በመፈንቅለ መንግስት ከስልጣን የወረዱት የጊኒ ቢሳው ፕሪዚዳንት ወደሴኔጋል መሸሻቸው ተገለጸ

በሀገሪቱ በወታደራዊ መፈንቅለ መንግስት ስልጣን ላይ በወጡት ኃይሎች ታስረው የነበሩት ፕሬዚዳንት ኡማሮ ሲሴኮ ኢምባሎ ወደሴኔጋል መሸሻቸው የተገለጸው ፕሬዚዳንቱ ያለምንም ቅድመ ሁኔታ እነዲለቀቁ የአፍሪካ ሕብረት ጥሪ ካቀረበ ከሰዓታት በኋላ ነው።

እሁድ ዕለት በጊኒ ቢሳው ፕሬዚዳንታዊና ፓርላሜንታዊ ምርጫ ተካሄዶ ነበር። የምርጫው ውጤት ትናትንና ሐሙስ ሊገለጽ ቀጠሮ ተይዞለት የነበረ ሲሆን ሀገሪቱን ለሁለተኛ ዙር ለመምራት በመወዳደር ላይ የነበሩት ፕሬዚዳንት ኡማሮ ሲሴኮ ኢምባሎ እና ተቀናቃኛቸው ፈርናንዶ ዲያዝ ዳ ኮስታ ግን የምርጫው ውጤት ከመገለጹ በፊት ከማክሰኞ ጀምረው ሁለቱም በየፊናቸው ማሸነፋቸውን መግለጽ ጀመሩ።

በዚህ መካከል ነበር “ብጥብጥ እንዳይከሰትና ሁኔታውን ለማረጋጋት” በሚል በመሃል የገባው የሀገሪቱ ጦር ከአንድ ቀን በኋላ በተደራጁ ከፍተኛ የጦር መኮንኖች አማካኝነት ረቡዕ ዕለት መፈንቅለ መንግስት ማድረጉንና በኃይል ስልጣን መያዙን በሀገሪቱ ብሔራዊ የቴሌቪዥን ጣቢያ ቀርቦ የገለጸው።

መፈንቅለ መንግስቱ የተመራው በራሳቸው በፕሬዚዳንት ኡማሮ ሲሴኮ ኢምባሎ የግል ጠባቂና የሃገሪቱ የፕሬዚዳንታዊ ዘብ ዋና አዛዥ በነበሩት ጀኔራል ዴኒስ ንካና ሲሆን ፕሬዚዳንት በመጨረሻም ፕሬዚዳንት ኢምባሎንም ተቀናቃኛቸው ፈርናንዶ ዲያዝንም በጥጥር ስር በማዋል ማሰሩንም አስታወቀ።

በመጨረሻም ከፍተኛ ወታደራዊ ቡድኑ በትናንትናው ዕለት ጀነራል ሆርታ ንታምን የሀገሪቱ መሪ አድርጎ መሾሙን የገለጸ ሲሆን እርሳቸውም በቀጣይ ለአንድ ዓመት የሀገሪቱ መሪ ሆነው ለማስተዳደር ቃለ መሃላ ፈጽመዋል።

በዚህም በጊኒ ቢሳው በመፈንቅለ መንግስት በኃይል መንበረ ስልጣኑን በተቆጣጠሩት ወታደራዊ መኮንኖች ከረቡዕ ጀምሮ በእስር ላይ የቆዩት ፕሬዚዳንት ኡማሮ ሲሴኮ ኢምባሎ ያለምንም ቅድመ ሁኔታ እንዲፈቱ የአፍሪካ ሕብረት ጥሪ ካቀረበ በኋላ በአሁኑ ሰዓት ተለቀው ወደሴኔጋል መሸሻቸው ታውቋል።

የሀገሪቱ የቀድሞ ቅኝ ገዥ ፖርቱጋል፣ የምዕራብ አፍሪካ መንግሥታት ኢኮኖሚክ ኮሚሽን(በእንግሊዝኛ ምህጻሩ ኢኮዋስ)፣ የአፍሪካ ሕብረትና የተባበሩት መንግስታት በጊኒ ቢሳው የተካሄደው መፈንቅለ መንግስት የሀገሪቱን ሕገ መንግስት የሚጥስ መሆኑን በመግለጽ በሀገሪቱ ሕግና ስርዓት ወደነበረበት እንዲመለስና የሲቪል መንግስት እንዲቋቋም ሁሉም አካላት ወደንግግርና ውይይት እንዲገቡ በማሳሰብ ላይ ይገኛሉ።

ከግማሽ በላይ የሚሆነው ሕዝቧ በአስከፊ ድህነት ውስጥ የሚኖርባት ትንሿ ምእራብ አፍሪካዊት ሀገር ጊኒ ቢሳው በአውሮፓውያን አቆጣጠር በ1974 ከፖርቹጋል ቅኝ ግዛት ነጻ ከወጣች ወዲህ ከዘጠኝ ጊዜ በላይ የተሳኩና ያልተሳኩ የመፈንቅለ መንግስት ሙከራዎች የተካሄዱባት ሀገር መሆኗንና ይህም ሀገሪቱን በማያቋርጥ የፖለቲካ ቀውስ ውስጥ እንድትሽከረከርና ከዓለማችን እጅግ ድሃ አገሮች መካከል አንዷ እንድትሆን ማድረጉን መረጃዎች ያመለክታሉ።

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

ትስስር ይፍጠሩ

325,851FansLike
49,039FollowersFollow
13,194SubscribersSubscribe