እንደዛሬው የሳተላይት ቴሌቪዥን ጣቢያዎች ሳይበዙ ከ15 ዓመት በፊት ብቸኛውና አማራጩ የቲቪ ጣቢያ ኢቢኤስ ቲቪ ብቻ ነበር፤ ከሁለት ዓመት በላይ ጣቢያው ያለ ማስታወቂያ ገቢ ሲቆይ ዛሬ ያለበት ደረጃ ላይ እንደሚደርስ እምነት ነበራቸው ባለቤቶቹ ፡፡ በወቅቱ ለቁም ነገር መጽሄት ቃለ መጠይቅ የሰጡት (ቅፅ 9 ቁጥር 105 ህዳር 2003)አቶ አማን ፍስሃ ጽዮንና አቶ ነብዩ ጣኡመ ልሳን (የአሁኑ ዋና ስራ አስኪያጅ) ካሳንቺስ የሚገኘው ንግስት ታወር 6ኛ ፎቅ ላይ ሳገኛቸው ከትካዜ ይልቅ ተስፋ ነበር ፊታቸው ላይ የሚነበበው፤ “ጥሩ የምንለውን ነገር ያለ መታከት በመስራት አማራጭ ጣቢያ መሆን እንችላለን” ነበር ያሉኝ፡፡ እንዳሉትም አልቀረም፤ አስቸጋሪ በሆነው የሃገራችን የሚዲያ ምህዳር ውስጥ ምርጫ ብቻ ሳይሆኑ ብልጫም ሆነው ዘልቀዋል፤
ዛሬ የካቲት 4 ቀን 2018 አንዱ የኢቢኤስ ቴሌቪዥን መስራች አማን ተለይቶናል፡፡ጠንካራ ብርቱ ታታሪና እጅግ ሲበዛ ቀና የሆነው አማን በማህበራዊና በመዝናኛው ዘርፍ ትርጉም ያላቸውን ስራዎች ለተመልካች የሚያቀርበውን ኢቢኤስ ቴሌቪዥን በሁለት እግሩ እንዲቆም የአንበሳውን ድርሻ የተወጣ ሰው ነው፡፡ በተለይም ለጀማሪ አርቲስቶች መድረክ ከመስጠት ጀምሮ ኑሮ ላዘነበለባቸው ወገኖች ድጋፍ ማድረጉ የጣቢያው ህልም ትርፍ ከማግኘት በላይ ያደርገዋል፤
አማን ከወሰደው ሃላፊነት በላይ እንደሚተጋ በኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ምክር ቤት ስራ አስፈፃሚነት አብረን በሰራንባቸው ጊዜያት ከቲዎሪ በላይ የሆነ የተግባር ሰው መሆኑን አይቻለሁ፡፡ ከፔንሲልቫኒያ ስቴት ዩኒቨርሲቲ በኦፕሬሽን ማኔጅመንትና ቢዝነስ አድምንስትሬሽን በከፍተኛ ማዕረግ የተመረቀው አማን ቀደም ሲል ከተለያዩ የአፍሪካ ሀገራት ዜጎች ናይጄሪያውያንና ጋናውያን ጋር የፕሮዳክሽን ኩባንያ መስርቶ ይሰራ ስለነበር እነሱ በየሀገሮቻችው የመዝናኛ የቴሌቪዥን ጣቢያ የመሰረቱ በመሆኑ ‹‹ይሄ ድፍረትና ልምድ ኢቢኤስን ለመመስረት መነሻ ሆኖናል›› ይላል፡፡

‹‹አማራጭ ቴሌቪዥን ጣቢያ በህዝብ እየተፈለገ ነገር ግን ለዘመናት ሊኖር ያልቻለ ክፍት የቢዝነስ መስክ በመሆኑ ነው ኢቢኤስን ወደ ማቋቋም የገባነው፡፡›› የሚለው አማን ‹‹ማንኛውም ህፃን ልጅ ከተወለደ በኋላ የሚድህበት፤ የሚቆምበትና የሚራመድበት ጊዜ አለው፤ ከንግድ ደንብ አንፃር በደንብ አስበንበትና አጥንተን ወደ ስራ የገባን በመሆኑ ጣቢያው ገንዘብ የሚሰራበት ዕድሜ ላይ በቅርቡ እንደርሳለን›› በማለት ጣቢያው ዛሬ ላይ ያለውን ስኬት ትላንት የተመለከተ ሰው ነው፡፡
የፕሮግራም ይዘት ፈጥረው ስፖንሰር ፈልገው ከሚመጡ የግል ድርጅቶች ሃምሳ በመቶ በመካፈል ላይ ተመስርቶ የነበረውን የቴሌቪዥን መዝናኛ ፕሮግራም ሞኖፖሊ ሙሉ ፕሮግራሞችን ከመግዛት ጀምሮ በመዝናኛ ፕሮግራሞች ላይ ለሚቀርቡ እንደግዶች ጭምር ገንዘብ በመክፈል ፈር ቀዳጅ የሆነው ኢቢኤስ ቴሌቪዥን በተለይም በመዝናው ዘርፍ ራሳቸውን የቻሉ 2 የፊልምና የሙዚቃ ቻናሎችን በመክፈት ግንባር ቀደም ተመራጭ ጣቢያ እንዲሆን መሠረት በመጣል በኩል የአማን ድርሻ የላቀ መሆኑን መመስከር ይገባል፡፡
ድርጅቶች ይመሰረታሉ፤ መስራቾቻቸው ሲያልፉ ግን ራዕያቸው አብሮ ይከስማል፤ ኢቢኤስ ቴሌቪዥን ግን ከዚህ በተለየ መልክ የታቀደ፤ የተዋቀረና መሰረት የያዘ ጣቢያ በመሆኑ በእርግጠኝነት ሌሎቹ የጣቢያው ባለድርሻዎችና ሠራተኞች አማን ከመዳህ ጀምሮ በሁለት እግሩ እንዲቆም ያደረገውን ጣቢያ ወደ ፊት እንዲራመድና ከኢትዮጵያ ውጭ ጭምር ተፈልጎ የሚታይ ተወዳዳሪ የቴሌቪዥን ጣቢያ እንደሚያደርጉት ይታመናል፤
ቀና ሰዎች አልበረክት እያሉ ነው፤ ግን ምን ይደረጋል?
አማን ነፍስህ በሰላም ትረፍ! (ታምራት )

