በኢትዮጵያ ከ4.3 ሚሊየን በላይ የሚሆነው አርሷደር በድንች ምርት ዋጋ ላይ የመወሰን እድል እንደሌለው ተገለጸ

አርሷ አደሩ ከፍተኛ ወጪ እያወጣ ከሚያመርተው ምርት ውስጥ ተጠቃሚ መሆን የቻለው አስር በመቶ ብቻ መሆኑ ተገለጸ፡፡

በኢትዮጽያ አርሷደሩ ከፍተኛ ወጪ በማውጣት ከሚያመርተው ምርት ተጠቃሚ እንዳልሆነ በጥናት መረጋገጡ ተነግሯል፡፡

በሀገሪቱ ከ4.3 ሚሊየን በላይ የሚሆነው አርሷደር ድንችን በማምረት ለገበያ የሚያቀርብ ነው ሲባል ከምርቱ ላይ የሚያገኙት ጥቅም ግን አስር በመቶ ብቻ እንደሆነ ተሰምቷል፡፡

በአንጻሩ ግን ነጋዴውና ደላላው ገበያውን በስፋት ተቆጣጥረው እንዳሻቸው እያደረጉት እንደሆነና የተጋነነ ጥቅም እያገኙበት መሆኑ ተመላክቷል፡፡ የኢትዮጽያ ግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት ከሌሎች አጋር አካላት ጋር በመሆን ባደረገው ጥናት ነው ይህ የታወቀው፡፡

ኢትዮጽያ ድንች በማምረት ከግብጽና ከደቡብ አፍሪካ ቀጥላ በሦስተኛ ደረጃ ላይ ትገኛለች የተባለ ሲሆን በመስኖ የሚያመርቱትን ሳይጨምር በበልግና በመአር ብቻ ከ4.3 ሚሊየን በላይ አርሷደሮች ድንች ያመርታሉ፡፡

የድንች ምርት ባለፉት ሦስት ዓመታት ከነበረው ጠቅላላ ምርት አስር በመቶ መቀነሱም ተገልጻል፡፡

ኢትዮጽያ ለድንች ምርት ተስማሚ ብትሆንም በተለያዩ ምክንያቶች ከሌሎች ሀገራት ጋር ሲነጻጸር ዝቅተኛ እንደሆነ በጥናት መረጋገጡ ተሰምቷል፡፡ ለዚህ ደግሞ የተለያዩ ምክንያቶች ቢኖሩም በቴክኖሎጂ ታግዞ አለመስራት እና በማከማቻ ወቅት በሚያጋጥም የምርት ብክነት እንደሆነ በጥናት ተለይቷል፡፡

የኢትዮጽያ 95 በመቶ የሚሆነው ድንች የሚመረተው በአማራ ክልል፡በኦሮሚያና በደቡብ ኢትዮጽያ አካባቢዎች ነው፡፡

የድንች ገበያ በደላሎችና በጥቂት ግለሰቦች እጅ እንደወደቀ በጥናቱ የተለየ ሲሆን ይህም በምርቱ ላይ የዋጋ ጭማሬ እንዲኖርና አርሷደሩም ተገቢውን ጥቅም እንዳያገኝ አድርጓል፡፡

የግብይት ስርዓቱ በህግ አለመመራትና በጥቂት ግለሰቦች ቁጥጥር ስር መውደቁ አርሷደሮችን ከአምራችነት ሊያስወጣ እንደሚችልም ተመላክቷል፡፡

ገበሬው በምርቱ ላይ ዋጋ የመወሰን እድል እንደሌለው የተገለጸ ሲሆን ነጋዴው በሚያቀርበው ዋጋ ለመሸጥ እንደሚገደድ ተገልጻል፡፡

በመሆኑም አርሷደሮች ከሚያመርቱት ምርት አስር በመቶውን ብቻ ሲጠቀሙ፡ደላሎች 18 በመቶውን እንዲሁም ነጋዴዎች 60 በመቶ የሚሆነውን እንደሚጠቀሙ በጥናቱ ተጠቁሟል፡፡

አርሷ አደሩ 60 በመቶ የሚሆነውን ወጪ የሚሸከም ሲሆን ከጥቅሙ ግን ድርሻው አስር በመቶ ብቻ እንደሆነ ተነግሯል፡፡

በአንጻሩ ነጋዴው የሚያወጣው ወጪ ዝቅተኛ ሆኖ ሳለ ትርፉ ግን 60 በመቶ እንደሆነ ነው በጥናቱ የተመላከተው፡፡/

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

ትስስር ይፍጠሩ

325,851FansLike
49,039FollowersFollow
13,194SubscribersSubscribe