ጥር 14፣ 2018 ዓ.ም፤ 6ኛው የሕዝብ ተወካዮች ም/ቤት ዛሬ ባካሄደው 9ኛ መደበኛ ስብሰባው በኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ መንግስት እና በተለያዩ ሀገራት መካከል የተደረገውን ፍርደኞችን ማስተላለፍ እንዲሁም የወንጀል ጉዳይ የአሳልፎ መስጠት አዋጅ አጽድቋል፡፡
ፍርደኞችን ማስተላለፍ ስምምነቱ በኢትዮጵያ እና በሕዝባዊት ሪፐብሊክ ቻይና እንዲሁም በኢትዮጵያ እና በብራዚል ፌዴራላዊ ሪፐብሊክ መንግሥታት መካከል የተደረገ ነው፡፡
በወንጀል የሚፈለጉ ሰዎችን የአሳልፎ የመስጠት ስምምነቱ ደግሞ በኢትዮጵያ እና በደቡብ አፍሪካ ሪፐብሊክ መንግሥታት መካከል የተደረገ ነው፡፡
ረቂቅ አዋጆቹን አስመልክቶ በምክር ቤቱ የህግ እና ፍትሕ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ የተዘጋጀውን ሪፖርትና ውሳኔ ሀሳብ የቋሚ ኮሚቴው ሰብሳቢ የተከበሩ ወ/ሮ እጸገነት መንግስቱ አቅርበዋል፡፡
በተለያዩ ወንጀሎች ምክንያት ዜጎቻቸው ተፈርዶባቸው ፍርዳቸውን በሀገራቸው ጨርሰው እና ታርመው ወደ ማህበረሰባቸው እንዲቀላቀሉ በማድረግ የመታረም ሂደቱን ውጤታማነት የሚያግዝ አዋጅ እንደሆነ የተከበሩ ወ/ሮ እጸገነት ባቀረቡት የውሳኔ ሀሳብ ገልጸዋል፡፡
ስምምነቶቹ ፍርደኞቹ ከሚያውቁት ማህበረሰብ፣ ቋንቋ እና ባህል ጋር በቅርበት ፍርዱን እንዲፈጽሙ እና ፍርዳቸውን በሀገራቸው እንዲጨርሱ ለማድረግ የሚረዳ እንደሆነ የተከበሩ ወ/ሮ እጸገነት ባቀረቡት የውሳኔ ሀሳብ ገልጸዋል፡፡
በኢትዮጵያ እና በሀገራቱ መካከል የተደረጉት ስምምነቶች የወንጀል ሥነ-ስርዓት ሂደት ያገናዘቡ፤ ዓለም አቀፍ አሰራርን መሰረት ያደረጉ ውጤታማ የሆነ የወንጀል መከላከል ትብብር ማድረግ፣ የሕግ የበላይነትን ለማረጋገጥ እና የፍትህ ስርዓትን ለማስፈን ጠቀሜታቸው የጎላ እንደሚሆንም የኮሚቴው ሰብሳቢ ባቀረቡት የውሳኔ ሀሳብ ጠቁመዋል፡፡
በወንጀል ጉዳይ ግለሰቦችን አሳልፎ መስጠትን አስመልክቶ የተደረገው ስምምነት ወንጀልን የፈጸመ ግለሰብ ወይም ተጠርጣሪ ለፍትህ ለማቅረብና ወንጀልን ፈጽሞ ወደሌላ ሀገር በመሸሸጉ ከተጠያቂነት እንዳያመልጥ ለማድረግ የሚረዳ ስለሆነ አሳልፎ የመስጠት ረቂቅ አዋጁን ማፅደቅ አስፈላጊ እንደሆነም ተገልጿል፡፡
በተለይ ኢትዮጵያ እና ቻይና እንዲሁም ኢትዮጵያ እና ደቡብ አፍሪካ በንግድና ኢንቨስትመንት ዘርፍ ያላቸው ግንኙነት እየጨመረ በመሆኑ፤ ተጠርጣሪዎችና ወንጀለኞች ይህንን ሁኔታ በመጠቀም ከህግ ለማምለጥ ወደ ሁለቱም ሀገራት ለመሄድ የሚችሉበትን አጋጣሚ ሰፊ እንደሚያደርገው በቀረበው የውሳኔ ሀሳብ ተገልጿል፡፡
በረቂቅ አዋጆቹ አስፈላጊነትና ተግባራዊነት ላይ የምክር ቤቱ አባላት ላቀረቡት ጥያቄና አስተያየት የተከበሩ ወ/ሮ እጸገነት መንግስቱ ተጨማሪ ማብራሪያ ካቀረቡ በኋላ ምክር ቤቱ በአብላጫ ድምጽ አጽድቋቸዋል፡፡

