ቱርክ በተኩስ አቁሙ ስምምነት አቅጣጫ ዙሪያ ነው የሃማስን ሰዎች ወደ ኢስታንቡል በመጥራት ያነጋገረችው፡፡
ሁለቱም ወገኖች የተደረሰው የተኩስ አቁም ስምምነት ተጠናክሮ እንዲዘልቅ፡እያጋጠሙ ያሉ ችግሮችን ለመቅረፍ እና የሰብዓዊ ድጋፍ ወደ ጋዛ በበቂ ሁኔታ ሊገባ በሚችልበት ዙሪያ ነው የመከሩት ተብሏል፡፡
የሃማስን ሉዑክ እየመሩ ወደ ኢስታንቡል ያመሩት የቡድኑ የፖለቲካል ቢሮ መሪ የሆኑት እና ከዚህ ቀደም በኳታር ከእስራኤል የግድያ ሙከራ የተረፉት ካህሊል አልሃያ ናቸው፡፡
በኢስታንቡልም የቱርክ የኢንተለጀንስ ተቋም ዳይሬክተር ከሆኑት ኢብራሂም ካሊን ጋር ነው የተገናኙት፡፡ በንግግራቸውም ስለ ቀጣዩ ዙር የሰላም ስምምነቱ ተነጋግረዋል ተብሏል፡፡
በንግግራቸው ወቅትም የሃማስ ሉዑካን ቡድኖች ቱርክ የአሸማጋይነት ሚናዋን እየተወጣች ስለሆነ እናመሰግናለን ብለዋል፡፡ በተለይም ለፕሬዝዳንቱ ረሲፕ ጣይብ ኤርዶሃን ልዩ ምስጋና ማቅረባቸው ተነግሯል፡፡
በተጨማሪም ሃማስ ስምምነቱን ለማክበር ቁርጠኛ ቢሆንም፤እስራኤል ግን ስምምነቱን በመጣስ ጥቃት እያደረሰች ነው የሚል ክስ አቅርበዋል፡፡
እስራኤል ሃማስ ቢጫ መስመር ተብሎ የተሰመረውን አካባቢ ለማለፍ ሲሞክር እንዲሁም ወታደሮቿም በቡድኑ ሲገደሉ ጥቃት በቡድኑ ላይ ማድረሷን ከዚህ ቀደም ገልጻለች፡፡
በሌላ በኩል ሃማስ ትላንት ቀሪ የእስራኤል ታጋች አስክሬኖችን ማስረከቡ ተሰምቷል፡፡ እስካሁን ቡድኑ ከ28 የሟች አስክሬን ውስጥ 22 የሚሆኑትን ለእስራኤል ያስረከበ ሲሆን ቀሪ 6 አስክሬንም ማስረከብ ይኖርበታል፡፡
ሁለተኛው እና ዋናው የሰላም ድርድሩ እንዳይጀመር ምክንያት የሆነውም ሃማስ የሁሉንም ታጋች አስክሬን ማስረከብ ባለመቻሉ ነው፡፡ ቡድኑ መዘግየቱ የገጠመው ከአቅም በላይ ስለሆነበት እንደሆነ ይገልጻል፡፡ እስራኤል ግን ሃማስ የሁሉንም አስክሬን ያለበትን ስፍራ ያውቃል በሚል ውድቅ ታደርገዋለች፡፡
ሃማስ ትጥቁን እንዲፈታ ከእስራኤል፡ከዩናይትስ ስቴትስ እና ከግብጽ ተደጋጋሚ ሙከራዎች ሲደረጉ መቆየታቸው ይታወሳል፡፡ ነገር ግን ቡድኑ እስራኤል የፍልስጤማዊያንን ግዛት ለቃ እስካልወጣች ድረስ ትጥቁን እንደማይፈታ መግለጹም አይዘነጋም፡፡
በኦክቶበር 10 የተፈረውም የፕሬዝዳንት ትራምፕ የሰላም እቅድም ቡድኑ ትጥቁን እንዲፈታና የጋዛው ሚናም እንዲያከትም የሚያደርገው ነው፡፡//

