ለ90 ቀናት በሰይፉ ፋንታሁን የዩቲዩብ ቻናል ሲደረግ የቆየው የመጀመሪያው ዙር የቀጥታ ስርጭት ገቢ ማሰባሰቢያ ተጠናቀቀ፡፡ ቀጣይ ሃላፊነቱን ወስዶ ገቢውን የሚያሰባስበው አካል እየተጠበቀ እንደሆነም ተሰምቷል፡፡
በሰይፉ ፋንታሁ የዩቲዩብ ቻናል ሲደረግ የቆየው የቀጥታ ስርጭት ገቢ ማሰባሰቢ ፕሮግራም የመጀመሪያው ዙር ከ1 ቢሊየን ብር በላይ በማሰባሰብ ነው የተጠናቀቀው፡፡
መቄዶኒያ የአረጋዊያንና የአዕምሮ ህሙማን መርጃ ማዕከል እያስገነባ ላለው ዘመናዊ የመኖሪያና የሆስፒታል ህንጻ የፊኒሽንግ ስራውን ለማጠናቀቅ ያስፈልጋል የተባለውን 5 ቢሊየን ብር ለማሰባሰብ በሚል ሰይፉ ፋንታሁን ከየካቲት 1 ጀምሮ ላለፉት 3 ወራት በቀጥታ ስርጭት ሲያሰባስብ ቆይቷል፡፡
እስካሁን በቆየው የማሰባሰብ ዘመቻ የታሰበው እቅድ ተሳክቷል የተባለ ሲሆን፤በአይነትና በገንዘብ ከ1 ቢሊየን በላይ ብር ተሰብስቧል፡፡
የመጀመሪያው ዙር የቀጥታ ስርጭት የገቢ ማሰባሰቢያው ፕሮግራም ይህን በማሳካት ተጠናቋል፡፡
የገቢ ማሰባሰብ ፕቶግራሙ የተካሄደበት ሰይፉ ኦን ኢቢኤስ እና ሰይፉ ሾው የዩትዩብ ቻናል የተገኘውን ከ4 ሚሊየን በላይ የሚሆን የማስታወቂያ ገንዘብ ለመቄዶኒያ ገቢ ማድረግ እንደተቻለ ተነግሯል፡፡
የማዕከሉ መስራች የክብ ዶ/ር ቢኒያም በለጠ ላለፉት 3 ወራት በቀጥታ ስርጭቱ ለተሳተፉት በሙሉ ምስጋና አቀርቦ፤ትልቁን ሃላፊነት በመውሰድ ሲያስተባብር የቆየውን ሰይፉ ፋንታሁንን በልዩነት አመስግኗል፡፡
ይህን መሠረት አድርጎም የምስጋና የምስክር ወረቀት እንዲሁም በማዕከሉ ተረጂዎች የተሰራ ጋቢ ለሰይፉ እና ለአርቲስት ይገረም ደጀኔ ተበርክቷል፡፡ በተጨማሪም ለሰይፉ ፋንታሁን በራሱ ምስል የተቀረጸ የቅርጽ ስጦታ ተበርክቶለታል፡፡ የዘመቻው ሁለተኛው ምዕራፍ በጥቂት ቀናት ውስጥ እንደሚጀመርም ይጠበቃል፡፡

