ረቡዕ ኀዳር 28 ቀን 2015 (አዲስ ማለዳ) በሬጌ የሙዚቃ ስልቶቹ የሚታወቀው አርቲስት ሳሙኤል ብርሐኑ ሳሚ ዳን “ቅጽበት” የተሰኘና 7 የሙዚቃ ሥራዎች የተካተቱበትን ግማሽ (ኢ ፒ) አልበሙን ትናንት ኀዳር 27/2015 ማምሻውን በአዲስ አበባ ማሪዮት ሆቴል አስመርቋል።
በምርቃት ሥነ ስርዓቱ ላይም የአርቲስቱ የቅርብ የሙያ አጋሮች፣ ወዳጅ ቤተሰቦች እና ጥሪ የተደረገላቸው ሌሎች እንግዶች የተገኙ ሲሆን፤ በመድረኩም በአለበሙ ውስጥ የተካተቱ ሙዚቃዎች ሥራዎች ሙሉ በሙሉ፤ ሳሚ ዳን በአሜሪካ በነበረው ጉዞ ወቅት ያዘጋጃቸው ሙዚቃዎች መሆናቸው ተገልጿል።
ድምጻዊው ወደ አገሩ ሲመለስም ከ”መላ ሚውዚክ ሪከርድስ” ጋር በጋራ በመሆን፤ አልበሙን መስራቱም የተነገረ ሲሆን፤ በዚህ “ቅጽበት” በተሰኘው ግማሽ የሙዚቃ አልበም ላይም ከተለያዩ ወጣትና ባለራዕይ ሙዚቀኞችና የሙዚቃ ባለሙያዎች ጋር መጣመሩ ተገልጿል።
ሳሚ ዳን በመድረኩ በአልበሙ የተካተቱ ሙዚቃዎች “የተለያዩ መልዕክት ያላቸውና በህይወታችን አንዳች ለውጥን ሊፈጥሩ ስለሚችሉ ጊዜያት ይተርካሉ።” ያለ ሲሆን፤ በሙዚቃ ሥራዎቹ ለተሳተፉ ወጣት የሙዚቃ ባለሙያዎች ሁሉ ምስጋናውን አቅርቧል።
አክሎም ከአልበሙ ውስጥ “አምባሰል” የተሰኘው የሙዚቃ አልበሙን ከዚህ ቀደም ከሚታወቅበት የሬጌ ስልተ ምት ባለፈ የአምባስለን አጨዋወት በተለየ መንገድ ያቀረበበት መሆኑን ተናግሯል።
ሳሚ ዳን ከዚህ በፊት “ከራስ ጋር ንግግር” እና “ስበት” የተሰኙ ኹለት የሙዚቃ አልበሞች ከዚህ በፊት ወደ አድማጭ ማድረሱ ይታወቃል።

