ኒያላ ኢንሹራንስ ለዳያስፖራው ከ10 ሺ እስከ 13 ሺ ዶላር የመድን ሽፋን እሰጣለሁ አለ

ኒያላ ኢንሹራንስ ለዳያስፖራው የሚሆን ልዩ የመድን ሽፋን እንደሚሰጥ አስታወቀ፤ ከ10ሽ እስከ 13 ሽ ዶላር የመድን ሽፋን እሰጣለሁ ብሏል

ኒያላ ኢንሹራንስ አ.ማ. የኢትዮጵያን ዳያስፖራ ማኅበረሰብ ፍላጎትና አቅም ግምት ውስጥ በማስገባት የዳያስፖራ ልዩ ኢንሹራንስ አገልግሎት ለገበያ ማቅረቡን አስታወቀ፡፡

ታኅሳስ 13 ቀን 2014 ዓ.ም. የኩባንያው የሥራ ኃላፊዎች በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ እንዳብራሩት፣ የዳያስፖራ ልዩ የኢንሹራንስ ሽፋን አገልግሎት ላይ የዋለው በዓለም አቀፍ ደረጃ ከታወቁ ከፍተኛ የጠለፋ ዋስትና ሰጪ ኩባንያዎች ጋር በመደራደርና ሽፋኑን በሚገባ ለመስጠት የሚያስችል መተማመኛ ከተገኘ በኋላ ነው፡፡

ሽፋኑን ለመስጠት እንዲቻልም የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ፈቃድ ከተሰጠው በኋላ የተተገበረ ስለመሆኑ ከተሰጠው ማብራሪያ ለመረዳት ተችሏል፡፡

በመድን ሽፋኑ ይዘት ላይ ማብራሪያ የሰጡት የኩባንያው የውል ክፍል ኃላፊ አቶ ዘውዱ በየነ፣ በዚህ መድን ሽፋን የኢትዮጵያውያን ዳያስፖራ አባላት ወደ ኢትዮጵያ መጥተው በሚቆዩበት ጊዜ የኮቪድ-19 ወረርሽኝን ጨምሮ በሕመምና በአደጋ ምክንያት ለሚወጡት የሆስፒታል፣ የቀዶ ሕክምና፣ የመድኃኒት፣ ለሕክምና ወጪዎች እስከ 90 ቀናት ድረስ የሚቆይ የመድን ዋስትና የሚሰጥበት መሆኑን ተናግረዋል፡፡

ከውጭ ወደ አገር ቤት ለሚደረግ የአስከሬን ሽንት ወጪ፣ እንዲሁም አስከሬን ይዞ ወደ አገር ቤት ለሚመጣ ዘመድ ወይም ጓደኛ የትራንስፖርት ወጪን የዳያስፖራ ልዩ ኢንሹራንስ ዋስትና ሽፋንንም አጠቃልሎ የያዘ ነው፡፡

እነዚህን የመድን ሽፋኖች ኩባንያው እስከ አሥር ሺሕ ዩሮ ወይም እስከ 13 ሺሕ ዶላር ወይም በብር ደግሞ ከ640 ሺሕ ብር በላይ ዋስትና እንደሚሸፍንም ገልጸዋል፡፡

ኢትዮጵያውያን በውጭ በሚኖሩበት ጊዜ የሞት አደጋ ሲያጋጥም አስከሬን ይዞ ወደ አገር ቤት ለመላክ ለትራንስፖርት የሚወጣው ወጪ ብዙውን ጊዜ በቅርብ ጓደኞቻቸውና ቤተሰቦቻቸው ነው የሚሸፈነው፡፡

የአስከሬን ሽንት ወጪን፣ ትራንስፖርትና ተያያዥ ወጪዎችን ለመሸፈን እንዲቻል ከውጭ ካሉ የጠለፋ ዋስትና ሰጪዎች ጋር ረዥም ጊዜ የቆየ ጥናትና ድርድር ከተደረገ በኋላ ይሁንታ በመገኘቱና በብሔራዊ ባንክም በመፈቀዱ አገልግሎቱ እንዲጀመር መደረጉን ገልጸዋል፡፡

ኒያላ ኢንሹራንስ ይፋ ያደረጋቸው አዳዲስ የመድን ሽፋን ዓይነቶችን ለመግዛት  አንድ ደንበኛ በዓመት ከ57 እስከ 74 ዶላር ብቻ በመክፈል የመድን ሽፋኑን ማግኘት ይችላል መባሉን የዘገበው ሪፖርተር ጋዜጣ ነው፡፡

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

ትስስር ይፍጠሩ

325,851FansLike
49,039FollowersFollow
13,194SubscribersSubscribe