አሜሪካ ከኢራን ጦር መሣሪያ ግዢ ጋር ግንኙነት አላቸው ያለቻቸው በርካታ ግለሰቦች፣ ድርጅቶች እና ሁለት የሩሲያ ኩባንያዎች ላይ ማዕቀብ ጣለች።
የአሜሪካ ግምጃ ቤት በትናንትናው ዕለት የጣለው አዲስ ማዕቀብ የሩሲያ ኩባንያዎችን ጨምሮ በሆንግ ኮንግ፣ ቻይና እና ፓኪስታን የሚገኙ 13 ግለሰቦችን ዒላማ ያደረገ ነው።
አሜሪካ በቴህራን ላይ የምጣኔ ሃብት ጫና ለመፍጠር በማሰብ የምታካሄደውን ዘመቻ መቀጠሏን ተናግራለች።
ማዕቀቡ ከተጣለባቸው የሩሲያ ኩባንያዎች መካከል ለአገሪቱ መከላከያ ሚኒስቴር የጦር መሣሪያዎችን የሚያጓጉዘው እና የሩሲያ አውሮፕላን አምራች ኩባንያዎች እንደሚገኙበት ሮይተርስ ዘግቧል።
ከዚህ ቀደም ሩሲያ ለቴህራን የድሮን መለዋወጫዎችን እና የጦር መሣሪያዎችን መስጠቷን የሚያሳዩ ሪፖርቶች ወጥተዋል።
ከዚህ በተጨማሪም ሞስኮ፣ ቴህራን በባሕረ ሰላጤው የሚገኙ የአሜሪካ ጦር ሠፈሮችን ማጥቃት እንድትችል ድጋፍ ማድረጓ ተገልጿል።
ሩሲያ በዩክሬን ላይ ሙሉ ወታደራዊ ጥቃት መክፈቷን ተከትሎ የቴህራን እና የሞስኮ ግንኙነት በከፍተኛ ሁኔታ እየተጠናከረ መጥቷል።
በጦርነቱ የመጀመሪያ ዓመት ኢራን በወታደራዊ እና በሲቪል ዒላማዎች ላይ በስፋት ጥቅም ላይ የሚውሉትን ‘ሻሄድ’ ድሮኖች ለሩሲያ አቅርባ ነበር።
በምላሹም የሩሲያው ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን፤ ኢራን በሆርሙዝ ባሕረ ሰላጤ አካባቢ ከአሜሪካ ጋር በምታደርገው ግጭት ድጋፋቸውን እንደሚቀጥሉ እና “አስፈላጊ ቁሳቁሶችን” እንደሚያቀርቡላት ተናግረዋል።
አሜሪካ ከቴህራን የጦር መሣሪያ ግዢ ጋር ንክኪ አላቸው ያለቻቸው የሩሲያ ኩባንያዎች ላይ ማዕቀብ ጣለች

