በሻምፕስ ኤሊሴ አካባቢ በሚገኝ አንድ በጣም ዘመናዊ የፓሪስ የምሽት ክበብ ውስጥ፣ ወንዶች ሳይታዩ በአብዛኛው መካከለኛ እድሜ ያላቸው በደርዘን የሚቆጠሩ ሴቶች ወደ ጭፈራው ወለል ሲገቡ ይታያሉ፡፡
ወንዶች በሌሉበትና ጫና በሌለበት ሁኔታ ለቤተሰብ ምቹ በሆነ ሰዓት የሚካሄዱ የምሽት ክለቦች ለሴቶች ተመራጭ እየሆኑ ነው፡፡ ጀማሬው በእንግሊዝና በጀርመን ሲሆን አሁን በተሻለ ሁኔታ በፈረንሳይ ተወዳጅ ሆኗል፡፡
ይህ ከስራ በኋላ የሚደረግ እንቅስቃሴ ሲሆን ከምሽቱ 1 ሰዓት እስከ ምሽቱ 4 ሰዓት ድረስ ለሴቶች ብቻ የተዘጋጀ ነው፣ በዋናነት እናቶች ላይ ያነጣጠረ ቢሆንም ያላገቡትንም ያካትታል፡፡
ጁሊ የ37 ዓመት የኮሙኒኬሽን ሥራ አስኪያጅ ናት፤” ወደ ክለቡ እንደገባን ወዲያውኑ እንጨፍራለን። የሚባክን ጊዜ የለም። ቀድመን ተገኝተን ተዝናንተን ወደ ባሎቻችንና ልጆቻችን መመለስ እንችላለን” ትላለች።
“ወንዶች አለመኖራቸው ይበልጥ በቀላሉ እንድንዝናና ያስችለናል። የሚተቸንና የሚጎነትለን የለም፤ እናም በፍጥነት እንረጋጋለን።” የምትለው ሌላኛዋ የክለቡ ደንበኛ “በመካከላችን ጠንካራ የሆነ የእህትማማችነት ስሜት አለ። ለማሽኮርመም ወይም ማንንም ለመያዝ እዚህ ጊዜ የለንም – ከምሽቱ 1 ሰዓት እስከ ምሽቱ 4 ሰዓት ድረስ ለመዝናናትና ለመደሰት ብቻ ነው የመጣነው” ስትል ታክላለች።
ሴቶች ወንዶች የሌሉበት ክለብ መምጣታቸው ምን ጠቀሜታ አለው ? የሚል ጥያቄ የቀረበላቸው የክለቡ ደንበኞች የተለያየ ምላሽ ሰጥተዋል፡፡ ሁለት ልጆች ያሏት ኢንደሬ “ወንዶች በዙሪያችን ሲኖሩ፥ ሴቶች ለመልካቸው የበለጠ ትኩረት ይሰጣሉ፥ ስለሚናገሯቸው ይጨነቃሉ፥ ወይምም የምሽኮርመም ግዴታ ይሰማቸዋል። እዚህ ግን እንደዛ የለም” ስትል ሌላኛዋ ተሳታፊ ዲቫ ደግሞ ወንዶች በሌሉበት የምሽት ክበብ እንደሄዱ ለባሎቻቸው ማስረዳት ቀላል ይሆንላቸዋል። በዚህም ባሎች በጣም ደስተኞች ናቸው ብዬ አስባለሁ፥›› ብላለች፡፡ ‹‹ቢያንስ ባለቤቴ እየጨፈረች ነው’ ብለው ባሎች እንዲያስቡ ያደርጋል የምትለው ኤልዛቤት ኢካም ደግሞ ከጓደኞቿ ጋር የምትዝናናበት ምሽት ብቻ እንደሆነ ያውቃሉ። በመሆኑም ባሎች አይቀኑም” ትላለች፡፡
ሴቶቹ በመጠጥ ቤቱ ውስጥ አልኮል የሌለበት ሻምፓኝ፣ ወይን እና እንደ በረዶ ሻይ ያሉ ለስላሳ መጠጦችን ይጠጣሉ። የመግቢያ ዋጋ 48 ዶላር ሲሆን ሳልመን አሳ፣ ፍራፍሬ፣ የቼሪ ቲማቲም እና ማካሮኒን ጨምሮ የተለያዩ ምግቦችን ያጠቃልላል።

