በአገራችን የሚገኙ የመንግስትና የግል የጤና ተቋማትን መሰረት አድርገው የሚወጡ መረጃዎች እንደሚያረጋግጡት፣ ከሕመማቸው ለመፈወስና እፎይታን ለማግኘት ወደ ጤና ተቋማት ከሚሄዱ አሥር ህሙማን መካከል፣ ሶስቱ የወገብና የጀርባ ህመም ተጠቂዎች ናቸው፡፡ የጀርባ ህመም በጀርባ አካባቢ ብቻ ተወስኖ የሚቀር ሳይሆን ቀስ በቀስ ወደ አንገት፣ እጅ፣ እግርና ወደ ፊኛ አካባቢ በመተላለፍ የችግሩ ተጠቂ የሆነው ሰው እንደልቡ ለመንቀሳቀስ፣ ዕቃ ለማንሳትና እንደፈለገ ለመዟዟር እንዳይችል ያደርጉታል፡፡
በጀርባ ህመም መንስኤነት የሚጠቀሱ በርካታ ጉዳዮች ቢኖሩም ከእያንዳንዱ ሰው የዕለት ተዕለት ተግባራት ጋር ቀጥተኛ ቁርኝት ያላቸው ጭንቀት፣ ድብርትና የሥራ ጫና የጡንቻ መወጣጠር እንዲፈጠር ያደርጋሉ፡፡ ይህ ደግሞ በጀርባ አካባቢ የሚገኙ ጡንቻዎችና ነርቮች እንዲኮማተሩ ያደርጋል፡፡ በዚህ ሣቢያም ከቀላል እስከ ከባድ ደረጃ ያላቸው የወገብ ህመሞች ይፈጠራሉ፡፡
በዘርፉ የተካሄዱ በርካታ ጥናቶችና ምርምሮች እንደሚጠቁሙት ያልተስተካከለ አቋምና በቂ እንቅስቃሴ ማድረግ አለመቻል የጀርባ ህመም፣ የአንገት ህመም እና ሌሎች ተያያዥ የጤና ችግሮች ይፈጥራል፡፡ ከዚህ በተጨማሪ ለወገብ ህመም በዋንኛ መንስኤነት ከሚጠቀሱት መካከል የዲስክ መንሸራተት፣ የአፈጣጠር ችግር፣ የአካሄድ፣ የአቀማመጥና የአተኛኘት ችግሮች፤ የተመጣጠነ ምግብ እጥረት፣ የምግብ መፈጨት ሥርዓት መስተጓጐል፣ ጡንቻዎችን በአካላዊ እንቅስቃሴ አለማጠንከር፣ እጢዎች፣ የኩላሊት፣ የማህፀን፣ የዳሌ፣ የሪህና የስኳር በሽታዎች እንዲሁም የጨረር ህክምናዎች ተጠቃሾች ናቸው፡፡ አካላዊ ውፍረት ከመጠን በላይ መጨመርና የአጥንት መሸርሸር ችግርም ለወገብ ህመም መንስኤ ሊሆኑ ይችላሉ፡፡
በዚህ ቪዲዮ የነርቭ ስፔሻሊስት ሐኪም የሆነችው ዶ/ር ሐና ክፍሉ ስለ ወገብ ህመም አደገኛ ምልክቶች እና እንዴት በቤት ውስጥ ማከም ፣ መቼስ ወደ ጤና ተቋም መሄድ አለብን የሚለውን ትነግረናለች ።

