ትራምፕ ኢራን ከኢዝላማባዱ ያልተሳካው ንግግር በኋላ ዳግም ወደ ድርድር መመለስ እፈልጋለሁ አለች አሉ

ኢራን ከኢስላማባዱ ያልተሳካው ንግግር በኋላ ዳግም ወደ ድርድር መመለስ እንደምትፈልግ ትራምፕ ተናገሩ፡፡

በአሜሪካ እና በኢራን መካከል ባለፈው ቅዳሜ ለ21 ስዓታት ያህል የተደረገው ንግግር ያለ ተጨባጭ ውጤት መጠናቀቁ ይታወሳል፡፡ ነገር ግን አሁንም ዲፕሎማሲያዊ ጥረቶች ቀጥለዋል ነው የተባለው፡፡

ፕሬዝዳንት ትራምፕ ኢራን በምንም መልኩ የኒውክሌር መሳሪያ ባለቤት እንድትሆን ዋሽንግተን እንደማትፈቅድ በድጋሚ ገልጸዋል፡፡

በብዙ ነገሮች ከኢራን ሰዎች ጋር ተስማምተናል በኒውክሌር ጉዳይ ግን እስካሁን ልንስማማ አልቻልንም በማለትም ገልጸው፤በዚህ ላይ ከመግባባት ሳይደረስ ግን ምንም አይነት ስምምነት ሊኖር አይችልም ብለዋል፡፡

በዚህ ስዓት በዋሽንግተን እና በቴህራን መካከል ትልቁ የልዩነት ነጥብ ሆኖ የዘለቀው ይሄው ዩራኒየም የማበልጸጉ ጉዳይ ስለመሆኑ በስፋት ይነገራል፡፡ አሜሪካ በዚህ ወቅት ኢራን ለመጪዎቹ 20 ዓመታት ድረስ ዩራኒየም ማበልጸጓን ሙሉ በሙሉ እንድትተወው እና የተከማቸውን ዩራኒየምም እንድታስወግደው ፍላጎት እንዳላት ሪፖርቶች ጠቁመዋል፡፡

በአንጻሩ ኢራን ለአጭር ጊዜ ዩራኒየም ማበልጸግ እንደምታቆም በመግለጽ ከዋሽንግተን ጋር ወደ ስምምነት እንዲመጣ ቅድመ ሁኔታዋን አስቀምጣለች ተብሏል፡፡

የአሜሪካው ምክትል ፕሬዝዳንት እና ዋነኛ ተደራዳሪ ጄዲ ቫንስ ዋሽንግተን ከቴህራን ጋር በከፍተኛ ባለስልጣናት ደረጃ እንዲህ አይነቱን ንግግር ስታደርግ የመጀመሪያዋ ነው ይህም መልካም አጋጣሚ ነው ብለዋል፡፡ ነገር ግን ወደ ስምምነቱ ስንመጣ አሁንም ቢሆን ኢራን ከያዘችው ግትር አቋም መለሳለስ ይኖርባታል ብለዋል፡፡

በእኛ በኩል ሁሉንም ምርጫዎች በጠረጼዛው ላይ አስቀምጠናል መምረጥ የእነርሱ ፋንታ ይሆናል በማለትም አክለዋል፡፡ ዋሽንግተን እና ቴህራን ለሁለት ሳምንት የሚቆም የተኩስ ማቆም ስምምነት ላይ ቢሆኑም ነገር ግን ስምምነቱ ስጋት ተጋርጦበት ቀጥሏል፡፡ አሁንም ቢሆን ግን ዲፕሎማሲያዊ መፍትሔዎች ሙሉ በሙሉ ከምርጫ ውጭ ናቸው ለማለት በሚቻልበት ሁኔታ ላይ እንዳልሆነ ይታመናል፡፡

ይህ በእንዲህ እንዳለ በሆርሙዝ ወሽመጥ በኩል ያለው ቀውስ አሁን ወደ አደገኛ ምዕራፍ ተሸጋግሯል ተብሏል፡፡ በአሜሪካም ሆነ በኢራን በኩል ባለው ወታደራዊ ውጥረት ነገሮች ተባብሰው እንዲቀጥሉ ምክንያት ሆነዋል ነው የተባለው፡፡

የሆርሙዝ ወሽመጥ ቀውስ ውስጥ እንዳለ በሚታመንበት በዚህ ስዓት ፕሬዝዳንት ትራምፕ በትላንትናው እለት 34 መከርከቦች በሰርጡ በኩል ማለፋቸውን ይፋ አድርገዋል፡፡ ይህም ኢራን ሰርጡን በጥብቅ መቆጣጠር ከጀመረችበት ጊዜ ወዲህ ከፍተኛው የትራፊክ እንቅስቃሴ ነው ተብሏል፡፡ ከጦርነቱ በፊት በሰርጡ በኩል በየቀኑ ከ100 በላይ መርከቦች ይተላለፉ የነበረ ሲሆን ፤ጦርነቱ ከተነሳ ከ6 ሳምንታት ወዲህ ግን በሰርጡ በኩል የተላለፉት መርከቦች ቁጥር ከ40 እንደማይበልጡ ነው የተነገረው፡፡

ምክትል ፕሬዝዳንት ጄዲ ቫንስ ጦርነቱን ለማስቆም ፍላጎት ስላለን የሁለት ሳምንት የተኩስ አቁም በእኛ በኩል አድርገናል በምላሹ ደግሞ ከኢራን የሆርሙዝን ሙሉ በሙሉ መከፈት እንፈልጋለን ብለዋል፡፡//

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

ትስስር ይፍጠሩ

325,851FansLike
49,039FollowersFollow
13,194SubscribersSubscribe