” ዋናው ነገር ኮንትሮባንድ ንግድ መስራታቸው እንደተጠበቀ ሆኖ ከባንኮች ብድር መውሰጃ እንደሆነ አረጋግጠናል ” – የኢትዮጵያ ነዳጅ አቅራቢ ድርጅት
” ለኮንትሮባንድ ንግድና ብድር ማግኛ ብሎ የገባው ኩባንያ ስርዓት ይይዛል ” – ንግድና ቀጠናዊ ትስስር ሚኒስቴር
በህገወጥ የነዳጅ ግብይት የታየዘ ግለሰብ ነዳጁ ተወርሶ ከ3 ዓመት በማይበልጥ እስራትና እስከ 100 ሺህ ብር የገንዘብ ቅጣት እንዲቀጣ የሚያደርግ ረቂቅ አዋጅ ተዘጋጀ።
ረቂቁ ምን ይላል ?
– አዲስ የነዳጅ ምርት አከፋፋዮች ስራ ለመጀመር ቢያንስ 500 ሺህ ሊትር የነዳጅ ውጤቶች መያዝ የሚችል ማከማቻ / ዴፖ እና 4 ማደያዎችን ማዘጋጀት እንዳለባቸው ያስገድዳል።
– በስራ ላይ ያሉ ማደያዎች ደግሞ አዋጁ ከሚጸድቅበት ጊዜ ጀምሮ ለአዲስ አከፋፋዮች የተጣሉትን ግዴታዎች ማሟላት ይጠበቅባቸዋል።
– አዲስ ጀማሪ ሆኑ ነባሮቹ በ3 ዓመታት ውስጥ ተጨማሪ 6 ማደያዎችን የመገንባት ግዴታ አለባቸው።
– የነዳጅ ውጤቶችን ከተፈቀደው ቦታ ውጭ ያከማቸ፣ ሊሸጥ ከሚገባው ሰው ቦታና የግብይት ስርዓት ውጭ ሲሸጥ የተገኘ ወይም አደጋ ያስከትላሉ በተባሉ መያዣዎች ሲሸጥ የተገኘ ማንኛውም ግለሰብ የተያዘው የነዳጅ ውጤት ተወርሶ ከ3 ዓመት በማይበልጥ እስርና ከብር 50 ሺህ እስከ ብር 100 ሺህ የሚደርስ ቅጣት ይፈጸምበታል።
– መንግሥት ከሚያወጣው የነዳጅ ምርቶች መሸጫ ተመን ውጪ በተደጋጋሚ የመገበያየት ወንጀል እንዲሁም የነዳጅ ምርቶችን ከባዕድ ነገሮች ጋር መቀላቀል እስከ 3 ዓመት እስርና እስከ 300 ሺህ ብር ቅጣት ያስጥላል።
የኢትዮጵያ ነዳጅ አቅራቢ ድርጅት ዋና ስራ አስፈጻሚ እስመለአለም ምህረቱ ምን አሉ ?
አሁን አሁን ወደነዳጅ አቅራቢነት ስራ ለመሰማራት ከፍተኛ ፍላጎት እየታየ ነው ብለዋል።
በድርጅቱ በተደረገው ጥናት ይህ ፍላጎት የኮንትሮባንድ ንግድ እና ከባንክ ብድር ለመወሰድ ተብሎ የሚደረግ እንደሆነ ተደርሶበታል ሲሉ ገልጸዋል።
ዋና ስራ አስፈጻሚው ፥ በዚህ 9 እና 10 ዓመት ውስጥ ከነበሩት 8 ወይም 9 ካምፓኒዎች አሁን 59 መድረሳቸውን ጠቁመዋል።
3ቱ የመንግሥት ገንዘብ አባክነው በፍርድ ቤት ክርክር ላይ ናቸው።
56ቱ ካምፓኒዎችን በማርኬትሼር በመደልደል ነዳጅ እየተሰጠ መሆኑን የገለጹ ሲሆን ” ይህ ሁኔታ እራሱ እስካሁን ስምምነት የሌለበት ሁልጊዜ ጭቅጭቅ ያለበት ድርጊት ነው ” ብለዋል።
ወደ ነዳጅ ግብይት አዲስ የሚገቡ ካምፓኒዎችን በተመለከተ ምንድነው አላማቸው ? ለምንድነው እንዲህ እያደገ የመጣው የሚለው መጠናቱን ገልጸዋል።
በጥናቱ ውጤትም ” ዋናው ነገር ኮንትሮባንድ መስራታቸው እንደተጠበቀ ሆኖ ከባንኮች ብድር መውሰጃ እንደሆነ ነው የተረጋገጠው ” ብለዋል።
እነዚህ የነዳጅ ካምፓኒዎች ባንኮች ጋር ሄደው ብድር በሚጠይቁበት ጊዜ ባንኮቹ ” ከናተ ጋር ያላቸው የሥራ አፈጻጸም ይጻፍልን ” እየተባለ ደብዳቤ እንደሚጻፍ ገልጸዋል።
የንግድና ቀጠናዊ ትስስር ሚኒስትር ካሳሁን ጎፌ (ዶ/ር) ምን አሉ ?
° አዋጁ አላማ መንግሥት በየዓመቱ በሚሊዮን ዶላሮች የሚያወጣበትን ለነዳጅ ምርት በአግባቡ ለማስተዳደር ነው።
° በመንግሥት በኩል የነዳጅ አቅርቦትን የማበራከት አላማ የለም።
° አዋጁ በእያንዳዱ የግብይት ሰንሰለት ውስጥ ባሉት ተዋናዮች ላይ የህግ ሪስትሪክሽኖችን ይጥላል። የአቅራቢ፣ የማደያ … ግዴታዎች አሉ።
° ግብይታችን ችግር አለበት። የአቅርቦት ችግር ሳይኖር ስርጭት ላይ ትልቅ ችግር አለ። የታሰበላቸው ቦታ ያለመድረስን በተመለከተ በክልሎች የሚቀርበው ቅሬታ ገሚሱ ትክክል ነው።
° ነዳጅ አለ !! ሳምንት ሁለት ሳምንት ገበያ ማስራብ ፣ በነዳጅ ማደያዎች ውስጥ ነዳጅ ይዞ ‘ ቤንዚን የለም ፤ ናፍጣ የለም ‘ ብሎ መለጠፍ ይሄ ደግሞ ተጠያቂነት የማያስከትልበት ሴክተራል ባህሪው እንዲቀየር ይታሰባል፤ ይፈለጋል በመንግሥት በኩል ለዛም ነው ይሄ አዋጅ የሚወጣው።
° ከዚህ በኃላ ንግድን አንከለክልም እናሰፋዋለን ፤ ግብይቱ እንዲሳለጥ እንፈልጋለን ነገር ግን ለኮንትሮባንድ ንግድና ብድር ማግኛ ብሎ የገባው ኩባንያ ስርዓት ይይዛል።
° የነዳጅ ኮታ እና ስርጭት ላይ ፍትሃዊ ስርዓት ለመፍጠር ይሰራል።
° ከአቅርቦት እና ስርጭት ይልቅ ማስተዳደሩ ከባድ ነው።
° ነዳጅ እያላቸው ዘግተው የሚቀመጡ ማደያዎች በስፋት አሉ። የቅጣት መጠኑ ላይ ጠንካራ ስራ ይሰራል።
ቲክቫህ ኢትዮጵያ መረጃውን ከሪፖርተር እንዲሁም ከህ/ተ/ም/ቤት የቀጥታ ስርጭት ማግኘቱን ይገልጻል።

