አስቀድሞ እውቅና ላላቸው ሰዎች አልያም በሰዎች ዘንድ ተወዳጅነት አላቸው ተብለው ለሚታሰቡ ሰዎች ሽልማት በመስጠት የራሳቸውን ዝና ለመገንባት ስለሚሯሯጡ ሰዎችና ተቋቁመው ዓመት ሳይሞላቸው ስለሚከስሙ የሽልማት ድርጅቶች ከዚህ በፊት በስፋት ፅፈናል፡፡ አሁን ደግሞ በታዋቂ ሰዎች ስም ስለሚነግዱና የግላቸውን ኪስ ስለሚያደልቡ የሽልማት ድርጅቶች አንዳንድ ነገሮችን እናነሳለን፡፡ ቃላቸውን ጠብቀው ሽልማቱን ወዲያውኑ የሚሰጡ እንዳሉ ሁሉ አንዳንዶቹ ሸላሚ ድርጅቶች ለሙያተኛው እንሸልማለን ብለው ከስፖንሰሮች ገንዘብ ከወሰዱ በኋላ በአደባባይ ‹ሸልመናል› ቢሉም የውሃ ሽታ ሆነው ይቀራሉ፡፡ ሌሎቹ ደግሞ ከሽልማቱ ላይ ኮሚሽን ሲጠይቁ ከዚህ አለፍ ያሉት ደግሞ ሽልማቱን ለመስጠት ‹‹የስሙኒ ዶሮ የብር ገመድ ይዛ ጠፋች!›› የተሰኘውን ብሂል ተግባራዊ ያደርጋሉ – በማመላለስ! ጓደኞቻቸውን ስለሚሸልሙና በሃገር ልጅነት የሚሰጠውን ሽልማት እን ሽልማት ሳንቆጥር ረስተን ማለት ነው፡፡
በበጎዎቹ እንጀምር
ከጥቂት ወራት በፊት ለአንጋፋው ጋዜጠኛ ደረጀ ኃይሌ 60ኛ ዓመት የልደት በዓሉን ምክንያት በማድረግ በተዘጋጀ ፕሮግራም ላይ ለደረጄ ብቻ ሳይሆን በስፍራው ለታደሙ እንግዶችን ለድንገቴ ፈንጠዝያ/ ሰፕራይዝ/ የዳረገ ስጦታ ተበርክቶለት ነበር፡፡ ጃምቦ ሪል ስቴት ካስገነባቸው የመኖሪያ ቤቶች መሀከል ባለ ሶስት መኝታ ቤት በመሸለም በጋራ የማስታወቂያ ስራ እንዲሰራ ግብዣ ሲያቀርብለት ታሜሶል ኮሚዩኒኬሽን ደግሞ የቢዋይዲ የኤሌትሪክ መኪና ሸልሞታል፡፡ ጋዜጠኛ ደረጀ በኢትዮጵያ ሚዲያ ውስጥ ካበረከተው አስተዋፅኦ አንፃር ሽልማቱ ተገቢ ተደርጎ በብዙዎች ዘንድ ተወስዷል፡፡ደረጀ በወቅቱ ለተደረገለት ሽልማት ስፖንሰሮቹንና የሙያ ጓደኞቹን ለማመስገን ቃላት አጥሮት ታይቷል፡፡
ከጥቂት ሳምንታት በፊት ደግሞ የሌላው የኪነት ሰው የጌትነት እንየው 68ኛ ዓመት የልደት በዓል በኢትዮጵያ ብሔራዊ ቴአትር ሲከበር ተመሳሳይ እጅን አፍ ላይ የሚያስጭን ሽልማት ለጌትነት ተበርክቶለታል፡፡ ሁለገቡ የጥበብ ሰው ላለፉት 50 ዓመታት በቴአትር መድረክ ላይ የነገሰ ከመሆኑ አንፃር የሰራቸው የቴአትር፤ የመድረክ፤ የፊልምና የግጥም ስራዎች ድንቅ ብቃቱን ግልፅ አድርገው የሚያሳዩ ናቸው፡፡ ይህን የዘመናት አገልግሎቱ መነሻ በማድረግ የተስፋ የኪነጥብብ ኢንተርፕተራይዝ ባለቤት በተፈራ ወርቁ መሪነት የሙያ ጓደኞቹን በማስተባበር ልደቱን ለማክብር እንቅስቃሴ ሲጀመር ትርጉም ያለው ስጦታ እንዲበረከትለት ብዙ ቦታዎች ስፖንሰር ፍለጋ መሄድ አላስፈለጋቸው ነበር፡፡ የጌትነትን ድንቅ ብቃትና የዘመናት አበርክቶ የተረዱ ሁለት ለስማቸው የሚጨበቁ ድርጅቶች ዳጎስ ያለ ሽልማት መድረክ ላይ አበርክተውለታል፡፡
በኢትዮጵያ የባንክ ዘርፍ ግንባር ቀደም ከሆኑ የፋይናንስ ተቋማት መሀከል አንዱ የሆነው አቢሲኒያ ባንክ የ5 ሚሊዮን ብር ቼክ ሲሰጠው ሌላው በማህበራዊ አገልግሎት ላይ ስሙን እየተከለ የመጣው ሀበሻ ቢራ የቢዋይዲ የኤሌትሪክ መኪና ቁልፍ አስረክቦታል፡፡ እውቅና መስጠትንም ሆነ ሙያተኛ ማክበር በዚህ መልኩ ሲሆን ትርጉም ይሰጣል፡፡ ምሳሌነቱም የላቀ ነው፡፡ አቢሲኒያ ባንክ በማህበራዊ ትስስር ገፁ ባወጣው መልዕክት ተጨማሪ ክብር ለጌትነን እንደሚሰጥ ይፋ አድርጓል እንዲህ ሲል‹ኑ ጌትነትን እናመስግነው በሚል የሁለገቡ ከያኒ ጌትነት እንየው የ68ኛ ዓመት የልደት በአልና የ43 ዓመታት የሙያ አገልግሎት የምስጋና መርሐ-ግብር በኢትዮጵያ ብሔራዊ ቴአትር መከበሩን ተከትሎ ባንካችን አቢሲንያ ለታላቁ ከያኒ ጌትነት እንየው የብር 5 ሚሊዮን ሥጦታ አበርክቷል፡፡በዚህ ተስፋ የኪነጥበብ ኢንተርፕራይዝ ባዘጋጀው እና በርካታ የጥበብ ቤተሰበች በተገኙበት ልዩ የምስጋና መርሐ-ግብር ላይ ባንካችን አቢሲንያ ለከያኒ ጌትነት እንየው የ5 ሚሊዮን ብር ስጦታ ያበረከተ ሲሆን፣ ለአርባ ሶስት ዓመታት ለኪነጥበብ ላበረከተው ጉልህ አስተዋፅኦ ባንካችን ያለውን ክብር እና አድናቆት በመግለጽ በቅርቡ በባህርዳር ከተማ የሚከፍተውን ቅርንጫፍ በጌትነት እንየው ስም መሰየሙን ሲገልፅ በታላቅ ደስታ ነው›
በዚሁ ዕለት በሌላ አዳራሽ በአዲሱ የህጻናትና ወጣቶች ቴአትር ቤት ይካሄድ የነበረ የፊልም ምርቃትም አንጋፋው ኮሜዲያን ደረጄ ኃይሌን ለድንገቴ ፈንጠዝያ የጋበዘ የገንዘብ ሽልማት ከቴምር ሪል ስቴት ተሰምቷል፡፡ ኮሜዲያን ደረጀ በላለፉት 40 ዓመታት የደበዘዘውን ህይወታችንን በሳቅ ያዋዛ በተጠራበት መድረክ ላይ ሁሉ እየተገኘ ‹ስንት አገኛለው› ብሎ ሳይጠይቅ ስራውን ብቻ የሰራ፤ ሙሉ እድሜውን ለኮሜዲ ሙያ ያበረከተ አይተኬ ኮሜዲያን ነው፡፡ የ‹በቃ ፍቅር › ፊልም አዘጋጆች ይህንን የደረጄን አስተዋፅኦ ከግምት በማስገባት ፊልማቸውን ሲያስመርቁ እንደተለመደው በአዳራሽ ጭብጨባና ሁካታ ብቻ ሊያደርጉት አልፈለጉም፡፡ እናም ከክብር ካባውና ዋንጫው በተጨማሪ በሪል ስቴት ዘርፍ ከተሰማራው ቴምር ሪል ስቴት ጋር በመነጋገር አንድ መቶ ሺ ብር ሽልማት ተበርክቶለታል፡፡ ኮሜዲያን ደረጄ ሸልሙኝ፤ አክብሩኝ የማይልና ስለ ራሱ መናገር የማይሆንለት ሙያተኛ ከመሆኑ አንፃር ከዚህ በላይ የሚገባው ኮሜዲያን መሆኑን መመስከር ያስፈልጋል፡፡
ሙሉ እድሜያቸውን ለኢትዮጵያ ኪነ ጥበብ ሰጥተው ስራቸውን ሲሰሩ የግልና የቤተሰብ ህይወታቸውን በአግባቡ ለማቃናት ላልቻሉ ሙያተኞች አጋጣሚውን በመጠቀም የማገዝና ለስራዎቻቸው እውቅና መስተትና አክብሮት የመስጠት ባህል ሊዳብርና ሊበረታታ የሚገባው እንደሆነ እናምናለን፡፡ ከዚህ በተቃራኒው የሚሄዱና ‹እናከብራችኋለን›› ብለው ጠርተው ክብር የሚነኩ የሽልማት ድርጅት አዘጋጆች መኖራቸው ሳይዘነጋ ማለት ነው፡፡
ወደ ሌላ የሽልማት ፕሮግራም ስናልፍ ከጥቂት ሳምንታት በፊት ይካሄዳል ተብሎ ጋዜጣዊ መግለጫ ስለተሰጠበት የ11ኛው የጉማ ሽልማትን እናገኛለን፡፡ በዚህ ሽልማት ዙሪያ የዚህ ፅሑፍ አዘጋጅ አንድ መጣጥፍ ብጤ በማህበራዊ ሚዲያ ላይ ፕሮግራሙ ከመካሄዱ በፊት ለጥፎ ነበር፡፡ የፅሑፉ ይዘት የዕድሜ ልክ አገልግሎት ተሸላሚ ተብለው የታጩትን ሁለት አንጋፋ አርቲስቶች ክብራቸውን እንዲጠብቁ የሚማልድ ነበር፡፡ እነሆ!
‹‹ እነዚህ ሁለት እንቁ አርቲስቶችን የማያውቅ የኪነጥበብ ቤተሰብ አለ ለማለት አይቻልም፡፡ በኢትዮጵያ የቴአትር ሙያ ውስጥ በየዘመናቱ መስዋዕትነትን የከፈሉ ኮከቦችን እንጥራ ብንል አርቲስት ፍቅርተ ጌታሁንና አርቲስት ወለላ አሰፋን ከቶም ቢሆን ልንዘነጋቸው አንችልም፡፡ ላለፉት 50 ዓመታት በመድረክ ቴአትር፤ በራዲዮ ድራማ፤ በፊልምና በቴሌቪዥን ድራማዎች ላይ የጥበብ ቤተሰቡን ሲያዝናኑ የኖሩ ኮከቦች ናቸው፡፡
ስለሙያቸው እንጂ ስለራሳቸው ለመናገር የማይሆንላቸው እነዚህ አርቲስቶች በየጊዜው እየተቋቋሙ የሚፈርሱት የሽልማት ድርጅቶች ለምን ይሆን የድካማቸውን ያህል ክብራቸውን የሚመጥን እውቅናና ሽልማት የማይሰጧቸው ? የሚል ቅሬታ አዘል ፅሑፍ ከዚህ ቀደም ማስመነበቤ ይታወሳል፡፡ የኢትዮጵያውያን ኩራት የሆነው የኢትዮጵያ አየር መንገድ እንኳ አዳዲስ የጉዞ መስመሮችን ሲከፍት እንዴት እንደነዚህ አይነት አንጋፋ ሰዎችን መመልከት አልቻለም የሚል ሃሳብም ሰንዝሬያለሁ፡፡ ነገሩ መስመር ሳይዝ አልቀረም፡፡አየር መንገዱ ዝርዝር ውስጥ ሳይገባ ‹Noted› የሚል ምላሽ ሰጥቶኛል፡፡
በቅርቡ 11ኛው የጎማ አዋርድ እነዚህን እንቁ አርቲስቶች የህይወት ዘመን ተሸላሚ አድርጎ እንደመረጠ በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ መነገሩ ይበል የሚያሰኝ ነው፡፡ ነገር ግን 50 ዓመት ሙሉ ላገለገሉ እነዚህ አርቲስቶችን የሚመጥን ምን ሊሸልም? ምን እውቅና ሊሰጥ ነው? የሚለው ጥያቄ አነጋጋሪ ነው፡፡ ከዚህ በፊት እውቅና ‹ተሰጣቸው!› የተባሉ አርቲስቶች የእንጨት ዋንጫና ሰርተፍኬት እንደተሰጣቸው ይታወሳል፡፡ በነገራችሁ ላይ በጉማ አዋርድ ብቻ ሳይሆን በሀገሪቱ ውስጥ ብቅ ጥልቅ የሚሉት ሁሉም የሽልማት ድርጅቶች ከፍተኛ የሚባል የስፖንሰር ገንዘብ ከሰበሰቡ በኋላ እንደነ ወለላ አይነት አንጋፋ አርቲስቶችን የሚጠሯቸው መድረክ ለማዳመቅና ሰርተፍኬት ለመስጠት እንደሆነ ታይቷል፡፡ ይባስ ብሎማ አንዳንድ የሽልማት ድርጅቶች አክብረው ለጠሯቸው አርቲስቶች መድረክ ላይ ካባ አልብሰው ፎቶግራፍ እንዲነሱ ካደረጉ በኋላ ከመድረክ ጀርባ ‹ካባውን ተከራይተን ያመያጣነው በመሆኑ አውልቁ!› ብለው ሲገፏቸው ታዝበናል፡፡
ለመሆኑ እንደዚህ አይነት ትላልቅ የሽልማት ዝግጅት ሲዘጋጅ ለሆቴሉ ኪራይ ፤ለመድረክ ግንባታው፤ ለዲኮሩ፤ ለቀይ ምንጣፉና ሌሎች ወጪዎች በሚሊዮን የሚገመት በጀት ሲመድቡ የእድሜ ልክ አገልግሎትን ለማክበር ለጠሯቸው አርቲስቶች ሽለማት የሚሆን በጀት የማይዙት ለምንድነው? ንቀት ወይስ አርቲስቶቹ በተደላደለ ኑሮ ላይ ስላሉ የገንዘብ ሽልማት አያስፈልጋቸውም ነው? ሁኔታው የአደባባይ ሚስጥር ይመስላል፡፡
ለፕሮግራሙ ድምቀት፤ ለጥሪ ካርድ ህትመት፤ ለቴሌቪዥን እይታና ለሬድ ካርፔቱ ሽር ጉድ የአለባበስ ኮድ እስከማውጣት ሲደረስ የህይወት ዘመን ተሸላሚዎቹ ምን ለብሰው እንዲገኙ፤ በምን ሁኔታ ተዘጋጅተው እንዲመጡ ታስቧል? በአንዳንድ የሽልማት ፕሮግራሞች ላይ ‹ሸላሚ› ተብለው የተጠሩ አንጋፋ አርቲስቶች ከሸለሙ በኋላ ወደቤታቸው ለመሄድ ታክሲ ሲጠብቁና የሚሸኝ ሰው ራይድ ፍለጋ በር ላይ ቆመው አይናቸው ሲንከራተት መታየታቸው የዘወትር ገጠመኛችን ነው፡፡
ስፖንሰሮችስ?
ለእንደዚህ አይነት ፕሮግራሞች በሚሊዮን የሚቆጠር ገንዘብ ድጋፍ ሲያደርጉ በፕሮግራሙ ዋና ይዘት ላይ ባይወስኑ እንኳ እንደነዚህ ላሉ አንጋፋ አርቲስቶች የህይወት ዘመን አገልግሎት እውቅና ሲሰጥ እንዴት ነው ስምና ዝናቸውን የሚመጥን የራሳቸውንም ድርጅት ክብር የሚያስጠራ የገንዘብ ይሁን የአይነት ሽልማት ለመስጠት የማያስቡት? እጃቸው ለምንድነው የማይፈታው? በየቴሌቪዥ ጣቢያው የተጀመሩ የሙዚቃ አይዶል ውድድሮች ላይ እንኳ ለሁለትና ለሶስት ወር የተወዳደሩ ወጣት ድምፃውያን የመኪና ሽልማትና ከሚሊየን ብር ያላነሰ ገንዘብ ሲሸለሙ ተመልክተናል፡፡ አበርክቶአቸው በባለሙያ የማይመዘንበት ትላንት የመጣው ቲክቶክ አዋርድም መኪና የሚሸልምበት ጊዜ ላይ ደርሰናል፡፡ እናስ? 50 ዓመታት ላገለገሉ አርቲስቶች ሰርተፍኬትና የእንጨት ዋንጫ የሚሰጠው በምን አግባብ በምን ሎጂክ ነው?
ለአርቲስቶቹ
ተወዳጆቹ አርቲስቶች ወለላ አሰፋና አርቲስት ፍቅርተ ጌታሁን ስራችሁ ሐውልታችሁ ሆኖ ይኖራል፡፡ ሰርተፍኬትና የእንጨት ዋንጫ ለመቀበል በየመድረኩ መገኘት እናንተን አይመጥንም፤ በእንደዚህ አይነት መድረክ ላይ የሚሰጣችሁ እውቅናንም የወደፊት የስራ ህይወታችሁ ሲቪ ላይ የሚጨምረው አንዳች ነገር የለም! Nothing! ፡፡ ሰርተፍኬት አላችሁ ብሎ ጠይቆ እናንተን ለስራ የሚያጭ ወይም ውል የሚዋዋል ድርጅት የለም፡፡ ቀድሞውኑ ይህንን ሁሉ በስራችሁ ያሳያችሁ ጀግኖች ስለሆናችሁ የሚቀርባች ነገር የለም፡፡ በመሆኑም የ50 ዓመታት ክብራችሁን የሚመጥን እውቅናና ሽልማት እስከሚመጣ ድረስ ስራችሁን ቀጥሎ ባይ ነኝ፡፡ ባይመጣስ? ባይመጣም የሚጎልባችሁ ነገር የለም፡፡
የፕሮግራሙ አዘጋጆች ከስፖንሰር በተቀበሉት ገንዘብ በየዓመቱ ዝግጅት እያዘጋጁ መኪና ሲቀያይሩና ከኮንዶሚኒየም ወደ ሪል ስቴት ቤት ሲዛወሩ ለቲቪና ለቲክ ቶክ ማዳመቂያ ላለመሆን አንዳንዴ ‹እኔ አልገኝም!!› በማለት ራስን ማክበር ሙያውንም ማስከበር ያስፈልጋል፡፡ ይሄ አካሄድ ሁሉንም አርቲስቶች የሚመለከት ነው፡፡ የአንድ አርቲስት መከበር የሁሉም አርቲስቶች ክብር ነው፡፡ የአንድ አርቲስት መዋረድም የሁሉም አርቲስቶች መዋረድ አድርጎ ማሰብ ያስፈልጋል ፤ ነግ በእኔ ነውና! አለበለዚያ ሽልማትና እውቅና እንደረከሰ ይቀጥላል፡፡››አራት ነጥብ!!
ይህ በተባለ ማግስት በፒያሳ አድዋ አዳራሽ የተካሄደው የጉማ ሽልማት እንደተገመተው የ50 ዓመታት አገልግሎት የህይወት ዘመን ተሸላሚዎች ክብራቸውን በማይመጥን መልኩ ሰርተፍኬትና የእንጨት ዋንጫ ተሰጥቷቸው ከምሽቱ አራት ሰዓት ወደ ቤታቸው ተሸኝተዋል፡፡አንጋፋዎቹ አርቲስቶች በእዛ መድረክ ላይ ባይገኙ ይቀርባቸው የነበረው ነገር ምንድነው? ምንም! ታሪካቸው እንኳ በመድረኩ ላይ ሳይነበብ ነው ስማቸው የተጠራው፡፡ ከዚያ ይልቅ ወጣቱ የፊልም ዳይሬክተር ሄኖክ አየለ ነው ሌላ ባለሙያ ለመሸለም ወደ መድረክ በወጣበት ቅፅበት የአንጋፋዎቹን አርቲስቶች ታሪክና ስራ አለመነገሩን ወቅሶ የራሱን ምስክርነት ሰጥቶ ነው ወደ ሽልማት ስነ ስርዓቱ የገባው፡፡
አወዛጋቢው የቲክ ቶክ አዋርድ
ሰሞኑን የተካሄደው 3ኛው ዙር የቲክ ቶክ አዋርድ ብዙ ነገሮችን አሳይቶ ነው ያለፈው፡፡ ከፕሮግራም መሪዎቹ ጀምሮ እስከ ሽልማት ሰጪዎች ማንነትና ስብዕና ድረስ አነጋጋሪ ጉዳዮች በርክተውበት መታየቱ እውነት ነው፡፡ ከባህልና ወጋችን ጋር የተጣረሱ አለባበሶችና ለሰበካ ወደ መድረክ የወጡ ሸላሚዎችን ጨምሮ የተፎካካሪዎቹ የኋላ ስብዕና ትውልዱ ወዴት እየሄደ ነው ማሰኘቱ አልቀረም፡፡ እንዲያም ሆኖ ግን ዘንድሮ ለ3ኛ ጊዜ የተካሄደው የቲክ ቶክ አዋርድ ለ11 ዓመታት ያህል ከዘለቀው ጉማ አዋርድ አንፃር ብዙ ሊባል የሚችል ነገር አሳቶ አልፏል፡፡
ገና እንደ ህፃን ልጅ በእግሩ ለመቆም ድክ ድክ እያለ ያለው የቲክ ቶክ አዋርድ ለተሸላሚዎች ከኤሌትሪክ መኪና እስከ ሚሊዮን ብሮች ድረስ በመሸለም ትኩረት መሳብ ችሏል፡፡ ዝግጅቱ በይዘት ደረጃ ብዙ ሊባልበት የሚችል ቢሆንም ሽልማቱ ሽልማት እንዲመስልና የብዙዎችን መነጋገሪያ መሆን ችሏል፡፡ ድርጅታቸውን ለማስተዋወቅ በብዙ ሚሊዮን የሚቆጠር ብር የሚያወጡ የግል ድርጅቶችም ኢትዮ ቴሌ ኮምን ጨምሮ ቀላል በማይባል ገንዘብ ፕሮግራሙን ስፖንሰር ለማድረግ በመቻላቸው አዘጋጁ ከተገኘው ገንዘብ ላይ ጠቀም ያለ ብር ለትዳዳሪዎቹ ሲሸልም ታይቷል፡፡ ከ7 ነጥብ 6 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ የተደረገበት የሽልማት ስነ ስርዓት ከነጉድለቶቹ ዓመት እየጠበቁ ፕሮግራም ለሚያዘጋጁ ተቋማት ጥሩ ትምህርት ጥሎ ማለፉን መዘንጋት አይገባም፡፡ ተቋማቱ በየዓመቱ ሲመጡ ገቢና ወጪያቸውን ትርፍና ኪሳራቸውን በጀታቸውን ጭምር ለጥበብ ቤተሰቡ በማቅረብ ከጥብብ ቤተሰቡ ጎን በመቆም ግልፀኝነትን ማሳየት ይጠበቅባቸዋል እንላለን፡፡
ይህንኑ በተመለከተ የጉማ አዋርድ አዘጋጆችን በተደጋጋሚ ለማግኘትና ሃሳባቸውን ለመጠየቅ ብንሞክርም ‹አሁን የቲክ ቶክ ና የኦዳ አዋርድ የሚካሄድብት ሳምንት ስለሆነ ወደ ኋላ ተመልሶ ስለጉማ ለመነጋገር ያስቸግራል › የሚል ጥቅል ምላሽ በመስጠታቸው ያደረግነው ጥረት ሊሳካን እንዳልቻለ ለመግለፅ እንወዳለን፡፡

