የኤርትራ መንግስትና የህወሃት ሀይሎች ዝምታን መርጠዋል፤
ሁለት ዓመት ሊሞላው ጥቂት ሳምንታት በቀረው ደም አፋሳሽ ጦርነት በሰላማዊ ዜጎች ላይ መደፈር፣ ወሲባዊ ጥቃቶች፣ የዘፈቀደ ግድያ እና ረሃብ እንደ ጦር መሳሪያ ጥቅም ላይ መዋላቸውን አዲሱ የተመድ ሰብአዊ መብት ሪፖርት ይፋ አደረገ ።
የኢትዮጵያ መንግስት ሪፖርቱን በይፋ ሲቃወም፤ የትግራይ ሀይሎች ዝምታን መርጠዋል፤
19 ገጾች ያሉትና የመጀመሪያ ግኝት የሆነው ይህ ሪፖርት ይፋ የተደረገው የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሰብዓዊ መብቶች ምክር ቤት፣ በኢትዮጵያ የእርስ በርስ ጦርነት የተፈጸሙ ጥሰቶች በሚያጣራው የሰብዓዊ መብቶች የባለሙያዎች ቡድን ነው።
ለተባበሩት መንግሥታት ሰብዓዊ መብቶች ምክር ቤት በቀረበው ሪፖርት መሰረት ጦርነቱ ከተቀሰቀሰበት ጥቅምት 24/2013 ዓ.ም. ጀምሮ በሰላማዊ ዜጎች ላይ ሆን ተብለው የተፈጸሙ የመብት ጥሰቶች እንደ ጦር መሳሪያነት ጥቅም ላይ ስለመዋላቸው ምክንያታዊ የሆኑ ማስረጃዎች አሉ ብሏል።
ኮሚሽኑ እነዚህ የተፈጸሙ ጥሰቶች የጦር ወንጀሎች እንዲሁም በሰው ልጆች ላይ የሚፈጸሙ ወንጀሎች እንደሆኑም ያምናል ብሏል። የኢትዮጵያ መንግሥት ግን የባለሙያዎቹ ቡድን ሲቋቋም ተቃውሞውን ማሰማቱ ይታወሳል።
የባለሙያዎቹ ቡድን ባወጣው ሪፖርት ላይ ተካተው የጦር ወንጀሎች እና በሰብዓዊነት ላይ የሚፈጸሙ ወንጀሎች ናቸው ከተባሉት መካከል የሚከተሉት ይገኙበታል።
በመቀለ የተፈጸመ የከባድ መሳሪያ ድብደባ
በመቀለ ከተማ በኅዳር 14/2014 ዓ.ም በአቅራቢያው ከነበሩ ተራራማ ስፍራዎች በነበሩ የኢትዮጵያ መከላከያ ኃይል በከባድ መሳሪያ ድብደባ እንደተፈጸመ የዐይን እማኞችን ዋቢ አድርጓል።
በእነዚህ ድብደባዎች በርካታ ሰዎች እንደተገደሉና እንደቆሰሉ ያመለከተው ሪፖርቱ በአይደር ሆስፒታል አንድ የጤና ባለሙያ 15 አስከሬኖች መቁጠሩንና ሆስፒታሉም 27 የሞቱ ሰዎችን መመዝገቡን ገልጿል።
በከተማዋ የተለያዩ ሰፈሮች ህፃናትን ጨምሮ በርካቶች መሞታቸውን ተናግረዋል። ኮሚሽኑ በእነዚህ ጥቃቶች ዘላቂ የሆነ አደጋ የደረሰባቸውንና ከጥቃት የተረፉ ግሰለሰቦችንም አናግሯል፤ ታማኝ የሆኑ መረጃዎችም ከ100 በላይ ሰዎች ላይ ጉዳት ደርሷል ብለዋል።
የኢትዮጵያ መከላከያ መቀለን ከተቆጣጠረ በኋላ ወታደሮቹ መድፈርን ጨምሮ ሌሎች ወሲባዊ ጥቃቶች ያደረሱ ሲሆን የመከላከያ አባላት የፈጸሟቸው መደፈሮች መጠነ ሰፊ በመሆናቸው የጥቃቱ ሰለባ ለሆኑም መጠለያዎች ተቋቁሞ ነበር።
በተጨማሪም ከከተማዋ ሴት ነዋሪዎች ጌጣጌጦችን፣ ገንዘብ እንዲሁም የቤት እቃዎችን ዘርፈዋል። የአፄ ዮሐንስ ትምህርት ቤት እና የአይደር ሆስፒታሎችን ጨምሮ ቢያንስ ከአምስት ወራት ባላነሰ ለጦር ሰፈር መጠቀማቸውን አመላክቷል።
እንዲሁም በኢትዮጵያ አየር ኃይል ሰኔ 15/2013 ዓ.ም. ቶጎጋ ገበያ ላይ በደረሰ ጥቃት 60 ንጹሃን ዜጎች የተገደሉ ሲሆን መከላከያም ንጹሃን ዜጎችን ለማዳን የደረሱ አምቡላንሶችን ለሁለት ቀናት አግዷል ብሏል።
ሪፖርቱ የትግራይ ታጣቂዎች ፈፅሟቸው ያለውን የቶር ወንጀል በቆቦና ጭና ከተሞች የተፈጸሙ ግድያዎች እንደማሳያ አቅርቧል፤
የትግራይ ኃይሉ ወደ አማራ ክልል ገብተው የቆቦን ከተማ ከተቆጣጠሩ በኋላ በከተማዋና በአካባቢው የሚገኙ ወንዶችን ፍለጋ ጳጉሜ 04/2013 ዓ.ም. ጀመሩ።
ይህንን ያደረጉት ጦርነቱ ካቆመ በኋላ ሲሆን የጦር መሳሪያ ፍለጋ በሚያደርጉበትም ወቅት በርካታ ወንዶችን ከቤታቸው እንደወሰዱና አንዳንዶቹንም በቤተሰባቸው ፊት ገድለዋቸዋል ብሏል።
ከመግደል በተጨማሪ ድብደባዎች፣ መደፈርና የአማራን ብሔር የሚያንቋሽሹ ስድብ ይሳደቡ ነበር ተጠቅሷል።
የዐይን እማኞች ለኮሚሽኑ እንደተናገሩት የተገደሉት ግለሰቦች ሰላማዊ አርሶ አደሮችና የቀን ሠራተኞች መሆናቸውን ነው። ኮሚሽኑ ከጥቃቱ የተረፉ ግለሰቦችንና ቤተሰብ ያጡ የከተማዋ ነዋሪዎችን ማናገሩን አመላክቷል።
ከጥቃቱ የተረፉ ሰዎች በየመንገዱ አስከሬኖች ተረፍርፈው እንደተመለከቱና በርካቶቹንም በጅምላ ቀብረናቸዋል ብለዋል። በርካቶቹም በአራት ቤተ ክርስቲያኖች ቢቀበሩም አስከሬናቸው በጅብ የተበሉ እንዳሉ የዐይን እማኞች የተናገሩ ሲሆን አስከሬኖችንም ይዘው እንዳይሄዱም የትግራይ ኃይሎች ከልክለውናል ብለዋል።
የዐይን እማኞች በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ተገድለዋል ያሉ ሲሆን ኮሚሽኑ በበኩሉ የሟቾችን ትክክለኛ ቁጥር ለማወቅ ምርመራ ሊደረግ ይገባል ብሏል። በተጨማሪም የትግራይ ኃይሎች መጠነ ሰፊ ዝርፊያና ቁሶችን ማውደማቸው ተጠቅሷል።
በጭና ከተማም በተመሳሳይ መልኩ ወንዶችን ከሴትና ከቤተሰብ በመለየት መግደላቸውንና አንዳንዶቹም በቤተሰባቸው ፊት ተገድለዋል ብለዋል ። አንድ የዓይን እማኝ አምስት ቄሶች መግደላቸውንና የጠቀሱ ሲሆን በርካታ ቁጥር ያላቸውም ሰዎች መገዳላቸውን ገልጸዋል።
በጭናም ድብደባዎች እንዲሁም የ11 ዓመት ህፃንን ጨምሮ ታዳጊዎችንና ሴቶችን ደፍረዋል በማለት ሪፖርቱ ይፋ ማድረጉን የዘገበው ቢቢሲ አማርኛ ዘግቧል።
ሪፖርቱ ከተለያዩ የኢትዮጵያ መንግሥት ባለሥልጣናት ተቃውሞና ትችት የቀረበበት ሲሆን የጠቅላይ ሚኒስትሩ የብሔራዊ ደኅንነት አማካሪ የሆኑት አምባሳደር ሬድዋን ሁሴን ቀድሞ የታሰበውን “ኢትዮጵያን የመወንጀል እና ዝቅ አድርጎ የማቅረብ” ፖለቲካዊ ውጤት ነው ሲሉ በትዊተር ገጻቸው ላይ ተቃውሟቸውን አሰምተዋል።
ሬድዋን ሪፖርቱን፣ “የተምታታና ተጨባጭነት የሌለው” ብለውታል።
የኤርትራ መንግስትና የህወሃት ሀይሎች በበኩላቸው በታጣቂዎቻቸው ተፈፅሟ ስለተባለው የጦር ወንጀል ግልፅ ምላሽ ከመስጠት ይልቅ ዝምታን መርጠዋል፡፡

