ከ1970ዎቹ ጀምሮ እስከ 1980ዎቹ አጋማሽ ድረስ ይታተሙ ከነበሩ ካሴቶች ጀርባ ጣዕም ያላቸውም ሙዚቃዎች ይጫወት የነበረው ሮሃ ባንድ ከጥላሁን ገሠሠ እስከ ማህሙድ አህመድ፤ ከኤፍሬም ታምሩ እስከ ነዋይ ደበበ፤ ከሐመልማል አባተ እስከ ኩኩ ሰብስቤ፤ ከአረጋኽኝ ወራሽ እስከ ኬኔዲ መንገሻ፤ ከዳዊት መለሰ እስከ ፀሀዬ ዮሐንስ ከ ቴዎድሮስ ታደሰ እስከ …/ዝርዝሩ ብዙ ነው/ ድረስ ሙዚቃዎቻን በማጀብ በሀገርና በውጪ ሀገር ልዩ ታሪክ ያለው ባንድ ነበር፡፡ በዚህ ባንድ ውስጥ ከነበሩት አንጋፋ ሙዚቀኞች መሀከል አንዱ የነበረው የሳክስፎን ተጫዋቹ አርቲስት ስምኦን ሊባኖስ //ዮናስ/ ከ25 ዓመታት በላይ ከኖረበት ከኪቤአድ መኖሪያ ቤቱ እንዲወጣ ተደርጓል፡፡ ቦሌ መንገድ ከሸዋ ሱፐር ማርኬት ፊት ለፊት ባለው የኪቤአድ ህንፃ ላይ ባለ ባለ ሁለት መኝታ ቤት ቤቱ ጥር 23 ቀን 2009 ዓ.ም የታሸገበት አርቲስት ስምኦን መላጨት የጀመረው ፂሙን ሳይጨርስ ከነአረፋው ከቤቱ ወጥቶ እንደታሸገና በማግስቱ ዕቃውን ጭኖ እንዲሄድ መደረጉን ይናገራል፤ያለፈ የሙዚቃ ህይወቱንና አሁን ያለበትን ሁኔታ በተመለከተ ቃለ ምልልስ ያደረገልት የቁም ነገር መፅሔት አዘጋጅ ሻንጣውን ይዞ ከሚውልበት ካፌ ተገኝቶ አነጋግሮታል፡፡
ቁም ነገር፡- ወደ ሙዚቃ እንዴት እንደገባህ እስኪ አጫውተን?
አርቲስት ስምኦን፡- እንግዲህ ሙዚቃን የጀመርኩት ከአርቲስት ዳዊት ይፍሩ ጋር ነው፤ ግርማ በየነ ጋር ራስ ሆቴል ነው የጀመርኩት፡፡ የአለማየሁ እሸቴ ሙዚቃ ቀረፃ ለማድረግ ይፈልግ ስለነበር ስድስት ሆነን እሱ ጋር የትንፋሽ መሳሪያ ሳክስፎን በመጫወት ጀመርኩ፡፡
ቁም ነገር፡- የአለማየሁ እሸቴ የቱ አልበም?
አርቲስት ስምኦን፡- ‹እሷስ እንኮይ ናት የአባይ ዳር› የሚለው ዘፈን ያለበት ነው፡፡ ያቀናበረው ግርማ በየነ ነው፡፡ ግርማ በየነ ጠማማ ፎቅ አካባቢ ቤት ተከተራይቶ ነበር የሚኖረው ፤ ጥሩ ስቱዲዮ ነበረው፡፡
ቁም ነገር፡- የሙዚቃ ትምህርትስ?
አርቲስት ስምኦን፡-ተምሬ ነው የጀመርኩት፡፡እነ ሙሴ ነርሲስ ናልቫልዲያና ፤ ጌታቸው ደባልቄ ያስተምሩን ነበር፡፡ፕሮፌሰር አሸናፊ ከበደም ይመጡ ነበር፡፡መዝሙርም እንዘምር ነበር፡፡ዳዊት ይፍሩ፤ ወንድሙ ቶላ፤ ጥላዬ ገብሬ ሁሉ ነበሩ ስልጠናው ላይ፡፡ ከስልጠናው በኋላ ከውጪ ሀገር ሳይቀር ከኢንዶኔዢያ ጭምር እየመጡ ሙዚቃ ስናቀርብ ያዩን ነበር፡፡
ቁም ነገር፡- በክለብ ደረጃ የት የት ሰርተሃል?
አርቲስት ስምኦን፡- ግዮን ሆቴል፤አውራሪስ ሆቴል የሚባል ነበር፤ እየተቋቀዋሙ የፈረሱ ባንዶች ነበሩ ልዩ ልዩ ሙዚቃዎችን እንጫውት ነበር፡፡ሠርግና ሌላም ሙዚቃ እንጫወት ነበር፡፡ ከዛ አንድ ባንድ ሲቋቋም ጓደኞቼ ጠሩኝና ቬነስ ክለብ አምባሳደር ቴአትር ምድር ቤት ያለ ክለብ ውስጥ መስራት ጀመርን፡፡ባለቤቱ አቶ አቡበክር አሸጌ ይባል ነበር፡፡ ባለቤቱ የውጭ ሀገር ዜጋ አሜሪካዊት ናት፤ እዛ ባንድ ውስጥ ስራ ከጀመርኩ በኋላ የባንዱ መሪ አደረገኝ አያያዜን አይቶ መሰለኝ፡፡ የተወሰነ ጊዜ ከሰራሁ በኋላ ወደ አስመራ ሄጄም ሰርቻለሁ፡፡

ቁም ነገር፡- ሮሃ ባንድ ውስጥ ነው ለረዥም ጊዜ የሰራኸው፤ እንዴት ገባህ?
አርቲስት ስምኦን፡- ለተወሰነ ጊዜ ካርቱም ውስጥ ከምንሊክ ወስናቸው ጋር ነበር የምሰራው፡ ፤የሱዳኖች የሀበሻ ሙዚቃ በጣም ነበር የሚወዱት፡ ፡ እዛ ሆኜ ወደ አሜሪካ ለመሄድ ነበር ሀሳቤ፡ ፡ ግን ልተቻለም፤ ባለቤቴም ልጆቼም እዚህ ስላሉ በየጊዜው ገንዘብ ብቻ እየላኩ መቆየቱ አስቸጋሪ ሲሆን አዲስ ባንድ ሮሃ ሊቋቋም እንደሆነ ባለቤቴ ሰምታ ነግራኝ ስለነበር ተመለስኩ፡፡ የሚገርምህ ከሰባት ወራት በኋላ ስመጣ በማግስቱ ነው ሮሃ ባንዶች ሂልተን ድረስ እንድመጣ የጠየቁኝ፡፡ ነፍሱን ይማረውና ተክሌ ተስፋእዝጊ ይመስለኛል የጠራኝ፡ ፡ ባለቤቴን ይዤ ሙዚቃቸውን ለመመልከት ነበር የሄድኩ፡፡ የእንግዶች ወንበር ላይ ሐረር ግሪል ከባለቤቴ ጋር ስቀመጥ ና ብለው አአስተናጋጁን ላኩብኝ፤ ምንድነው ? ስል ስቴጅ ላይ ካልወጣህ አሉኝ፡፡ መሳሪያ እኮ አልያዝኩም ስል ግድ የለም እኛ ጋር አለ አሉኝ፤የተለያዩ መሳሪያዎች በመጫወት እንደዛ እንደዛ እያልኩ ስራ ጀመርኩ ከእነርሱ ጋር ማለት ነው፡፡
ቁም ነገር፡- ሮሃ ባንድ እንግዲህ በብዛት የሚታወቀው የታወቂ ድምፃውያንን ካሴት በየወሩ ማውጣት መቻላችሁ ነው፤ እንዴት ነበር የምትሰሩት?
አርቲስት ስምኦን፡- ያው ሁሉም ከፍተኛ የሙዚቃ ችሎታ ያላቸው ሙዚቀኞች ነበርን የነበርነው፡፡ የባንዳችን አቀናባሪና መሪ ደግሞ ዳዊት ይፍሩ ነበር፡፡ ዳዊት እንደሚታወቀው በሙዚቃ ጉዳይ ላይ ቀልድ አያውቅም፤ በፕሮግራም ነበር የምንሰራው፡፡ እረፍት እንኳ በማጣት እያደርን ሁሉ ነበር የምንሰራው፡፡ ምክንያቱም የካሴት አሳታሚዎች በወረፋ ነበር የሚጠብቁን፡፡ አለመስማማት ሁሉ እየተፈጠረ ዳዊት ነበር ወረፋ የሚያወጣላቸው፤እኛ ደግሞ ለአንድ ድምፃዊ ከተያዘለት ጊዜ በላይ ስቱዲዮ ላለመቆጠየት በጥንቃቄ በፕሮግራም ነበር የምንሰራው፡፡የሙዚቃ መሳሪያው ራሱ እንዳሁኑ ዲጂታል አልነበረም፡ ፡ ተጠባብቀን ነበር የምሰንሰራው፡ ፡ ምክንያቱም ቀረፃ እየተናወነ አንዳችን ብንሳሳት እንደ አዲስ ነበር ሙዚቃውን የምንሰራው፡ ፡ እንደዛም ሆኖ ግን የብዙዎቹን ድምፃውያን ስራዎች ሰርተናል፡፤
ቁም ነገር፡- የእነማን የእነማንን ካሴቶች ሰርታችኋል?
አርቲስት ስምኦን፡ -የነማንን ልበልህ? የብዙዎቹ ካሴት የሚሰራው እኛ ጋር ነበር፡፡ ማህሙድ አህመድ ያው የባንዳችን አባል ነበር፡፡ ማህሙድ አንድ ጊዜ መድረክ ላይ ከወጣ እስከ አንድ ሰዓት ድረስ ሊዘፍን የሚችል ልዩ አርቲስት ነው፡፡ ኤፍሬም ታምሩ፤ነዋይ ደበበ፤አረጋኸኝ ወራሽ፤ ኩኩ፤ ኬኔዲ፤ ሐመልማል ማንን ጠርቼ ማንን ልተው?
ቁም ነገር፡- ጥላሁን ገሠሠስ?
አርቲስት ስምኦን፡-የጥላሁን ገሠሠን አንድ ካሴት ብቻ ነው የሰራንልት፡፡ ብዙዎቹን ክቡር ዘበኛ ሆኖ ነበር የተጫወተው፡፡
ቁም ነገር፡- ሮሃ ባንዶች ወደ መድረክ ላይ ስጥትወጡ ከአለባበሳችሁ ጀምሮ በከፍተኛ ዲስፕሊን ነበር የሙዚቃ ስራዎቻችሁን የምታቀርቡት፤ ግን ብዙዎቻችሁ ሙዚቃ የምትጫወቱ አይመስልም፤ ቆማችሁ ነበር ሙዚቃውን የምትጫወቱት ይህ ለምድነው የሆነው?
አርቲስት ስምኦን፡-እንግዲህ የሌሎቹን አላውቅም፤ እኔን በተመለከተ ግን ሳክስፎን ስጫወት የከንፈር ፓዚሽን የሚባል ነበር አለ፡፡ ስትንቀሳቀስ ከቅኝት ልትወጣ ትችላለህ፤ እርግጥ ነው አንዳንድ ሰዎች ለምድነው የማትጨፍሩት ይላሉ፡፡ ነፍሱን ይማረውና ታዋቂው የሳክስፎን ተጫዋች ጌታቸው መኩሪያም እንደዛ እያለ ይወቅሰን ነበር፡፡ በተለይ ቀረፃ ላይ በጥንቃቄ መሰራት አለበት፤ ቅኝት ከፈረሰ ሙዚቃው ይበላሻል፡፡
ቁም ነገር፡-በኢትዮጵያ ቴሌቪዥን የተቀረፃሁት ዘፈኖች አሁንም ድረስ ይታያሉ፤ እንዴት ነበር በነፃ ነበር ወይስ በክፍያ ነበር የምትቀረፁት?
አርቲስት ስምኦን፡- በጣም አድካሚ ከሚባሉ ቀረፃዎች መሀከል አንዱ የቴሌቪዥን ቀረፃ ነበር፡፡ ከረቫት አድርገን፤ ያ ሁሉ ዋት መብራት እላያችን ላይ እየበራ ነበር የምንቀረፀው፡፡እነዛን ሁሉ ዛሬ ታሪክ ሆነው የሚታዩ ዘፈኖችን ከወር በላይ ፈጅቶብን ነበር የተቀረፅነው፡፡
ቁም ነገር፡- ክፍያውስ?
አርቲስት ስምኦን፡-ክፍያ በወቅቱ እንደውም አልነበረም፡፡ የኢትዮጵያ ቴሌቪዥንም አይከፍልም ነበር፡፡
ቁም ነገር፡-ለምን?
አርቲስት ስምኦን፡- ምክንያቱም በቴሌቪዥን መታየት ለእናንተ ፕሮሞሽን ነው ይባል ስለነበር በነፃ ነበር ሊቀርፁን የመጡት፡፡ ትዝ ይከኛ አቶ ታደሰ ተስፋዬ የሚባሉ የካሜራ ክፍል ሀላፊ ነበሩ፡፡ ሙሉ ቀንም ነበር፡፡እናንተን ልንቀርፃችሁ እንፈልጋለን ሲሉን እንመካከርብት ነበር ያልናቸው፡፡ ምክንያም በኮንትራት ስራ የተጠመድን ሰዎች ስለሆንን ሌላ ገቢ የለንም ፡፡ እኛ መታወቅ ችግር የለብንም፡፡ ምክንያቱም ያ ሁሉ ታዋቂ ዘፋኝ ከእኛ ጋር ነው ያለው ፡፡ የምንሰራው ካሴት ሁሉ እስከ ጦር ግንባር ድረስ ነው የሚሸጠው፡፡ ከዛ ክፈሉን ስንላቸው አይሆንም በጀት ለዚህ ተብሎ የተያዘ የለም ብለው ሄዱ፡፡ ከአስር ይሁን ከአስራ አምስት ቀን በኋላ እሺ ይሁን ብለው ዳዊትን አነጋግረው በተወሰነ ብር ቀረፃው ተካሄደ፡፡ ግን የሚገርምህ በወቅቱ የተስማማነው ነገር የሚቀርፁትን ሙዚቃዎች ለስድስት ወራት ብቻ እንዲያጫውቱ ነበር ስምምነቱ፡፡ ያው በሌላ ሀገር የኮፒ ራይት ጉዳይ የሚባል ነገር አለ፡፡ ግን ያንን ማንም ያከበረው የለም፡ ፡ትንሽ ትንሽ የሮያሊቲ ክፍያ ቢደረግልን ኑሯችንን ይደግፍ ነበር፡፡
ቁም ነገር፡- ሮሃ ባንድ እስከ መንግስት ለውጥ ድረስ በብቸኝነት ሊባል በሚችል ሁኔታ ነበር የመድረክ ስራዎችንና ካሴቶችን የምትሰሩት፤ ሮሃ ባንድ ለምንድነው የፈረሰው?
አርቲስት ስምኦን፡- እንግዲህ የመንግስት ለውጥ ሲመጣ ከባንዳችን ጋር አብረው የነበሩት ሁለቱ ሙያተኞች ሰላምና ፈቃደ፤ አብረውን ሊቀጥሉ አልቻሉም ወደ ኤርትራ ነው የሄዱት፤ በዚህ ምክንያት ተዳከምን፡፡ እርግጥ ሌሎች ሙያተኞችን አስገብተን ለመቀጠል ተሞክሮ ነበር ፤ ግን አልሆነም፡ ፡ ከዛ በየግላችን እንጀራ ፍለጋ ወጣን ማለት ነው፡፡
ቁም ነገር፡- አርቲስት ኤፍሬም ታምሩ በቅርቡ ‹ሮሃ እንደገና› በሚል ርእስ የዱሮ ዘፈኖቹን ተጫውቷል፤ እዛ ውስጥ አለህበት?
አርቲስት ስምኦን፡- አለሁበት፤ አበጋዝ ስቱዲዮ ነው የተቀረፀው፤ ቀደም ሲልም ሮሃ ባንድ እያለን የተጫወትናቸው ዘፈኖች ስለነበሩ ተሰባስበን ነው የሰራነው፡፡ የኤፍሬምን ብቻ ሳይሆን የሌሎቹንም ተወዳጅ ዘፋኞች ስራዎች እንደገና ለመጫወት ነበር ሀሳቡ፡፡
ቁም ነገር፡-ከምሳሌ?
አርቲስት ስምኦን፡-የማህሙድ፤ የሐመልማል፤ የአረጋኸኝ የብዙዎቹን ለመስራት ሃሳብ ነበር፡፡
ቁም ነገር፡- አሁን ያለህበት ሁኔታ ምንድነው? ከኪቤአድ ጋር የተፈጠረው ችግር ምንድነው?
አርቲስት ስምኦን፡- ላለፉት ሰላሳ በላይ ዓመታት የኖርኩት በኪቤአድ ቤት ነው፡፡ ልጆች ወልጄ ያሳደግሁበት ቤት ነው፤ ድንገት መጥተው ቤቱን አሸጉት ጥር 23 ቀን፡፡
ቁም ነገር፡- ለምን ?
አርቲስት ስምኦን፡- የቤት ኪራይ ውዝፍ አልከፈልክም በሚል ነው፡፡ በውላችን መሠረት ግን ማስጠንቀቂያም አልሰጡኝ፤ አላነጋገሩኝም፡፡ ቤቴን ሲያሽጉ ያገኘሁት የኪቤአድ ውል እጄ ላይ አለ፡፡ መመልከት ትችላለህ፡፡ በአንቀፅ ሁለት ላይ የቤት ኪራይ ያልከፈለ ተከራይ ያለበት ውዝፍ በባንክ ወለድ እየታሰበ ይከፍላል ይላል እንጂ ከቤቱ ተጎትቶ ይወጣል አይልም፡፡
ቁም ነገር፡- አንተ ግን ያልከፈልከው ውዝፍ የቤት ኪራይ አለ?
አርቲስት ስምኦን፡- አዎ አለ፡፡
ቁም ነገር፡- ለምን አልከፈልክም?
አርቲስት ስምኦን፡- ምን ሆነ መሰለህ? ቤቴ ከላይ እያፈሰሰ ሽንት ቤት ሁሉ እየተለቀቀብኝ አሰሩልኝ ስል የሚሰማኝ አላገኘሁም፡፡ ከዛ እጄ ላይ ባለው ገንዘብ አስጠገንኩ፡፡ በዛ ላይ የነርቭ ታማሚ ነኝ፡፡ ያለሁት በፀበል ሀይል ነው፡፡ ታምሜ ምግብ ሁሉ መመገብ አቅቶኝ አርቴፊሻል ጥርስ ተገጥሞልኝ በእርሱ ሀይል ነው እንጀራ እንኳ ማኘክ የቻልኩት፡፡ በዚህ የተነሳ ተቸግሬ ቤት ኪራይ መክፈል አልቻልኩም፡፡ ከዛሬ ነገ እከፍላለሁ ስል በላዬ ላይ መጥተው አሸጉብኝ፡ ፡ ፂሜን እስክላጭ እንኳ ሊታገሱን አልቻሉም፡ ፡ሰው ይቸግረዋል፡፡ ለምን ተቸገርክ መንግስት እንዴት አይልም?
ቁም ነገር፡- ከመታሸጉ በፊት አቤቱታ አላቀረብክም?
አርቲስት ስምኦን፡- የተባለውን ሂሳብ ሁሉ እኮ ከፍያለሁ፡፡ ይኸው ደረሰኙን ማየት ትችላለህ፤ ግን የበላይ የሚባሉ ሀላፊዎች ጋር ገብቼ የሚያናግረኝ አላገኘሁም፡፡ እንደውም በማግስቱ ደውለውልኝ ዕቃህን የምትፈልግ ከሆነ መጋዘን ወስደን ሳናስገባ ቶሎ ውሰድ ነው ያሉኝ፡ ፡ እቃዬንም ወስደው ባዶ እጄን እንዳያስቀሩኝ ብዬ መኪና ተከራይቼ እቃዎቼን ዘመድ ቤት አስቀመጥኩ፡፡ያለ ምንም ማስጠንቀቂያ እንዲህ መደረጉ እኔስ ኢትዮጵያዊ አይደለሁም ወይ? ሀገሬን አላገለገልኩም ወይ ነው ያሰኘኝ፡፡
ቁም ነገር፡- የኪነ ጥበብ ባለሙያ መሆንህን ተናግረሃል?
አርቲስት ስምኦን፡- ቀድሞውኑ ማን አናግሮኝ? አንዲት ሀላፊ ብቻ የማውቀው ነገር የለም ብላ አመናጭቃኝ ከነባለቤቴ ተመልሰናል፡፤ ከዛ በኋላ አሉ የተባሉ የስራ ሀላፊዎች ጋር በቀጠሮ ነው የሚገባው ተብሎ ብሄድም ማንንም ማግኘት አልቻልኩም፡፡
ቁም ነገር፡- አሁን በምን ሁኔታ ላይ ነው ያለኸው?
አርቲስት ስምኦን፡- ጎዳና ላይ ነው ያለሁት ከነቤተሰቤ ለማለት እችላለሁ፡፡ ይህ መሆን የለበትም ያሉ ወዳጆቼ አንድ አነስተኛ መኝታ ተከራይተውልኝ ሻንጣዬን ይዤ ነው እየዞርኩ ያለሁት ፤ ባለቤቴና ልጆቼ በየሰው ቤት ነው ያሉት፡፡ እስከ መቼ እንደዚህ እንደምቆይ አላውቅም፡፡
ቁም ነገር፡- ስንት ልጆች አሉህ?
አርቲስት ስምኦን፡- ሁለት ፡፡እኔ ልጆች ወልጄ ሳሳድግ እንደዚህ አይነት ነገር ይገጥመኛል ብዬ አስቤ አላውቅም፡፡ እንደ ሌሎቹ ቁልፍ የሸጥኩ ሰው አይደለሁም፡፡ ደባል ያስገባሁ አይደለሁም፡ ፤ ይህን ያህል ዓመት ኖሬበት ጎትተው ሲያስወጡን የኢትዮጵያ ህዝብ ይፍረደኝ ነው የምለው፡፡
ቁም ነገር፡- ለሙዚቀኞች ማህበርና ለአርቲስቶች አስታውቀሃል?
አርቲስት ስምኦን፡- ዘግይቼ ነው ከነ ዳዊት ጋር ባለፈው ሳምንት የተነጋገርነው፡፡ ቀደም ሲል የነበረብኝን ችግር አሳውቄ ቢሆን ኖሮ አሁን የገባሁበት ችግር ውስጥ ላልወድቅ እችል ነበር፡፡
ቁም ነገር፡- እነዛን የመሳሰሉ ሙዚቃዎች ከተጫወቱ አርቲስቶች መሀከል አንዱ ነህ፤ አሁን ምን ይሰማሃል?
አርቲስት ስምኦን፡- ሞራሌ ተነክቷል፡፡ ልቦናዬ ተሰብሯል፡፡ ያም ሆኖ መብቴን በፍርድ ቤት ለመጠየቅ ወደ ክስ ሄጃለሁ፡፡ ለዚህ ነው እንዴ ስለፋ የኖርኩት? እንድል አድርጎኛል፡፡ያም ሆኖ በሙዚቃ ሳገለግለው የኖርኩት የኢትዮጵያ ህዝብ እንዲያውቅልኝ እፈልጋለሁ፡፡
ቁም ነገር፡- አብረሃቸው የሰራሃቸው አርቲስቶች እንዲያውቁ አድርገሃል?
አርቲስት ስምኦን፡- አላደረግሁም፤ አሁን ነው በእናንተ መፅሔት እንዲያውቁ እያደረግሁ ያለሁት፡፡ ሜዳ ላይ ነው ያለሁት፤ወንድ ልጅ አያለቅስም ይባላል፤ እኔ ግን ከደረሰብኝ ግፍ የተነሳ አልቅሻለሁ፡፡ ጤናዬ መታወክ ሲጀምር ነው ሰዎች ተቆጥተው ያረጋጉኝ፡፡ ቁም ነገር፡- አመሰግናለሁ፡፡
ከአዘጋጁ፡- ጉዳዩን በተመለከተ ለመጠየቅ የኪራይ ቤቶች አስተዳደር ሃላፊዎችን ምላሽ ለማግኘት ያደረግነው ጥረት ስበስባ ላይ ናቸው በሚል ሊሳካልን አልቻለም፡ ፡ ምላሽ ካላቸው የምናስተናግድ መሆኑን እንገልጻለን፡፡
(ምንጭ ቁም ነገር መጽሔት የካቲት 2009)

