በኢትዮጵያ የጫት ተጠቃሚነት በከፍተኛ ሁኔታ መጨመሩ አሳሳቢ መሆኑን የኢትዮጵያ የህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት መረጃዎችን ጠቅሰው የኤካ ኮተቤ ሆስፒታል የአዕምሮ ህክምና ክፍል ኃላፊ ዶ/ር እስጢፋኖስ እንዳላማዉ ገልፀዋል።
የሱስ ችግር ከአንጎል ባዮሎጂ ጋር በቀጥታ የተያያዘ በመሆኑ ህብረተሰቡ ጥንቃቄ እንዲያደርግና የሚመለከታቸው አካላት በጫት ቁጥጥር ላይ ትኩረት እንዲሰጡም አሳስበዋል።
ኤካ ኮተቤ ሆስፒታል የአዕምሮ ህክምናን ከሌሎች ህክምናዎች ጋር አቀናጅቶ እየሰጠ መሆኑን የጠቀሱት ኃላፊው፤ ተቋሙ ከአማኑኤል ሆስፒታል ቀጥሎ ከፍተኛ ቁጥር ያለው 145 የመኝታ አልጋዎችን በማዘጋጀት ለህጻናት፣ ለአዋቂዎች፣ ለአረጋውያን እና ከሱስ ጋር የተያያዙ ችግሮች ላለባቸው ወገኖች በየክፍሉ አገልግሎት እየሰጠ እንደሚገኝ አስታውቀዋል።

