ያለፈው 2025 ዓ.ም ከሩዋንዳው የዘር ጭፍጨፋ በኋላ ከፍተኛ የንጹሃን እልቂት የተፈጸመበት እንደነበር ጥናት አመላከተ፡፡
በዚሁ ዓመት ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት ወዲህ በዓለም ላይ ጦርነትና ግጭት እየተባባሰ የመጣበት እንደሆነም ተነግሯል፡፡
በአንድ የስዊድን ዩኒቨርሲቲ ተመራማሪዎች የተካሄደ አዲስ ጥናት በ2025 በሀገራት መካከል የተመዘገበው የግጭት ብዛት ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት ወዲህ ከፍተኛው መሆኑን ጠቁሟል፡፡
የሟቾች ቁጥርም ከሩዋንዳ የዘር ማጥፋት እልቂት ወዲህ ታይቶ የማይታወቅ ደረጃ ላይ ደርሷል ተብሏል፡፡ የሩዋንዳው የዘር ፍጅት በዘመናዊ የሰው ልጆች ታሪክ ውስጥ እጅግ መራር የተባለውና 1 ሚሊዮን የሚደርሱ ሰዎች ያለቁበት ክፉ ክስተት ነው፡፡
ሪፖርቱ ባለፈው የ2025 ዓመት 65 ጦርነቶች በመላው ዓለም ነበሩ ብሏል፡፡
የሩሲያው እና የዩክሬኑ ጦርነት፡የእስራኤል፡አሜሪካ እና ኢራን ጦርነት፡ያለፈው ዓመት የህንድና የፓኪስታኑ ጦርነት፡የታይላንድና ካምቦዲያው ጦርነት፡የእስራኤል፡የመን እና ሶሪያው ጦርነት፡የአፍጋኒስታን እና ፓኪስታኑን ጦርነት፡ የጋዘው ጦርነት፡የሱዳኑን የእርስ በርስ ጦርነትን ጨምሮ ባለፈው ዓመት 65 ጦርነቶች መደረጋቸውን ሪፖርቱ ጠቁሟል፡፡
በሀገራት ውስጥ በመንግስትና በአማጺ ሃይሎች መካከል የሚደረጉ ግጭቶችም መጨመራቸው ተነግሯል፡፡ በ2025 በግጭቶች ምክንያት 244ሺ 600 ሰዎች ተገድለዋል፡፡ ያለፈው ዓመት በንጹሃን ላይ የተመዘገበው ሞት እጅግ ከፍተኛ ነው የተባለ ሲሆን በተለይም በሱዳን ቁጥሩ አስደንጋጭ ነበር ተብሏል፡፡
የሩሲያ እና ዩክሬን ጦርነት ባለፈው ዓመት ከሞቱ ሰዎች ውስጥ 62 በመቶ የሚሆነውን እንደሚሸፍን ሪፖርቱ አመልክቷል፡፡ በሁለተኛነት ደረጃ የተቀመጠው ደግሞ የእስራልና ሐማስ ጦርነት ሲሆን ሦስተኛው የሱዳኑ የእርስ በርስ ጦርነት ነው፡፡//

