዩኒቨርሲቲው የሰው ሰራሽ አስተውሎት አጠቃቀምን ለመገደብ አዲስ መመሪያ ማውጣቱንም አቶ ዓለሙ ተናግረዋል።
በዚህ መሠረት መምህራን እና ተማሪዎች እስከ 30 በመቶ ብቻ በኤአይ እንዲጠቀሙ ቢፈቀድም፤ የአጠቃቀም መጠኑን ለመለየት ተርኒቲን (Turnitin) የተባለ ሶፍትዌር ጥቅም ላይ እየዋለ እንደሆነ አብራርተዋል።
ሰው ሰራሽ አስተውሎት ቴክኖሎጂ በትምህርት ዘርፍ አዎንታዊ ጎኖች ቢኖሩትም በጥንቃቄ መጠቀም ያስፈልጋል ያሉት መምህር ዓለሙ በተለይም ጥናታዊ ጽሑፎች የባለቤቱን የፈጠራ ክህሎት ሊያንፀባርቁ ይገባል ብለዋል።

