በሱዳን ብሉ ናይል ግዛት ጌሳን ወረዳ ባለፈው ሳምንት ውጊያው በመጠናከሩ ምክንያት ወደ 22 ሺህ የሚጠጉ ሰዎች ከቀያቸው መፈናቀላቸውን የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሰብዓዊ ጉዳዮች ማስተባበሪያ ቢሮ (OCHA) ማክሰኞ ዕለት አስታወቀ።
የሰብዓዊ ጉዳዮች ማስተባበሪያ ቢሮ ባወጣው መግለጫ፣ የቀጠለው ግጭት የዜጎችን ሕይወት ለአደጋ በማጋለጥ በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎችን ከቤት ንብረታቸው እንዲፈናቀሉ እያስገደደ መሆኑን ገልጿል። «በብሉ ናይል ግዛት ጌሳን ወረዳ ባለፉት ሰባት ቀናት ውስጥ በተባባሰው ውጊያ ምክንያት ወደ 22 ሺህ የሚጠጉ ሰዎች መፈናቀላቸውን የአካባቢው ባለሥልጣናት ገልጸዋል» ሲል መግለጫው አመልክቷል።
መግለጫው አክሎም «ብዙዎቹ በትምህርት ቤቶች ውስጥ ተጠልለው የሚገኙ ሲሆን፣ ሌሎች ደግሞ የግዛቷ መዲና ወደሆነችው ኤድ ዳማዚን ጨምሮ ወደ ሌሎች አካባቢዎች ተሰደዋል» ብሏል። ጌሳን የተሰኘው የአካባቢው የእርዳታ አካል እሑድ ዕለት ባወጣው መረጃ፣ በውጊያው እና እየከፋ በሄደው የፀጥታ ችግር ምክንያት በጌሳን ወረዳ ከሚገኘው መዲና 12 ከተባለው አካባቢ ወደ 20 ሺህ የሚጠጉ ሰዎች መሸሻቸውን ገልጿል።
የፈጥኖ ደራሽ ኃይሎች (RSF) እና አጋሩ የሆነው የሱዳን ሕዝቦች ነፃነት ንቅናቄ-ሰሜን በግዛቷ በርካታ አካባቢዎች ላይ ጥቃት መሰንዘራቸውን ተከተሎ በብሉ ናይል ግዛት ባለፉት ሁለት ቀናት አዲስ ውጊያ ተባብሷል።
የሰብዓዊ ጉዳዮች ማስተባበሪያ ቢሮው አክሎ እንዳመለከተው፣ የሰሜን ኮርዶፋን ግዛት ዋና ከተማ ከሆነችው ኤል ኦቤይድ በስተ ሰሜን እና ሰሜን ምዕራብ አቅጣጫ በሚገኙ መንደሮች ላይ ቅዳሜ ዕለት በተፈጸመ ጥቃት ንፁሃን ሰዎች መገደላቸውን፣ መቁሰላቸውን እና መፈናቀላቸውን ገልጾ፣ የሲቪሎች ንብረት እና የቤት እንስሳት መዘረፋቸውን የሚጠቁሙ ዘገባዎች መኖራቸውን ጠቁሟል።
«በምዕራብ ዳርፉር ግዛት ከቻድ ድንበር አቅራቢያ በሚገኘው ዓዴኮንግ የነዳጅ ገበያ ላይ ባለፈው ሐሙስ በተሰነዘረ የድሮን ጥቃት የሲቪሎች ሕይወት ማለፉ እና መቁሰላቸው ተዘግቧል። ጥቃቱ በሲቪሎች ንብረት ላይም ጉዳት አድርሷል» ሲል ድርጅቱ ገልጿል።
የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሰብዓዊ ጉዳዮች ማስተባበሪያ ቢሮ በግጭቱ ተሳታፊ የሆኑ ወገኖች ሁሉ «ሲቪሎችን እና የሲቪል መሠረተ ልማቶችን እንዲጠብቁ፣ ዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብቶች ሕግን እንዲያከብሩ፣ እንዲሁም የሰብዓዊ እርዳታ ድርጅቶች በሰላም እና በነፃነት እንዲንቀሳቀሱ እንዲፈቅዱ» ያቀረበውን ጥሪ ድጋሚ አድሷል።//
በ ሱዳን ብሉ ናይል ግዛት በተካሄደ ውጊያ 22 ሺህ ሰዎች መፈናቀላቸው ተነገረ

