በመዲናዋ በ2017 በጀት ዓመት 6 ወራት ውስጥ ሕግና ስርዓትን ባልጠበቀ መልኩ የሕዝብ ትራንስፖርት አገልግሎት ሲሰጡ በነበሩ ከ99 ሺሕ በላይ አሽከርካሪዎች ላይ እርምጃ መውሰዱን የአዲስ አበባ ትራንስፖርት ቢሮ አስታውቋል።
እርምጃ የተወሰደባቸው አሽከርካሪዎች ከተመደቡበት መስመር ውጪና አቆራርጦ በመጫን፣ ከታሪፍ በላይ እንዲሁም ትርፍ በመጫን ጥፋተኛ የተባሉ መሆናቸውን በቢሮው የሕዝብ ትራንስፖርት ስምሪትና አደረጃጀት ዳይሬክተር አሸናፊ ስዩም ለአሐዱ ገልጸዋል።
በተለያዩ ጥፋቶች 99 ሺሕ 213 አሽከርካሪዎች ላይ የእርምት እርምጃ መወሰዱን አስታውቀዋል።
ሕግና ስርዓቱን አክብረው የሚሰሩ አሽከርካሪዎች በብዛት መኖራቸውን ያነሱት ዳይሬክተሩ፤ በአንፃሩ ያልተገባ ትርፍ ለማግኘት ከሕጉ ውጪ የሚንቀሳቀሱ መኖራቸውን አንስተዋል።
በመሆኑም በተለያየ መንገድ በተቀመጠው የሕግ አቅጣጫ እንዲሰሩ ለማስቻል የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራ በሰፊው እየተሰራበት እንደሚገኝ አስታውቀዋል።

