የቀድሞው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን እና የቅዱስ ጊዮርጊስ አጥቂ ሙሉጌታ ከበደ (ወሎየው) ከዚህ ዓለም በሞት መለየቱ ተሰምቷል። የሀገራችን የምንጊዜውም ምርጡ አጥቂ የሚባለው ሙሉጌታ ባጋጠመው ህመም ምክንያት በህክምና ሲረዳ ቆይቶ በዛሬው ዕለት ሰኔ 4 ቀን 2017 ከዚህ ዓለም በሞት ተለይቷል። ሙሉጌታ በኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን እና በቅዱስ ጊዮርጊስ ለበርካታ ዓመታት በስኬት በመጫወት የገዘፈ ስም ያለው ምርጡ አጥቂ ነበር።
የቅዱስ ጊዮርጊስ ድንቅ አጥቂ ሙሉጌታ ከበደ (ወሎዬው) በ1959 ዓ.ም በደሴ ከተማ ይህችን ምድር በመቀላቀል ሃገራችን ካፈራቻቸው የአጥቂ መስመር ተጫዋቾች በቀዳሚነት ስፍራ የተፈረጀ ስለመሆኑ ብዙ የእግር ኳስ አፍቃሪዎች ይስማማሉ፡፡ ወላጆቹ ባወጡለት ስም ሙሉጌታ ከበደ ሲባል በኳስ ክህሎቱ ግን የበርካታ ስያሜ ባለቤት ለመሆን ችሏል፡፡ እግር ኳስ መጫወት የጀመረው በትውልድ ሰፈሩ ገና በልጅነት እድሜው ሲሆን በአካባቢው ለሚገኙ የሰፈር ቡድኖች በመጫወት የድንቅ ክህሎት ባለቤት መሆኑን አስመስክሯል፡፡
በክለብ ደረጃ ከ1974 ዓ.ም እስከ 1976 ዓ.ም ለወሎው ፔፕሲ ክለብ ከመጫወቱ በላይ በፔፕሲ ውስጥ ባደረገው ምርጥ እንቅስቃሴም የሃገራችን ታላቅ ክለብ የሆነው ቅዱስ ጊዮርጊስን የመቀላቀል እድሉን አገኘ፡፡ በ1976 ዓ.ም ክረምት ላይ ፈረሰኞቹን ሲቀላቀል ቋሚ የስራ ዕድል ለማግኘት ከመቻሉ በተጨማሪ በጊዜው ለተጫዋቾች ይከፈል የነበረውን የደሞዝ ክብረወሰን ለመስበር ችሏል፡፡ በቅዱስ ጊዮርጊስ መለያ ከ1977 ዓ.ም እስከ 1989 ዓ.ም ተጫውቶ ማሳለፍ የቻለው ሙልጌታ ከቡድኑ ጋር በኢትዮጵያ ሻምፒዮና ሰባት፣በኢትዮጵያ ጥሎ ማለፍ አንድ፣በአሸናፊዎች አሸናፊ ስድስት በጥቅሉ 14 ዋንጫዎችን ከቡድኑ ጋር በክብር አንስቷል፡፡
ከነዚህ ድሎች በተጨማሪ ሙልጌታ በግሉ የተለያዩ ስኬቶችን ለማግኘት ችሏል፡፡ በቅዱስ ጊዮርጊስ ቆይታው ክለቡን ለድል ለማብቃት የበኩሉን አስተዋፅዖ ከማድረጉበላይ በግሉ በኢትዮጵያ ሻምፒዮና ውድድሮች ላይ በኮከብ ተጫዋችነት እና ግብ አግቢነት ለመሸለም የበቃባቸው ዓመታት የሚጠቀሱ ናቸው፡፡ በግሉ ስኬትን ያስመዘገብኩባቸው ዓመታት በ1977 ዓ.ም፤ በ1978 ዓ.ም እና በ1986 ዓ.ም ኮከብ ግብ አስቆጣሪ በ1978 ዓ.ም፣ በ1980 ዓ.ም እና በ1982 ዓ.ም ኮከብ ተጫዋች በመሆን በኢትዮጵያ ሻምፒዮናዎች ላይ ለመሸለም በቅቷል። የአዲስ አበባ ኮከብ ተጫዋችና ጎል አስቆጣሪ የሆነባቸው ዓመታቶች ነበሩ፡፡
የሙልጌታ ከበደ የቀብር ስነስርአት ሰኔ 5 ቀን 2017 ኮልፍይ በሚገኝው የእስላም መቃብር ቅዱስ ጊዮርጊስ ስፖርት ማህበር አመራሮች ክለባችንና የብሔራዊ ቡድን ተጨዋች፤ቤተሰቦቹና የቅዱስ ጊዮርጊስ ስፖርት ማህበር ደጋፊዎች በተገኙበት ይፈጻማል፡፡

