ሳዑዲ አረቢያ በሚሊዮን ለሚቆጠሩ ግመሎቿ ፓስፖርት ልትሰጥ ነው

ሳዑዲ አረቢያ በሚሊዮን ለሚቆጠሩ ግመሎች ፓስፖርት ለመስጠት ዕቅድ እንዳላት ይፋ አደረገች።

ይህ የሳዑዲ ውሳኔ አገሪቱ በባህል እና ምጣኔ ሃብት ረገድ ትልቅ ሃብት አድርጋ የምትቆጥራቸውን ግመሎች ለመቆጣጠር እና በአግባቡ ለማስተዳደር ያስችላታል ተብሏል።

በዚህ ሳምንት የሳዑዲ አካባቢ፣ውሃ እና ግብርና ሚኒስቴር ባወጣው መግለጫ እርምጃው በማዕከል የሚሰበሰብ አስተማማኝ የመረጃ ቋት እንዲኖር ያደርጋል ብሏል።

አክሎም ግመሎች ፓስፖርት እንዲኖራቸው መደረጉ በዘርፉ “ምርታማነትን እና ውጤታማነትን” ከማበረታታቱ ባሻገር የግመሎቹን ባለቤቶች ለመቆጣጠር ያስችላል ሲል ገልጿል። የአገሪቱ ብሔራዊ መገናኛ ብዙኃን የሆነው አል ኢክህባሪያ ፓስፖርቱ ሽያጭን፣ ከቦታ ቦታ ማጓጓዝን እና ንግድን ለመቆጣጣር ያገለግላል ሲል ዘግቧል።

ከዚህም በተጨማሪ የግመሎቹን ባለቤቶች መብት የሚጠብቅ ሲሆን የባለቤትነት ማረጋገጫም ሆኖ ያገለግላል።የሳዑዲ ባለሥልጣናት እአአ በ2024 ይፋ የሆነን መረጃ በመጥቀስ በአገሪቱ 2.2 ሚሊዮን ግመሎች እንዳሉ ይናገራሉ።

ግመሎች በሳዑዲ ባህል እና ታሪክ ውስጥ ትልቅ ቦታ ያላቸው ሲሆኑ በዋናነት ለመጓጓዣ እንዲሁም የሀብትና የኩራት ምንጭ ተደርገው ይቆጠራሉ።ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ግመሎችን በማዳቀል ከፍተኛ የሆነ የውድድር ኢንዱስትሪ እየተስፋፋ መጥቷል።

በእነዚህ ውድድሮች ላይ የሚያሸንፉ ግመሎች በሺህዎች በሚቆጠር ገንዘብ ይሸጣሉ።ይህ እያደገ የመጣው ንግድ የአገሪቱ ባለሥልጣናት ቁጥጥራቸውን እንዲያጠብቁ አድርጓቸዋል።

በተለይ የግመሎች የቁንጅና ውድድር በሚል የተጀመሩት ፉክክሮች የባለሥልጣናቱን ትኩረት ከሳቡት መካከል ናቸው።የውድድሩ አዘጋጆች የግመሎችን ከንፈር፣ አፍንጫ እና ሻኛ ለማተለቅ የሚሰጡ ክትባቶችን አግደዋል።

የሳዑዲ አረቢያ ባለሥልጣናት ለግመሎች የሚሰጠው ፓስፖርት ግብርናን ያዘምናል፤ የአገሪቱ ባህል ተጠብቆ እንዲቆይ ያደርጋል ሲሉ ተናግረዋል።

SourceBBC News

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

ትስስር ይፍጠሩ

325,851FansLike
49,039FollowersFollow
13,194SubscribersSubscribe