ከዉጭ አገራት በቀጥታ ወደ አገር ዉስጥ ገንዘብ መላክ የሚያስችል ስምምነት ተፈርሟል፡፡
ሳፋሪኮም፣ ዳሽን ባንክ እና ካሽ ጎ በጋራ የፈጸሙት ስምምነት ከዉጭ አገራት በቀጥታ ወደ አገር ዉስጥ ገንዘብ መላክ የሚያስችል ነዉ፡፡
የሶስቱ ተቋማት ስምምነት ኢትዮጵያውያን ከውጭ በቀጥታ በካሽ ጎ ሞባይል አፕልኬሽን አማካይነት ወደ ኤምፔሳ ገንዘብ የሚልኩበትና መቀበል የሚቻልበትን ዕድል ይፈጥራል ተብሏል።
የኤምፔሳ ሳፋሪኮም ዋና ስራ አስፈፃሚ ኤልሳ ሙዞሊኒ፤ይህ ትብብር የፋይናንስ አካታችነትን ለማበረታታት እና አዳዲስ የዲጂታል ፋይናንሺያል መፍትሄዎችን ለማቅረብ የሚያስችል ነዉ ብለዋል፡፡
የዳሸን ባንክ ዋና ስራ አስፈፃሚ ተወካይ፤ ይህ ትብብር ለኢትዮጵያውያን አለም አቀፍ የገንዘብ ልውውጥ አገልግሎትን ለማሳደግ ዕድል የሚፈጥር መሆኑን አንስተዋል፡፡
በዚህ ስምምነት ውስጥ የሐዋላ ገንዘብ ልውውጥን አስተማማኝ ለማድረግ ዳሸን ባንክ የራሱን ሚና እንደሚጫወትም ነዉ የተናገሩት፡፡
የካሽ ጎ ተወካይ በበኩላቸው፤ በካሽ ጎ አፕልኬሽን በኩል የኤምፔሳ ደንበኞች የገንዘብ /የሐዋላ ሕጋዊ ዝውውር እንዲያደርጉ ቴክኖሎጂው መመቻቸቱን ገልፀዋል።

