ከዚህ ቀደም ለሕጻናት ይሰጥ የነበሩትን ሶስት ጸረ ኤች አይ ቪ መድሃኒቶች ተጣምረው በአንድ እንክብል መልክ የያዘ pALD የተሰኘ መድሃኒት ለማስጀመር ዝግጅት ተጠናቋል።
ከዚህ ቀደም አዲሱን pALD የተሰኘ የህጻናት ጸረ-ኤች.አይ.ቪ መድሃኒቶችን ወደ ሃገር ውስጥ ማስገባት መቻሉን ያስታወሱት በጤና ሚኒስቴር የኤች.አይ.ቪ ኤድስ መከላከል እና መቆጣጠር መሪ ስራ አስፈጻሚ አቶ ፍቃዱ ያደታ አሁን ላይ በጤና ተቋማት መድሃኒቱን በአጭር ግዜ ዉስጥ ለማስጀመር አስፈላጊዉ ዝግጅት መጠናቀቁን ገልጸዋል።
አቶ ፍቃዱ አክለውም pALD የተሰኘው የፀረ ኤች አይ.ቪ መድሃኒት ከዚህ ቀደም ለሕጻናት ይሰጥ የነበሩትን ሶስት ጸረ ኤች አይ ቪ መድሃኒቶች ተጣምረው በአንድ እንክብል መልክ የያዘ እና በቀን አንድ ጊዜ ብቻ የሚወሰድ እንዲሁም ህጻናት ከመድሃኒት ጋር ያላቸውን ቁርኝት ታሳቢ በማድረግ የተመረተ መሆኑን ጠቁመው መድሃኒቱ በደም ውስጥ የቫይረስ ልኬት ወደ ሚፈለገው መጠን ለማዉረድ ከፍተኛ አቅም እንደሚኖረውም ገልጸዋል።
ይህንን የፀረ-ኤች አይ.ቪ መድሃኒት በማስተዋወቅ በደማቸው ውስጥ የኤች.አይ.ቪ ለሚገኝ ህጻናት በአግባቡ ደርሶ በስፋት ጥቅም ላይ እንዲውል በጉዳዩ ላይ የሚሰሩ ሁሉ ሃላፊነታቸውን እንዲወጡ አቶ ፍቃዱ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።
(ጤና ሚኒስቴር)

